“ሁለተኛ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ሊሰጣቸው ሲል በራሳቸው ጊዜ ጥለው ሄደዋል” አቶ ሱልጣን ዛኪር
“ደሞዝ ሳይከፈለኝ ማሰልጠን አልችልም” ጳውሎስ ጌታቸው
በ2012 የውድድር ዘመን አባ ጅፋርን የተቀላቀሉት አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ውድድሩ በኮሮና ቫይረስ እስቀተቋረጠበት ጊዜ ድረስ ቡድኑ በሜዳም ከሜዳም ውጭ የተለያዩ ችግሮች እያስተናገደ መዝለቅ ችለው ነበር። ዓምና የነበረው ተመሳሳይ ችግር ዘንድሮም ተከትሎ የመጣው ጅማ አባ ጅፋር በተመሳሳይ የውጤት ቀውስ ውስጥ ይገኛል። ከጨዋታ በፊት እና በኃላ በሚሰጡት አስተያየት መነጋገሪያ የሆኑት አሰልጣኝ ጳውሎስ ትናንት በድንገት ከሰዓት በነበረው በረራ ወደ አዲስ አበባ መግባታቸው ታውቋል። ታዲያ የጅማ አባጅፋር እና የአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው እህል ውሀ ያበቃ ይሆን ስንል በክለቡ በኩል አቶ ሱልጣን የክለቡን ሥራ አስኪያጅ እና አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸውን አናግረን ተከታዩን ምላሽ ሰጥተውናል።
አሰልጣኝ ጳውሎስ
” የፊርማ ገንዘብ አልተከፈለኝም። በተጨማሪ የሰባት ወር ደሞዝ አልተከፈለኝም። ከዚህ በኋላ በምን ሁኔታ ነው ልሰራ የምችለው። ደሞዝ ሳይከፈለኝ ማሰልጠን አልችለም። ከዚህ በኃላም በሚኖሩ ጨዋታዎች ቡድኑን እንደማልመራ ለሚመለከታቸው ለከንቲባ ፅህፈት ቤት፣ ሊግ ካምፓኒው እና ለሌሎችም አካላት ደብዳቤ አስገብቻለሁ።”
አቶ ሱልጣን (የክለቡ ሥራ አስኪያጅ)
ሰበብ እየቆጠሩ ኃላፊነታቸውን ከመወጣት ይልቅ ቸልተኝነት እያሳዩ ነው ስንል የመጀመርያ ማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ሰጥተን ነበር። ሆኖም ትኩረት ሰጥተው የቡድኑን ውጤት ከማሻሻል ይልቅ ምንም ማሻሻል ባለመቻላቸው ሁለተኛ ማስጠንቀቂያ ደብዳቤው ሊፃፍባቸው እንደሆነ ሲያውቁ በራሳቸው ጊዜ ጥለው ሄደዋል።”
ጅማ አባ ጅፋር ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ከነገ በስቲያ የስምንተኛ ሳምንት ጨዋታውን የሚያደርግ ሲሆን በዚህ ጉዳይ ዙርያ የሚኖሩ አዳዲስ መረጃዎችን ተከታትለን ወደ እናንተ የምናደርስ ይሆናል።
© ሶከር ኢትዮጵያ