የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የዛሬው ተጠባቂ ጨዋታ በዐፄዎቹ የበላይነት እንዲጠናቀቅ ለሙጂብ ቃሲም ጎል በጥሩ ሁኔታ ወደፊት ካሻገረው ተስፈኛው ወጣት ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ጋር ቆይታ አድርገናል።
ጎንደር ዩኒቨርስቲ የፕሮጀክት ቡድን የተገኘው ይህ ወጣት በጎንደር ከተማ አስራ ስምነት አካባቢ ተወልዷል። በአሰልጣኝ ውበቱ ዘመን በ2009 ከተስፋ ቡድን ወደ ዋናው ቡድን ማደግ ችሏል። በ2012 በኮሮና ቫይረስ በተሰረዘው የውድድር ዘመን ለመጀመርያ ጊዜ ሀዋሳ ከተማ ላይ ዐፄዎቹ ከሀዋሳ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ተቀይሮ በመግባት ለዋናው ቡድን አገልግሎት መስጠትም ጀምሯል። በዘንድሮ ዓመት ደግሞ በባህር ዳር ጨዋታ ተቀይሮ በመግባት ቡድኑን ከመሸነፍ የታደገውን የአቻነት ጎል ያስቆጠረው ይህ ወጣት ነው። በተመሳሳይ ፋሲሎች ወላይታ ድቻን 3–2 በረቱበት ጨዋታ ወሳኙን ሦስተኛ ጎል ሙጂብ ቃሲም በፍፁም ቅጣት ምት እንዲያስቆጥር ጥፋት ተሰርቶበት ምክንያት የሆነው ይህ ተስፈኛ ወጣት ነው። በዛሬው ዕለትም ተቀይሮ በመግባት ዐፄዎቹ የሊጉ መሪ እንዲሆኑ ያስቻለውን ለሙጂብ ቃሲም ጎል ጥሩ ዕድል መፍጠር የቻለው ናትናኤል መሆኑን ስናስብ ይህ ተጫዋች ወደ ፊት ተስፋ የሚጣልበት ወጣት መሆኑን አመላካች ነገር ነው። በሦስት ጨዋታ ተቀይሮ በመግባት አንድ ጎል በማስቆጠር ሁለት የጎል ዕድል ከፈጠረው ፈጣኑና ሁለገቡ አጥቂ ናትናኤል ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርገናል።
” ዘንድሮ የመሰለፍ እድል እንደማገኝ ተስፋ አደርግ ነበር። ከባለፈው ዓመት በተሻለ በዚህ ዓመት በሦስት ጨዋታዎች ላይ ተቀይሬ በመግባት ጎል በማስቆጠር እና ሁለት የጎል ዕድሎችን በመፍጠር ከፈጣሪ ጋር ለቡድኔ ውጤት የተሻለ ነገር እያደረኩ እገኛለው። ከዚህ በኃላም የምችለውን በሚሰጠኝ እድል ተጠቅሜ የተሻለ ነገር ለመሥራት አስባለሁ። አሰልጣኞቼ ተቀይሬ ወደ ሜዳ ስገባ የጎል ዕድል እንድፈጥር ይነግሩኛል። እኔም ይህን ተግባራዊ ለማድረግ እየጣርኩ እገኛለው። በቀጣይ ጥረቴን ቀጥዬ ወደ መጀመርያ አሰላለፍ ለመግባት አስባለሁ። በዚህም ብቻ ሳልቆም ከፈጣሪ ጋር ጠንክሬ በመሥራት ለሀገሬ ብሔራዊ ቡድን መጫወት አስባለሁ።”
ከወራት በፊት ይህን ወጣት ተጫዋች በተስፈኛ አምዳችን ባቀረብንበት ወቅት ተከታዩኑ ሀሳብ ሰጥቶን ነበር። ሊንኩን ተጭነው ያንብቡ:-
LINK | “ዘንድሮ የተሻለ የመሰለፍ ዕድል ለማግኘት ጥረት አደርጋለሁ”
© ሶከር ኢትዮጵያ