የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዲያ ሆሳዕና 0-1 ፋሲል ከነማ 

በ7ኛ ሳምንት እጅግ ተጠባቂ የነበረውና ፋሲል ከነማ በሙጂብ ቃሲም ብቸኛ ግብ ሀዲያ ሆሳዕናን ከረታበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዩን ሀሳብ ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።

አሸናፊ በቀለ – ሀዲያ ሆሳዕና

ወደ አጥቂነት በቀየረው ሙጂብ ቃሲም ቡድኑ ግብ ስለማስተናገዱ

“ያው ያሳደከው ልጅ ጥሩ ቦታ ሲደርስ ደስ ይላል። ሙጂብ ገና ከዚህ በላይ በጥሩ ሁኔታ ይሄዳል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ሙጂብ ከበረኛ ውጭ የትም ቦታ ላይ መጫወት ይችላል፤ ሁለገብ ተጫዋች እና ለሀገርም ተስፋ ሰጪ ተጫዋች ነው።”

ጥንቃቄን መርጠው ስለመጫወታቸው

“ለዚህ የዳረገን አብዘኛዎቹ ተጫዋቾች ህመም ላይ መገኘታቸው ነው። ለምሳሌ ግብ ጠባቂያችን ከአልጋ ተነስቶ ነው የመጣው። ስለዚህ የተጎዱብን ልጆችን ታሳቢ በማድረግ ስናጠቃም ስንከላከልም የምንበዛበትን መንገድ ታሳቢ አድርገን ነበር የገባነው።”

የተጫዋቾች ጉዳት በዛሬ ጨዋታ ስለፈጠረባቸው ጫና

“ምንም ጥያቄ የለውም። ምክንያት እንዳይንብኝ እንጂ ሳሊፉ ፎፋና እና ቢስማርክ አፒያን የመሰሉ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾችን ማጣት በእርግጥም ጎድቶናል።”

ሥዩም ከበደ – ፋሲል ከነማ

ከጫና የወጣበት ውጤት ስለመሆኑ

“ፋሲል ከነማ እጅግ ብዙ ደጋፊ ያለው ትልቅ ክለብ ነው ፤ መላው ደጋፊያችን ዘንድሮ ሻምፒዮን መሆን ህልሙ ነው እኛም ያንን ለማሳካት እየሰራን እንገኛለን በዚህ ጉዞ ውስጥ ብዙ ውጣ ውረድ አለ ያንን ተቋቁመን እዚህ ደርሰናል። በተለይ ደግሞ በዛሬው ጨዋታ ያለመሸነፍ ግስጋሴ ላይ የነበረውን ቡድን ማስቀረታችን ለእኛ ትልቅ ነገር ነው፤ ለቀጣይ ጨዋታ ትልቅ ጥንካሬ ይሆነናል ብዬ አስባለሁ። በተጨማሪም ብዙ ነገር ለሆኑልን የፋሲል ደጋፊዎች እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እወዳለሁ።”

ስለ ሙጂብ ቃሲም

“ከዚህ በፊትም ደጋግሜ ተናግሬዋለሁ። የሙጂብ ዋነኛ አቅም ሳጥን ውስጥ ክፍት ቦታዎችን መፍጠር፣ ሳጥን ውስጥ ከገባ በኋላም እንዲሁ ዝም ብሎ በጭፍን ሳይሆን አስቦ የሚያደርጋቸው ነገሮች በልምምድም ሆነ በጨዋታ ላይ የሚያደርጋቸው ነገሮች ናቸው። አሁን ላይ ስኬቱ ጥሩ ነው። በዚህ የሚቀጥል ከሆነ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን የሚፎካከረው አይኖርም።”


© ሶከር ኢትዮጵያ