ሪፖርት | የሳላሀዲን ሰዒድ ጎል ጊዮርጊስን ባለ ድል አድርጋለች

በስምንተኛው ሳምንት የቤት ኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዛሬ ከሰዓት በኋላ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወላይታ ድቻን 1-0 ማሸነፍ ችሏል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ጅማ አባ ጅፋርን ካሸነፈበት ጨዋታ ባደረጋቸው ለውጦች በአማኑኤል ተርፋ ፣ ሀይደር ሸረፋ እና አማኑኤል ገብረሚካኤልን ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ በማስገባት ምንተስኖት አዳነ ፣ ሙሉዓለም መስፍን እና ሮቢን ንግላንዴን አሳርፏል። በአንፃሩ በወላይታ ድቻ በኩል ከመጨረሻው የሰበታ ጨዋታ ፊት መስመር ላይ ቢኒያም ፍቅሬ በያሬድ ዳርዛ ተተክቷል።

የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ እንቅስቃሴ የተቀዛቀዘ ነበር። ሁለቱም ቡድኖች የተጋጣሚዎቻቸውን የማጥቂያ መንገዶች በአግባቡ መቆጣጠር የቻሉበትን አጋማሽ ነበር ያሳለፉት። የጊዮርጊስን የመስመር ጥቃት ወደ ሳጥናቸው እንዳይደርስ ማድረግ የቻሉት ድቻዎች ለፀጋዬ ብርሀኑ እና ቢኒያም ፍቅሬ የግብ ዕድሎችን መፍጠሩ ላይ ግን ተዳክመዋል። በሙከራ ደረጃ በድቻ በኩል 34ኛው ደቂቃ ላይ ደጉ ደበበ ከማዕዘን የተሻማን ኳስ በግንባሩ የገጨበት ሙከራ ብቻ ተጠቃሽ ነበር። ጊዮርጊሶችም እንዲሁ ረጃጅም ኳሶችን ወደፊት ለመጣል ቢሞክሩም በድቻ ሦስት የመሀል ተከላካዮች በቀላሉ ይመለሱባቸው ነበር። አቤል ያለው 7ኛው ደቂቃ ላይ በግራ በኩል ከሳጥን ውስጥ ያደረገው ሙከራ ካልሆነ በቀር ቡድኑ የመጨረሻ የግብ ዕድል መፍጠር ሳይችል ወደ ዕረፍት አምርቷል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር ሳላሀዲን ሰዒድን ቀይረው ያስገቡት ጊዮርጊሶች ነቃ ብለው ታይተዋል። በጌታነህ ከበደ እና የአብስራ ተስፋዬ ከሳጥኑ መግቢያ አቅራቢያ ሙከራዎች ያደረጉት ፈረሰኞቹ 60ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። አቤል ያለው ያሻማውን የማዕዘን ምት አማኑኤል ገብረሚካኤል በግንባሩ ቢገጭም ሙከራው የግቡን ቋሚ ታክኮ ወጥቶበታል። ቀስ በቀስ የተፈጠረባቸውን ጫና መቆጣጠር የቻሉት ድቻዎች በበኩላቸው ፀጋዬ ብርሀኑ እና ቸርነት ጉግሳን ለውጠው በማስገባት የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ለመጠቀም ሲሞክሩ ታይተዋል። ሆኖም ወደ ፊት ሲሄዱ በተደጋጋሚ ከጨዋታ ውጪ ሲሆኑ ይታይ ነበር።

ድቻዎች ወደ ራሳቸው ሜዳ ተስበው ወደ ጥንቃቄው ይበልጥ ባደሉባቸው የመጨረሻ 15 ደቂቃዎች ጊዮርጊሶች ወደ ፊት ገፍተው ለማጥቃት ጥረት አድርገዋል። በዚህም 83ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ አዱኛ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ሳላሀዲን ሰዒድ በግንባሩ በመግጨት ወሳኟን ግብ አስቆጥሯል። በቀሩት ደቂቃዎች ድቻዎች በተለይም ከቆሙ ኳሶች አቻ ለመሆን ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ጨዋታው በ 1-0 ውጤት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ