ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 7ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፩) – ክለብ ትኩረት

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የመጀመርያ ሳምንት ውሎዎች የታዘብናቸው ዓበይት ክለብ ነክ ጉዳዮችን በተከታዩ ፅሁፋችን ተመልክተናቸዋል።


👉 ፋሲል ከነማ ወደ ሰንጠረዡ አናት

ከአቅም በታች የሚጫወቱ ተጫዋቾች እንዲሁም በቡድኑ አሰልጣኝ እና ተጫዋቾች መካከል መከፋፈል አለ በሚል ከፍተኛ ስሞታ ሲቀርብባቸው የነበሩት የፋሲል ከተማ የቡድን አባላት በሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ሀዲያ ሆሳዕናን በሙጂብ ቃሲም ብቸኛ ግብ በማሸነፍ ፕሪምየር ሊጉን መምራት ጀምረዋል።

ከፍተኛ ጫና ውስጥ የነበረው ቡድኑ በእስካሁኑ የሊጉ የ7 ሳምንት ጉዞ ውስጥ በተሻለ ወጥ የሆነ እንቅስቃሴ በማድረግ ሳይሸነፍ ሊጉን እየመራ ይገኝ የነበረው ሀዲያ ሆሳዕናን በማሸነፍ ወደ ሰንጠረዡ አናት መመለስ የመሸርሸር ምልክቶችን ያሳየው የቡድኑ የራስ መተማመንን ከፍ በማድረግ የቡድኑን የውድድር ዘመን ጉዞ ሊቀይር የሚችል ወሳኝ ድልን ነው።

ዐፄዎቹ ካለፉት ሁለት ዓመታት ጋር ሲነፃፀር ደከም ባለ እንቅስቃሴ፣ እዚም እዚያም በሚሰሙ ሀሜታዎች እና ከተጠባቂነት የሚመነጭ ጫና ውስጥ ሆነው ጨዋታዎች እያደረጉ ቢሆንም ሊጉን ከመምራት ያገዳቸው የለም። ይህም ወደ ሀገሪቱ ትልቁ ሊግ ካደገ ገና አምስት ዓመት ያልሞላው ክለብ እየገነባ የሚገኘው ግዙፍ የአሸናፊነት ስነ-ልቡናን እዚህ ጋር ማንሳት አስፈላጊ ነው። በቀጣይ ተነሳሽነታቸውን ከጨመሩ እና የቀደመ አስፈሪ የሜዳ ላይ ጥንካሬያቸውን መመለስ ከቻሉም በዋንጫ ፉክክሩ እስከመጨረሻው መዝለቃቸው አይቀሬ ነው።


👉 ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ አሸናፊነት መመለስ እና እየተዳከመ የመጣው የኃላ ክፍሉ

በ7ኛ ሳምንት የቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በስድስተኛው የጨዋታ ሳምንት በተጠባቂው የሸገር ደርቢ ሽንፈትን አስተናግዶ የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስ በዚህኛው ሳምንት ጅማ አባጅፋርን ከመመራት ተነስቶ በማሸነፍ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል። የቅዱስ ጊዮርጊስ የተከላካይ መስመር ተዳክሞ በተስተዋለበት እንዲሁም ጌታነህ ከበደ ድንቅ ብቃቱን ባሳየበት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ 3-2 በሆነ ውጤት በሊጉ ግርጌ የሚገኘው ጅማ አባጅፋርን ሲረታ በጨዋታው ጌታነህ ከበደ ሐት-ትሪክ መስራት ችሏል።

ቡድኑ ገና በጊዜ ጎል አስተናግዶ ተጠቅጥቆ መከላከልን የመረጠው የጅማ አባጅፋር የኋላ መስመር ለማስከፈት በመጀመርያው አጋማሽ ቢቸገርም ከዕረፍት መልስ አሰልጣኙ ባደረጓቸው ለውጦች በመታገዝ በርካታ የጎል ዕድሎችን በመፍጠር ጨዋታውን አሸንፈው መውጣት ችለዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከድሉ ባሻገር ለወትሮው በሊጉ በጥንካሬው በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የኋላ መስመር በቀላሉ ግቦችን እያስተናገደ ይገኛል። ከዚህ ቀደም ባልተለመደ ሁኔታ በሊጉ ባደረጋቸው ስድስቱም ጨዋታዎች ላይ ጎሎች ተቆጥረውበታል። ቡድኑ ጅማ አባ ጅፋርን በረታበት ጨዋታ ላይ ደግሞ የኋላ መስመሩ ድክመት ጎልቶ የታየ ነበር። የመጀመርያው ከቅብብል ስህተት የተገኘ ሲሆን በሁለተኛው ጎል ደግሞ ቤካም አብደላ ኳሱን ከማግኘቱ በፊት እና በኋላ በሳጥን ውስጥ የነበረው ሰፊ ቦታ እና ጊዜ የኋላ ክፍሉን ድክመት በሚገባ የሚያሳይ ነበር።

ለዚሁ የኋላ መስመር ድክመት በርካታ ጉዳዮች በምክንያትነት ቢቀርቡም በዋነኝነት የተጫዋቾች የብቃት መውረድ ግን ከፍተኛ ድርሻን ይወስዳል ። ኳስን መስርቶ ለመውጣት በሚደረጉ ጥረቶች የሚፈፀሙ ግለሰባዊ የማቀበል ስህተቶች ፣ የተከላካይ መስመር ተሰላፊዎች በተለይ ከጉዳት የተመለሱት አስቻለው ታመነ እና ለዓለም ብርሃኑ ብቃት ወርዶ መታየት፣ የሙሉዓለም መስፍን እንደቀደመው ጊዜያት ለተከላካዮች በቂ ሽፋን ያለመስጠት እና ኳሶችን የማሰራጨት አቅሙ ተዳክሞ መስተዋል ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ምክንያቶች ናቸው። ታድያ መሰል ስህተቶችን በአፋጣኝ ማረም ካልተቻለ ቡድኑ በተፎካካሪነት ለመዝለቅ በሚያደርገው ጥረት ላይ በቀጣይ ፈተና መደቀናቸው አይቀሬ ይመስላል።


👉 ወላይታ ድቻ አስፈላጊዋን አንድ ነጥብ አግኝቷል

በ2ኛ ሳምንት ጨዋታ አዳማ ከተማን 2-0 ከረታበት ብቸኛው የውድድር ዘመኑ ድል በኃላ ለአራት የጨዋታ ሳምንታት ምንም ነጥብ ማስመዝገብ ተስኖት የነበረው ወላይታ ድቻ ከቀናት በፊት አሰልጣኝ ደለለኝ ደቻሳ እና ረዳቶቻቸውን ማሰናበቱ ይታወሳል። በዚህ ሳምንት በጊዜያዊ አሰልጣኛቸው ዘላለም ማቴዎስ እየተመሩ ሰበታ ከተማን በገጠሙበት እና በ90 ደቂቃ እንቅስቃሴ በንፅፅር የተሻሉ በነበሩበት ጨዋታ አንድ ነጥብ አስመዝግበው መውጣት ችለዋል።

ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ ኳሶች እና በፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ሰበታ ከተማን ሲፈትኑ የነበሩት ወላይታ ድቻዎች አንተነህ ጉግሳ ከማዕዘን የተሻማውንና የግቡ አግዳሚ የመለሰበት እንዲሁም ፀጋዬ አበራ በሁለት አጋጣሚች እና በረከት ወልዴ በሁለተኛው አጋማሽ ከርቀት በተደረጉ ሙከራዎች ለግብ መቅረብ ችለው ነበር።

አዲሱ የክለቡ አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው በሹመታቸው ማግስት በስታዲየም ተገኝተው በተከታተሉት በዚህ ጨዋታ ወላይታ ድቻዎች አሰልጣኝ እንደቀየረ ቡድን በእንቅስቃሴም ሆነ በውጤት ረገድ አዎንታዊ ግብረ መልስን ያሳዩበት ጨዋታ ሆኗል።


👉ገራገሩ ባህር ዳር ከተማ

በ7ኛ ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማን የገጠመው ባህርዳር ከተማ 2-1 በሆነ ውጤት ሽንፈት ለማስተናገድ ተገዷል።

በጨዋታው ባህር ዳሮች በተለይ በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች የተሻለ ጫና ፈጥረው በመጫወት የሀዋሳ ተጫዋቾችን ስህተት ተጠቅመው ተደጋጋሚ የግብ እድሎችን መፍጠር ቢችሉም ገና በማለዳ ያገኟቸውን አጋጣሚዎች ወደ ግብነት መቀየር አለመቻላቸው በስተመጨረሻ ዋጋ አስከፍሏቸዋል።

በክረምቱ የዝውውር መስኮት ከአዳማ ከተማ ባህር ዳር ከተማን የተቀላቀለው መናፍ ዐወል መምጣትን ተከትሎ የተሻለ የመረጋጋት ምልክቶችን እያሳየ የነበረው የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት አሁንም ቢሆን እንደ ቡድን በመከላከል ረገድ ብዙ ሥራዎች እንዲሚቀሩት ያመላከተ የጨዋታ ዕለትን አሳልፏል።

በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ መሪነት ብዙ ተስፋ የተጣለበት የባህር ዳር ከተማ ስብስብ በዚሁ የማጥቃት ስልነት መጓደል እና እንደ ቡድን በመከላከል ረገድ የሚስተዋልባቸው ክፍተት ቡድኑ በሰንጠረዡ አናት ከጠንካራዎቹ ቡድኖች ጋር ለመፎካከር በሚያደርገው ጥረት ተግዳሮት ሊሆንበት እንደሚችል ይገመታል።

ሌላው ተያይዞ የሚነሳው ባህር ዳር እና ወጥነት ከዓምና ጀምሮ ሊገጥም ያልቻለ ጉዳይ መሆኑ ነው። ቡድኑ ዓምና በሜዳው እያሸነፈ ከሜዳው ውጪ የሚሸነፍ ቡድን እንደነበር የሚታወስ ሲሆን ዘንድሮ በተመረጡ ቦታዎች ጨዋታዎች መካሄዳቸው ዐዎንታዊ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተገምቶ ነበር። ሆኖም አንዱን ጨዋታ አሸንፎ በቀጣይ ነጥብ መጣል፤ በአንዱ ሳምንት እንደ ቡድንም በተጫዋቾች የተናጠል እንቅስቃሴም አጀብ አሰኝቶ በቀጣዩ መርሐ ግብር ግራ የተጋባ ቡድን መመልከት አሁንም የባህር ዳር ከነማ መለያ ሆኗል።


👉የሀዲያ ሆሳዕና ያለመሸነፍ ጉዞ መገታት

በተሰረዘው የውድድር ዘመን ላለመውረድ ሲንገዳገድ የነበረው ሀዲያ ሆሳዕና ዘንድሮ ደግሞ በሊጉ እስከዚህ የጨዋታ ሳምንት ድረስ ምንም ሽንፈት ሳያስተናግድ ሊጉን ከአናት ሆኖ ሲመራ ቆይቷል። ሆኖሞ በዚህ ሳምንት በተከታዩ ፋሲል ከነማ ሽንፈትን በማስተናገድ ያለመሸነፍ ጉዞው ሊገታ ችሏል።

በምግብ መመረዝ የተነሳ ያለ ወሳኝ የፊት መስመር አጥቂዎቻቸው ቢስማርክ አፒያ እና ሳሊፉ ፎፋና ጨዋታቸውን ያደረጉት ነብሮቹ ሁለቱ ተጫዋቾች አለመኖራቸው በግልፅ አጉዱላቸው ተስተውሏል። በቀደሙት ጨዋታዎች በፈጣኖቹ አጥቂዎቹ እንቅስቃሴ አስፈሪ የነበረው የሀዲያ የፊት መስመር በፋሲሉ ጨዋታ እጅግ ተዳክሞ ተስተውሏል።

የሁለቱ ተጫዋቾች መጉደል በአጠቃላይ የቡድኑ መዋቅር እንዲፋለስ ባስገደደበት በዚሁ ጨዋታ በተለይ አሰልጣኝ አሸናፊ በመጀመሪያው አጋማሽ ተደጋጋሚ የተጫዋቾች የሚና ለውጥ እና የቅርፅ ለውጥ ለማድረግ ያስገደዳቸው ሲሆን በ80ኛው ደቂቃ በራሳቸው የሜዳ አጋማሽ ከአልሀሰን ካሉሻ እግር በተነጠቀች ኳስ በተቆጠረችባቸው ግብ ለውድድር ዘመኑ የመጀመሪያ ሽንፈት ተዳርገዋል።

ሆሳዕና ምንም እንኳ እንደ ቡድንም ሆነ በተናጠል የተጫዋቾች ጥራቱ ከፍ ያለ ስለመሆኑ በመጀመርያዎቹ ጨዋታዎች ላይ በሚገባ ማሳየት ቢችልም ከተጋጣሚዎቹ የገጠመው ፈተና በቀጣይ ጨዋታዎች ከሚገጥመው ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ እንደነበር መናገር ይቻላል። በቀጣይ የሚገጥሙት ቡድኖች ከወገብ በላይ ያሉ መሆናቸው እና ስኬታማ ጅማሮው የፈጠረው የትኩረት ማዕከልነት ለቡድኑ ከባድ ፈተና ይዞበት ሊመጣ ይችላል።


👉እየተቸገረ የሚገኘው ድሬዳዋ ከተማ

በመጀመሪያዎቹ ሦስት ሳምንታት ደካማ አጀማመር አድርገው የነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች በተከታታይ ባስመዘገቡት ውጤት የተነቃቁ ቢመስሉም ባለፉት የመጨረሻ ሁለት ሳምንታት እየተቸገሩ መጥተዋል።

በፈጣን አጥቂዎቻቸው ፍጥነት ላይ የተመሰረተ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴን ምርጫቸው ያደረጉት ብርቱካናማዎቹ ከአጥቂ መስመር ተሰላፊዎች በፓስፖርት ጉዳይ አለመኖር እና ያሉትም ላይ ሰሞነኛ የአቋም መውረድ ጋር በተያያዘ የተሻሉ በነበሩባቸው የጨዋታ ሳምንታት ያደርጉት የነበረውን እንቅስቃሴ ለማድረግ እየተቸገሩ ይገኛል።

ለማጥቃት አንድ እና አንድ መንገድ ብቻ ያለው ቡድኑ አማራጭ የጥቃት መሰንዘርያ መንገዶችን ብሎም ለመተግበር የሚፈልገውን የመልሶ ማጥቃት መሰንዘር የሚያስችሉ ስልቶችን መዘየድ ካልቻለ ከሰበሰበው ነጥብ አንፃር እኖዳለፉት ዓመታት ሁሉ በቀጣይ ፈታኝ ጉዞ ሊጠብቀው እንደሚችል ምልክቶች እየታዩ ይገኛል።


👉በኳስ ማንሸራሸር የተለከፈው ሰበታ ከተማ

በሀገራችን በንፅፅር በቴክኒኩ ረገድ ከፍ ያለ ቦታ የሚሰጣቸው አማካዮችን ያሰባሰው ሰበታ ከተማ እንደ ቀደሙት ሳምንታት ሁሉ በዚህኛው ሳምንት ከወላይታ ድቻ ጋር አቻ በተለያየበት ጨዋታ በአመዛኙ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ የተሻለ ቢሆንም የግብ እድሎችን መፍጠር ቀርቶ ወደ ተጋጣሚ የማጥቃት ወረዳ ለመድረስ በእጅጉ ሲቸገር ተስተውሏል።

ቡድኑ እስካሁን ባደረጋቸው ጨዋታዎች በተመሳሳይ ኳሶችን በመሀል ሜዳው አካባቢ ወደ ጎን እና ወደ ኃላ ሲንሸራሸሩ እንጂ አደጋ ወደሚፈጥሩበት ቀጠና አድገው እድሎችን ሲፈጠር አይስተዋልም። በዚህም ረገድ ቡድኑ የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎችን የተቆጣጠረ ቢመስልም ከውጤታማነት አንፃር ግን እየተቸገረ ይገኛል።

በእርግጥ ከድቻው ጨዋታ በኋላ አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ የአማካይ ተጫዋቾችን አብዝተው ለመጠቀም የፈለጉት ቡድኑ ከጨዋታው በፊት በቂ ልምምድ ባለመስራቱ አላስፈላጊ ሪስክ ላለመውሰድ እንደሆነ መናገራቸው እዚህ ላይ ከግምት የሚገባ ቢሆንም ከዚህ ጨዋታ ቀደም ብሎም በተለያዩ ጨዋታዎች ላይ በርካታ አማካዮችን የመጠቀም ዝንባሌ አሳይተዋል። ይህም ቡድኑ በፊት መስመር በቁጥር እንዲያንስ እና ስልነት እንዲጎድለው ያደረገው ይመስላል። በተጨማሪም በአማካይ ተጫዋቾች የአጨዋወት ባህርይ መመሳሰል ምክንያት አንድ ቦታ በመከማቸት በተጋጣሚ ቁጥጥር ስር በቀላሉ እንዲውሉ እያደረጋቸው ይገኛል።


👉 የተነቃቃው ሲዳማ ቡና

በተደጋጋሚ በዐበይት ጉዳያችን ላይ ያነሳነው የዘንድሮው የሲዳማ ቡና ቀዝቃዛ አጀማመር በዚህ ሳምንት ጨዋታ የተሻሻለ ይመስላል። የወትሮው አስደናቂ እና ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ጠፍቶ እጅግ ደካማ እና ቅርፅ አልባ የነበረው ቡድን ድሬዳዋ ከተማን 3-1 በረታበት ጨዋታ ላይ የመሻሻልና መነቃቃት ምልክቶችን አሳይቷል።

የአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ቡድን ኳስን የመቆጣጠር ፍላጎት የሚያሳይ ቡድን ቢሆንም ከተጫዋቾቹ ባህርይ እና ከሚያስቆጥሯቸው ጎሎች መነሻነት ፈጣን የመልሶ ማጥቃት ውጤታማው ቡድኑ አጨዋወት እንደሆነ ታይቷል። በዚህ ሳምንት ጨዋታ ላይም ከዚህ ቀደም የቡድኑ መለያ የነበረው ፈጣን ሽግግር በተደጋጋሚ የታየ ሲሆን የፍሬው ጌታሁን የዕለቱ ድንቅ ብቃት ድሬዎችን ታደጋቸው እንጂ እንደፈጠሯቸው የጎል እድሎች በርካታ ጎሎችን ማስቆጠር በቻሉ ነበር።

የማማዱ ሲዲቤ ከአስደናቂ ብቃት ጋር መመለስ፣ የሀብታሙ ገዛኸኝ አቋም መሻሻል እና በፓስፖርት ጉዳዮች ሳያሰልፋቸው የቀሩ ተጫዋቾችን ማግኘቱ ለቡድኑ መልካም ዜና ሲሆን እንደ ጫላ ተሺታ ያሉ በጉዳት ከሜዳ የራቁ ተጫዋቾች ሲመለሱ ሲዳማ ቡና ወደቀደመ ተፎካካሪነቱ ሊመለስ እንደሚችል ፍንጭ የሚሰጥ ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ