በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ሰባተኛ ሳምንት የተጠበቀው የሀዋሳ ከተማ እና ንግድ ባንክ ጨዋታ በንግድ ባንክ 4 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
በሠንጠረዡ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ላይ ያሉትን ቡድኖች ያገናኘው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ፊት መስመር ላይ ሲያደርጉ የነበረው እንቅሴቃሴ እጅጉን ለሀዋሳ ተከላካዮች ፈታኝ የነበረ ሲሆን በአንፃሩ ወደ ጎል በመድረስ ሀዋሳዎች ባይቸገሩም ፍፁም የአጨራረስ ድክመት ግን ዋጋ አስከፍሏቸዋል፡፡ ገና በጊዜ በቅብብብል ሂደት ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል መጠጋት የጀመሩት ባንኮች በሰናይት ቦጋለ ሙከራ ቀዳሚውን ቦታ ይዘዋል፡፡በተደጋጋሚ የማይቋረጥ የማጥቃት ኃይል ይታይባቸው የነበሩትን የአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ተጫዋቾች በሎዛ አበራ ረሂማ ዘርጋው እንዲሁም ከቆሙ ኳሶች ደግሞ በገነሜ ወርቁ የርቀት ሙከራን ማድረግ ችለዋል፡፡ በዚህ ፈጣን እንቅስቃሴ የቀጠለው ጨዋታው 20ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ተገኝቶበታል፡፡ የሀዋሳዋን ፍፁም የመከላከል እና የአቋቋም ስህተት ተመልክታ ሰናይት ቦጋለ የሰጠቻትን ኳስ ሎዛ አበራ በድንቅ አጨራረስ አስቆጥራው ባንክን መሪ ማድረግ ችላለች፡፡
የአጨራረስ ድክመት እየታየባቸው የመጣው እና መሀል ሜዳው ላይ ሁነኛ ፈጣሪ ተጫዋች ያልነበራቸው ሀዋሳ ከተማዎች ወደ ንግድ ባንክ የግብ ክልል ሲደርሱ ቢስተዋልም የአጥቂዎቹ መሳይ ተመስገን እና ረድኤት አስረሳኸኝ ደካማ የውሳኔ አሰጣጥ ቡድኑ ወደ ጨዋታ እንዳይመለስ ያደረጉ ነበሩ፡፡ ሆኖም የሀዋሳን ደካማ የመከላከል አደረጃጀት በሚገባ በመጠቀሙ የተዋጣላቸው ንግድ ባንኮች 33ኛው ደቂቃ በድጋሚ የሀዋሳን መረብ ደፍረዋል፡፡ የሀዋሳዋ የግራ ተከላካይ ካሰች ፍሰሀ ኳስን ለማቀበል ስትል ስህተት በመፈፀሟ ከጀርባዋ የነበረችሁ ትዕግስት ያደታ ጋር ደርሶ ተጫዋቿ በፍጥነት ስታሻማ አምበሏ ረሂማ ዘርጋው በጥሩ አቋቋም ላይ በመሆኗ በግንባር ገጭታ በማስቆጠር የክለቡን የግብ መጠን ከፍ ማድረግ ችላለች፡፡ከግቧ በኃላ በአረጋሽ ካልሳ እና ሎዛ አበራ ተጨማሪ የማግባት ዕድልን አግኝተው ሳይጠቀሙ ቀርተዋል፡፡
ከእረፍት መልስ በነበረው የጨዋታ እንቅስቃሴ ሀዋሳ ከተማዎች የሜዳውን ሙሉ አካል መጠቀም ቢችሉም ለመልሶ ማጥቃት ተጋላጭ በመሆናቸው እና በመከላከሉ ረገድ ከወትሮው ቀዝቅዘው መታየታቸው ተጨማሪ ጎሎችን ለማስናገድ አስገድዷቸዋል፡፡ ሀዋሳ ከተማዎች ቶሎ ቶሎ ወደ ንግድ ባንክ የግብ ክልል በፍጥነት በመድረስ እንዲሁም ደግሞ ቀላል የማይባሉ ዕድሎችን መፍጠር ቢችሉም ከግብ ጋር ለመቆራኘት ግን አልቻሉም በተለይ አጥቂዎቹ ረድኤት አስረሳኸኝ እና መሳይ ተመስገን ያደረጓቸው ያለቀላቸው አጋጣሚዎች እጅጉን አስቆጪዎች ነበሩ፡፡በተለይ ከቅጣት ምት መሳይ እና ረድኤት ከተመሳሳይ አቅጣጫ ሞክረው የንግድ ባንኳ ግብ ጠባቂ ንግስቲ መዐዛ አስደናቂ ብቃት ጎል ከመሆን አትርፏቸዋል፡፡
በቀኝ በኩል ከመከላከል ወደ ማጥቃት ሽግግሩ ለቡድኗ ጎል ለማስቆጠር የታተረችው ካሰች ፍሰሀ አንድ የጠራ ዕድል ስታበክን ሁለተኛ ኳስ አግኝታ ወደ ጎለልነት ብትለውጠውም ከጨዋታ ውጪ ተብሎ ተሽሯል፡፡ ሆኖም የሀዋሳን የመከላከል ድክመት በሚገባ የተረዱ የሚመስሉት ንግድ ባንኮች በመልሶ ማጥቃት ሶስተኛ ጎላቸውን አግኝተዋል፡፡ አረጋሽ ካልሳ ከግራ በኩል አክርራ መታ በአባይነሽ ኤርቄሎ ሲመለስ ተከላካዮች ኳስን ለማውጣት የነበራቸው የላለ ውሳኔ በቀላሉ ረሂማ ዘርጋው ጋር ደርሶ ወደ ጎልነት ተለውጧል፡፡
መሀል ሜዳ ላይ ድክመት የነበረባቸው ሀዋሳዎች ዙፋን ደፈርሻንን ዮዲት መኮንን በማስገባት የተደራጀ የጨዋታ ቅርፅን ለመፍጠር ሞክረዋል፡፡ በማጥቃቱ ወረዳም ምስር ኢብራሂምን አስገብተው ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ይሁን እንጂ በዛሬው ጨዋታ የአቋምም ስህተት በተከላካይ መስመር ላይ ይታይባቸው የነበሩት ሀዋሳዎች 87ኛው ደቂቃ ረሂማ ዘርጋው ጣጣውን የጨረሰ ኳስ ሰጥታት ሎዛ አበራ ለራሷ ሁለተኛ ለንግድ ባንክ አራተኛ ጎል አግብተለች።
ሀዋሳዎች በቀረው ደቂቃ በመሳይ ተመስገን አማካኝነት ሁለት ዕድልን አግኝተው የነበረ ቢሆንም መጠቀም ባለመቻላቸው ተጠባቂው ጨዋታ 4 ለ 0 የንግድ ባንክ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ንግድ ባንክም ያደረጋቸውን ሰባት ጨዋታዎች በመርታት በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ በ21 ነጥብ ሲቀመጥ ሀዋሳ ከተማ ባለበት ሁለተኛ ደረጃ በ16 ነጥቦች ተቀምጧል፡፡
ጨዋታው ከሰዓት ቀጥሎ ሲውል ድሬዳዋ ከተማ ተከታታይ ድሉን ለማግኘት አርባምንጭ ከተማ ወደ አሸናፊነት ለመግባት ብርቱ ፉክክርን 10፡00 ላይ ያደርጋሉ፡፡
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ልሳን የሴቶች ስፖርት ረሂማ ዘርጋውን የጨዋታው ምርጥ በማለት ሲሸልም ሎዛ አበራ በሀዋሳ በምትጫወትበት ወቅት በታዳጊነቱ እያያት ያደገው ኪሩቤል የተባለ ወጣት ለሎዛ የማስታወሻ ስጦታ አበርክቶላታል።
© ሶከር ኢትዮጵያ