በኢትዮጵያውያን ግብጠባቂዎች ዕምነት በተነፈገበት ያለፉት ዓመታት ተጠባባቂ ወንበር ላይ ተቀምጦ የቆየው ዳንኤል ተሾመ በትናንትናው ጨዋታ አስደናቂ ብቃቱን አስመልክቶ የስፖርት ቤተሰቡ መነጋገርያ ሆኗል።
በወሊሶ የጀመረው የግብጠባቂነት ጅማሬው ለትምህርት ባቀናበት ሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ቀጥሎ በማስከተል አዲስ አበባ ከተማን በመቀላቀል ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊግ ሲያድግ የራሱን አስተዋፆኦ አድርጓል። በተጫወተባቸው ጊዜያት ክስተት በመሆን የማይታመኑ እንቅስቃሴዎች አድርጎ ይወጣል። ሆኖም በድጋሚ ወደ ተጠባባቂ ወንበር በመውረድ ዓመታትን ገፍቷል። አአ ከተማን ለቆ ወደ አዳማ ከተማ በማምራት ያለፉትን ሦስት ዓመታት ቆይታ ያደረገው ዳንኤል ቡድኑ የውጭ ግብጠባቂዎችን ይጠቀም የነበረ በመሆኑ አቅሙን የማሳየት ዕድል ሳያገኝ ቆይቷል። በተለይ በ2011 አዳማ ከተማ የቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ ግብጠባቂ ሮበርት ኦዶንካራ እና አሁን ጅማ አባ ጅፋር እየተጫወተ የሚገኘውን ጄኮ ፔንዜን እየቀያየረ ይጠቀም የነበረ መሆኑ ለዳንኤል የበለጠ ሰብሮ ለመውጣት ፈተናውን ከባድ አድርጎበት ቆይቷል።
አዳማ ዘንድሮ በፋይናንስ እጥረት ግብጠባቂውን ጨምሮ የውጪ ተጫዋቾቹን አሰናብቶ ለወጣቶች እና በሌሎች ክለቦችመጫወት ዕድል ላላገኙ ተጫዋቾች ዕድል ሲሰጥ ለዳንኤልም ፀሐይ ወጥቶለታል። በአራተኛው ሳምንት ቡድኑ ከሲዳማ ቡና ጋር ሲጫወት ጥሩ ብቃት አሳይቶ ጎል ሳይቆጠርበት የወጣ ሲሆን ትናንት ደግሞ ቡድኑ ምንም እንኳን በጠባብ ጎል ተሸንፎ ቢወጣም በርከት ያሉ ጎሎች እንዳይቆጠሩ ያዳነበት መንገድ ተጠባባቂ ወንበር ለረጅም ጊዜ መቀመጥ ለታከታቸው ኢትዮጵያውያን ግብጠባቂዎች ትልቅ ተስፋ ያለመቁረጥ ተምስሌት አድርጎታል።
ዳንኤል ትናንት ደምቆ ከዋለበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ የተወሰኑ ጥያቄዎችን አንሰተንለት ተከታዮን ሀሳብ አጋርቶናል።
” የዛሬው ጨዋታ ጥሩ ነበር። በተቻለን መጠን ነጥብ ይዘን መውጣት አስበን ነበር። ይህ አልተሳካም። እኔም በግሌ የምችለውን ለማድረግ ሞክሬያለው። ከሦስት ዓመት በላይ እንደምታውቁት ተጠባባቂ ወንበር ላይ ቆጭ ብዬ ቆይቻለው። ይህም የሆነው የውጭ ሀገር ግብጠባቂዎች በመኖራቸው ነው። ዘንድሮ መጀመርያ አካባቢ አንድ ሁለት ጨዋታ መጫወት ጀምሬ ትንሽ ህመም አጋጥሞኝ ከጨዋታ ዕርቄ ዛሬ ለመጫወት ችያለው። ሁሌም ቢሆን ሥራዬን በትጋት ተስፋ ባለመቁረጥ እሠራ ነበር። ያ ይመስለኛል ዛሬ ጥሩ እንቅስቃሴ እንዳሳይ የረዳኝ። አሁንም ለኢትዮጵያውያን ግብጠባቂዎች ማለት የምፈልገው ብዙ ጊዜ ተስፋ አለመቁረጥ ነው። በአንድ ወቅት በሁለት የውጭ ሀገር ግብጠባቂዎች መሐል ሆኜም ተስፋ አልቆረጥኩም። ሁሌም ያለማቋረጥ ጠንክሬ እሰራ የነበረ በመሆኑ ዛሬ ቋሚ ተሰላፊ ወደ መሆን መጥቻለው። ስለዚህ በትዕግስት ጊዜውን መጠበቅ አለባቸው።”
ከትናንትናው ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ አሰልጣኝ አስቻለው ኃይለሚካኤል ስለ ዳንኤል ተሾመ ይህን ምስክርነት ሰጥተው ነበር።
“ዳንኤል ከነ ሥነ-ስርዓቱ ታጋሽ የሆነ ግብ ጠባቂ ነው። በፊት በነበሩት የአሠልጣኝ ቡድን አባላት ምርጫ ውስጥ በነበሩት ሁለት የውጪ ዜጋ ግብ ጠባቂዎች ተሸፍኖ የነበረ ነው። ከደፈርን በሀገራችን ጥሩ ጥሩ ግብ ጠባቂዎች እንዳሉ ማሳያ ነው። በነበሩት ዜጋ ግብ ጠባቂዎች ተሸፍኖ የነበረ ቢሆንም አሁን ያገኘውን እድል ተጠቅሞ አቅሙን እያሳየ ነው። ዛሬም ጥሩ ተጫውቷል።”
© ሶከር ኢትዮጵያ