“ለኢትዮጵያውያን ግብጠባቂዎች ምሳሌ መሆን እፈልጋለው” ጀማል ጣሰው

በቋሚነት ለመጫወት ከዓመታት በኃላ ያገኘውን ዕድል በአግባቡ እየተጠቀመ የሚገኘው ጀማል ጣሰው ስለተበረከተለት ሽልማት እና ስለሌሎች ጉዳዮች ይናገራል። 

ከ1997- 2000 በአሳዳጊ ክለቡ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከታችኛው እስከ ዋናው ቡድን መጫወት ችሏል። ሀዋሳ፣ ደደቢት፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ መከላከያ፣ ጅማ አባ ቡና፣ ድሬዳዋ ከተማ ተጫውቶም አሳልፏል። በግብ ጠባቂነት ህይወቱ በተለያዩ ጊዜያት ከበድ ያለ ጉዳቾች የማያጣው ይህ ምርጥ ግብ ጠባቂ በ2002 ለደደቢት እየተጫወተ ባለበት ወቅት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ተጫዋቾች ምርጫ ታሪክ የመጀመርያውና ብቸኛው ግብ ጠባቂ በመሆን ችሏል። በ2005 በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው መሪነት ወደ አፍሪካ ዋንጫ ያቀናው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወሳኝ አባል የነበረው ጀማል ጣሰው በ2009 በጅማ አባቡና መለያ በቋሚነት ሲጫወት ከተመለከትነው ወዲህ በድሬዳዋ ከተማ እና ፋሲል ከነማ ሜዳ ላይ ከተሰለፈባቸው ደቂቃዎች የሚልቁትን ጊዜያት በተጠባባቂነት ለማሳለፍ ተገዷል። ዘንድሮ ወደ ወልቂጤ ከተማ ካደረገው ዝውውር በኃላ ግን በቋሚነት እየተመለከትነው እንገኛለን። ደፋር እና ለውሳኔዎች ፈጣን የሆነው ጀማል ያለውን ከፍተኛ ልምድ ለቡድኑ እያበረከተ ይገኛል። ይህን ብቃቱን ከግምት በማስገባት ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት የወልቂጤ ደጋፊዎች ጀማል ጣሳውን የወሩ የክለቡ ምርጥ ተጫዋች በማድረግ የማስታወሻ ስጦታ እና የ10,000 ሽልማት አበርክተውለታል። በዚህም መነሻነት ከጀማል ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ሀሳቡን አጋርቶን እንዲህ አሰናድተነዋል።

“ልምዴን ተጠቅሜ ቡድኑን እያገዝኩ ነው። ለሦስት ዓመት ሳልጫወት ቀርቻለሁ። አሁን ደግሞ የመጫወት ዕድል አግኝቼ በመጫወት ላይ እገኛለሁ። ገና ከዚህ በኃላ ለኔ ብቻ አይደለም ለኢትዮጵያውያን ግብጠባቂዎች ምሳሌ መሆን እፈልጋለው። ብዙዎች አሉ መጫወት እየቻሉ ዕድል አጥተው የተቀመጡ። እንደምንችል አቅም እንዳለን ማሳየት እፈልጋለሁ። ከዚህ በፊት አንድ ክለብ ስጫወት አንድ ስህተት ሰርቼ ነው ብዙ ጊዜ ያስቀመጡኝ፤ ትግስት የላቸውም፤ ጊዜ አይሰጡንም። ይህን ዘንድሮ እኔ ብቻ ሳልሆን ፍሬውን ተመልከት፤ ዛሬ የአዳማው ዳንኤልን ተመልከት፤ የቡና ግብጠባቂዎች፣ የሰበታውን ፋሲል አስብ፤ ኢትዮጵያውያን በረኞች እንደምንችል ማሳያ ነው። ለዓመታት የተቀመጥንበት መንገድ ተገቢ አይደለም። የውጭ ግብጠባቂዎች አይችሉም እያልኩ አይደለም። ግን ምን ያህል እንደሚሳሳቱ እየተመለከትን ነው። እነርሱ ሲሳሳቱ ደግመው ዕድል ያገኛሉ። ለእኛ ግን ጊዜ አይሰጠንም። ስለዚህ ለኢትዮጵያውያን በረኞች የሚሰጠው ግምት መቀየር አለበት። ሁሉም ልብ ሊለው ይገባል። ግብጠባቂ ላይ ብቻ ችግር እንዳለ ይወራል። ሌላ ቦታስ? ይህ መስተካከል አለበት። ሁላችንም ዕድሉን ካገኘን ብዙ ነገር ማሳየት እንችላለን።

“ወልቂጤ ባለኝ ቆይታ ደስተኛ ነኝ። ልምዴም በጣም ጠቅሞኛል። ቡድኑን በአንበልነት እየመራሁ ነው። በዚህም በየጨዋታው ልጆቹን እመክራለው አስተባብራለው አነሳሳሳለው። ይህ የሆነው ልምዴ ብቻ ሳይሆን አብረውኝ የሚጫወቱት በሙሉ የምላቸውን ስለሚሰሙኝ ነው። ከወልቂጤ ጋር ሁላችንም ዘንድሮ ከዚህ የተሻለ አንድ ነገር ለመሥራት እናስባለን።

“ለሽልማቱ በጣም አመሰግናለሁ። የዛሬው ሽልማት ለኔ ብቻ ሳይሆን ለቡድኑ አባለት በሙሉ የተሰጠ ሽልማት ነው። ይህ መለመድ አለበት። ለተጫዋቾች የበለጠ እንዲሰሩ የሚያነቃቃ ትልቅ ሀሳብ ነው። በቀጣይ ሁላችንም ቡድኑን አመራሮች እና ደጋፊዎቻችንን ለማስደሰት የበለጠ ጠንክረን እንሰራለን።”


© ሶከር ኢትዮጵያ