የአሠልጣኞች አስተያየት | አዳማ ከተማ 0-1 ወልቂጤ ከተማ

አንድ ለምንም ከተጠናቀቀው የአዳማ እና ወልቂጤ ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሠልጣኞች አስተያየታቸውን ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል። 

አስቻለው ኃይለሚካኤል – አዳማ ከተማ

ስለ ቡድኑ እንቅስቃሴ

ከዚህ በፊትም እንደገለፅኩት ነው። እንደ አቅማችን መሻሻሎች አሉን። ሲጀምርም እንደ አቅማችን ሆነን ነው ትልቁን አዳማ ለመገንባት እየሞከርን ያለነው። ግን ጊዜ ያስፈልገናል። ምንም ቢሆን ግን ከዕለት ዕለት ለውጦች አሉ። አብዛኞቹ ተጫዋቾች ወጣቶች ናቸው። ቡድኑም አዲስ ነው። እኔ በሂደት ጥሩውን አዳማን ለመሥራት ነው እየጣርኩ ያለሁት።

ስለ ግብ ጠባቂው አቋም…

ዳንኤል ከነ ሥነ-ስርዓቱ ታጋሽ የሆነ ግብ ጠባቂ ነው። በፊት በነበሩት የአሠልጣኝ ቡድን አባላት ምርጫ ውስጥ በነበሩት ሁለት የውጪ ዜጋ ግብ ጠባቂዎች ተሸፍኖ የነበረ ነው። ከደፈርን በሀገራችን ጥሩ ጥሩ ግብ ጠባቂዎች እንዳሉ ማሳያ ነው። በነበሩት ዜጋ ግብ ጠባቂዎች ተሸፍኖ የነበረ ቢሆንም አሁን ያገኘውን እድል ተጠቅሞ አቅሙን እያሳየ ነው። ዛሬም ጥሩ ተጫውቷል።

ደግአረገ ይግዛው – ወልቂጤ ከተማ

ስለ ጨዋታው…

ጅማ ላይ የምናደርገውን ጨዋታ በሙሉ ሦስት ነጥብ ለመጀመር ነበር ዛሬ እንቅስቃሴ ያደረግነው። ይህንን ለማሳካት በሄድንበር እንቅስቃሴ በመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ተጫዋቾቼ በጥድፊያ ውስጥ ሆነው ነበር ሲጫወቱ የነበረው። መረጋጋቶች አልነበሩም። የተገኙትን የግብ እድሎችም በስክነት የተገኙ አልነበረም። በሁለተኛው አጋማሽ ግን ይህንን አሻሽለን የተሻለ እንቅስቃሴ ተጫዋቾቼ አሳይተዋል። ከጎሉም በኋላ ተጫዋቾቼ ሦስት ነጥቡን ለማስጠበቅ በሚመስል መልኩ ጫናዎች ነበሩባቸው። ተጋጣሚያችንም ረጃጅም ኳሶችን ሲጠቀም ነበር። የሆነው ሆኖ ግን ተጫዋቾቼ ባደረጉት ተጋድሎ አሸንፈን ወጥተናል።

በጨዋታው ላይ ቡድኑ ስላደረገው የጨዋታ ለውጥ

መጀመሪያ ያሰብነውን ነገር በጨዋታው ለውጠናል ብዬ አላስብም። መጀመሪያም በጋራ ኳስን የመጫወት እቅድ ይዘን ነበር ስንጫወት የነበረው። ማለትም ኳስን ይዘን መስርተን ለመጫወት። በዚህ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ደግሞ የሚፈጠሩ ክፍተቶችን አህመድ ፍጥነቱን ተጠቅሞ እንዲጠቀም ነበር ያደረግነው። ምክንያቱም አዳማዎች ግጥግጥ ብለው ስለነበር ሲከላከሉ የነበሩት እነሱን ለመዘርዘር ወደ መስመር ኳሱን ማውጣት ነበረብን። ከዚህ በተጨማሪ ግን ተጋጣሚን ማስከፈት ስለነበረብን አልፎ አልፎ ረጃጅም ኳሶችን ተጠቅመናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ