ቅድመ ዳሰሳ | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ወላይታ ድቻ

በጊዮርጊስ እና በድቻ ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

የሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ አሰልጣኝ በመሆን የተመረጡት አሰልጣኝ ማሂር ዴቪድስን አዲሱን ሹመታቸውን ከተረከቡት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው የሚያገናኘው ጨዋታ በሁለት የውጤት ፅንፍ ላይ የሚገኙትን ቡድኖች ነገ አመሻሽ ላይ ያፋልማል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሸገር ደርቢው ሽንፈት በቶሎ ማገገም ችሏል። ጅማን ያሸነፈበት ውጤት ብቻ ሳይሆን ያሸነፈው ከመመራት ተነስቶ መሆኑ ድሉ ይበልጥ የቡድን መነሳሳቱን ከፍ የሚያደርግለት ሆኖ ነበር ያለፈው። በበድኑ ውስጥ በችግርነት የቀጠለው እና በጉልህ የታየው ጉዳይ ግን የመከላከል ችግሩ ነው። ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ስድስት ግቦችን ያስተናገደው ጊዮርጊስ እንደ ፊት መስመሩ ጥንካሬ ባይሆን ኖሮ ከባድ ችግር ውስጥ በገባ ነበር። በጅማው ጨዋታ እንደቡድን ያሳየው ደካማ የመከላከል አደረጃጀት ከግለሰባዊ ስህተቶች ጋር ተዳምረው የቡድኑ የኋላ ክፍል እንዲዳከም አድርገውት ታይቷል።

ወደ መከላከል የሚደረጉ ሽግግሮች ላይ ተበታትኖ መታየት እና የቅብብል ስህተቶችን መስራት በተጋጣሚ አጥቂዎች ዘንድ ጫና ውስጥ ሲከተው የሚታየው ጊዮርጊስ ምን አልባት ችግሩ በተጣበበው የጨዋታ ቀናት ውስጥ ወጥነት ያለው ቡድን ከመጠቀሙ አንፃር የመጣ ከሆነ ነገ መጠነኛ ለውጦችን ሊያደርግ ይችላል። ከዚህ አንፃር እና በማጥቃቱ ረገድም ከነበረው በጎ ውጤት አኳያ አሰልጣኝ ማሂር ዴቪድስ በጅማው ጨዋታ ሁለተኛ አጋማሽ እንዳደረጉት በሦስት የኋላ ተከላካዮች የሚጀምር አደራደር ይዘው ሊቀርቡም ይችላሉ። በተመሳሳይ አኳኋን ቡድኑ ይህንን ችግሩን ካልቀረፈ ግን የመልሶ ማጥቃት አቀራረብ ሊኖረው እንደሚችል ፍንጭ በሰጠው ወላይታ ድቻ ፈተና ሊገጥመው ይችላል።

ወላይታ ድቻ ከአራት ጨዋታዎች በኋላ መረቡን ሳያስደፍር እንዲሁም አንድ ነጥብ ይዞ የወጣበትን ጨዋታ አሳልፎ ለነገው ግጥሚያ ደርሷል። የቡድኑን ዋና አሰልጣኝነት ኃላፊነት የረከቡት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው በታደሙበት ጨዋታ ድቻ ጥሩ የመከላከል አደረጃጀት ታይቶበታል። ከዚህ ባለፈ የመልሶ ማስትቃት እሳቤ ሊኖረው እንደሚችል የሚጠቁም እንቅስቃሴም ነበር ያደርገው። ይህም ነገ በተመሳሳይ አኳኋን የቅዱስ ጊዮርጊሶችን የማጥቃት መስመር በመዝጋት በተለይም ፀጋዬ ብርሀኑ በሚሰለፍበት የቡድኑ የቀኝ ወገን የሚያመዝን ፈጣን ጥቃትን መሰንዘር ምርጫው ሊያደርግ እንደሚችል የሚጠቁም ነው።

ወደ ቀደመ የቡድን ትጋታቸው እየተመለሱ ያሉ የሚመስሉት ድቻዎች በዚህ ሁኔታ ተጋጣሚያቸውን ለመፈተን የሚያስችል የቡድን ውህደት ላይ መድረስ ከተሳካላቸው ለቀጣይ ጨዋታዎች ከእስካሁኑ አመጣጣቸው ፍፁም የተለየ አቀራረብ የዘው እንደሚቀጥሉ ማረጋገጫ ይሆናል። ይህ እንዲሆን ግን በአመዛኙ በስንታየሁ መንግሥቱ ላይ ተመርኩዞ የነበረው ግብ የማስቆጠር ኃላፊነትን የሚወጣ እና ከተከላካይ ጀርባ የሙጣሉ ኳሶችን በፍጥነት በመግባት መጠቀም የሚችል አጥቂ በእጅጉ ያስፈልገዋል። ድቻዎች ይህን ኃላፊነት ተከታታይ ዕድል በተሰጠው ያሬድ ዳርዛ ላይ ጥለው ይገባሉ ወይስ ሌላ አማራጭ ይፈልጋሉ የሚለው ጉዳይ በነገው ጨዋታ ምላሽ እንደሚያገኝ ይጠበቃል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በቀጥታ ቀይ ካርድ ሁለተኛ የጨዋታ ቅጣቱን የሚያሳልፈው ግብ ጠባቂው ፓትሪክ ማታሲ ሌላ በጉዳት የሚያጣው ተጫዋች የሌለ ሲሆን በወላይታ ድቻ በኩል ስንታየሁ መንግሥቱ እና እዮብ ዓለማየሁ አሁንም ከጉዳታቸው አለማገገማቸው ተሰምቷል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 12 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 5 ጊዜ ሲያሸንፍ ወላይታ ድቻ (አንድ ፎርፌ ጨምሮ) አራቱን ድል አድርጓል። ቀሪዎቹን ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

– በአስራ ሁለቱ ጨዋታዎች ፈረሰኞቹ 17 ጎሎች ሲያስቆጥሩ የጦና ንቦቹ ደግሞ (ሦስት የፎርፌ ጎሎች ጨምሮ) 11 ጎሎች አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-2-3-1)

ለዓለም ብርሀኑ

ሄኖክ አዱኛ – አስቻለው ታመነ – ምንተስኖት አዳነ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ

ሀይደር ሸረፋ – የዓብስራ ተስፋዬ

ጋዲሳ መብራቴ – ሮቢን ንግላንዴ – አቤል ያለው

ጌታነህ ከበደ

ወላይታ ድቻ (3-5-2)

መክብብ ደገፉ

አንተነህ ጉግሳ – ደጉ ደበበ – መልካሙ ቦጋለ

አናጋው ባደግ – እንድሪስ ሰዒድ – በረከት ወልዴ – ኤልያስ አህመድ – ያሬድ ዳዊት

ፀጋዬ ብርሀኑ – ቸርነት ጉግሳ


© ሶከር ኢትዮጵያ