የሰባተኛ ሳምንት ዓበይት ትኩረቶቻችን ማጠቃለያ በሆነው በዚት ክፍል ሌሎች መነሳት የሚገባቸው ጉዳዮችን ተመልክተናል።
👉 ከኃላ ተነስቶ ማሸነፍ
በዚህ የጨዋታ ሳምንት በመሸናነፍ ከተጠናቀቁት ጨዋታዎች መካከል ሦስቱ አስቀድመው ግብ ያስተናገዱ ክለቦች ከመመራት ተነስተው ያሸነፉበት ነበር። በዚህም ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ሀዋሳ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ተጋጣሚዎቻቸውን ማሸነፍ ችለዋል።
ጨዋታዎች በሜዳ ላይ ከሚደረጉ ፉክክሮች ባልተናነሰ ከሜዳ ውጭ ባሉ ሁነቶች እንደሚወሰን በሚነገርበት ሊጋችን በተለምዶ አስቀድመው ግብ ያስቆጠሩ ባለሜዳ ቡድኖች “በየትኛውም መንገድ” ጨዋታዎችን አሸንፈው መውጣታቸው የተለመደ ነው። በዚህም ሒደት የባለሜዳው ቡድን ደጋፊዎች ተፅዕኖ ቀላል የሚባል አልነበረም።
የዘንድሮ የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ተከትሎ ውድድሩ ከቀደመው የደርሶ መልስ አካሄድ ወጥቶ በተመረጡ ከተማዎች እየተካሄደ መገኘቱ ለቡድኖች ከወትሮው በተለየ እኩል የሆነ የደጋፊዎች ተጠቃሚነት እንዲያገኙ ማስቻሉ ለሊጉ አዲስ ገፅታ ያላበሰው ይመስላል። ይህም ጨዋታዎች ከሜዳ ውጭ ባሉ ተፅዕኖ ከመወሰን ይልቅ በሜዳ ላይ በሚኖረው የ90 ደቂቃ እንቅስቃሴ የተሻለ መንቀሳቀስ በቻለው ቡድን ጥረት መወሰኑ እየበረከተ ለመጣው ቡድኖች ከኋላ ተነስተው የማሸነፍ ሂደት እንደ አይነተኛ ምክንያት መቅረብ የሚችል ጉዳይ ነው።
👉የጅማ ዝግጅት ሲፈተሽ
ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የስድስት ሳምንታት የአዲስ አበባ ቆይታውን አጠናቆ ለአንድ ወር ያክል ደግሞ በተረኛው የጅማ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም መካሄዱን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ጅማሮውን አድርጓል።
ሊጉ ከሚደረግባቸው ስታዲየሞች በተለየ መልኩ በጅማ ዩኒቨርስቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኘው እና ውድድሩ እየተካሄደ የሚገኝበት የጅማ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም በሀገራችን ከሚገኙ ጥሩ ከሚባሉ የስፖርት መሰረተ ልማቶች አንዱ ነው።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በቀዳሚነት ከቆሙለት የመማር ማስተማር እንዲሁም ምርምር እና ስርፀት በተጓዳኝ መሰል ከፍተኛ ኢንቨስትመንት በሚጠይቁ የውድድር ስፖርት መሰረተ ልማቶችን የመገንባት ተነሳሽነት ማሰየታቸውና በተሻለ ጥራት ማስገንባት መቻላቸው የሚደነቅ ነው።
እንደ ሌሎች አዲስ እየተገነቡ እንደሚገኙት የሀገራችን ስታዲየሞች መሰረታዊው የመዋቅር ሥራው የተጠናቀቀው ስታዲየሙ የማጠናቀቂያ ሥራዎች ከፊቱ ይጠብቁታል።
ከሌሎች የሀገራችን የውድድር ሜዳዎች በተለየ በጅማ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም የህክምና አርዳታ ለመስጠት የተቋቋመው የህክምና ቡድን ፍፁም የተለየ ነው። ለመጀመሪያ እርዳታ የሚያገለግልና በአስፈላጊ ቁሶች የተደረጃው ዘመናዊ ተሽከርካሪን ጨምሮ የህክምና እርዳታ በሚሰጡ ስፔሻሊስት ዶክተሮች ድረስ የተደራጀው የህክምና ቡድን ለሌሎች የውድድር ሜዳዎች በትልቁ ትምህርት የሚሰጥ ነው። ከሀገሪቱ ስመጥር ህክምና ትምኅርት ተቋማት አንዱ የሆነው ጅማ ዩኒቨርሲቲ ከዚህ ስኬት ጀርባ አይነተኛ ሚና እንደሚኖረው አያጠራጥርም።
ለአንድ የእግርኳስ ስታዲየም መሰረታዊው የሆነው የመጫወቻ ሜዳ ጉዳይ ግን ጥሩ የሚባል አይደለም። በተወሰነ መልኩ ጭቃማ እንዲሁም አለፍ አለፍ ብሎ ደግሞ ከፍ ከፍ ያሉ ሳሮች የሚስተዋሉበት የመጫወቻ ሜዳው በተለይ ኳስን በመሬት ለማንሸራሸር እጅግ ፈታኝ መሆኑ ተስተውሏል።
በተያያዘም በስታዲየሙ በተከናወነው እና ጅማ አባጅፋርን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ባገናኘው የመጀመሪያ ጨዋታ ከመጀመሩ 30 ደቂቃዎች እስኪቀሩ ድረስ የግቡ ቋሚዎች ያለመረብ ለመቆየት የተገደዱበት እና በቀሪዎቹ ደቂቃዎች በጥድፊያ መረቡን ለመስቀል የተደረገው ሂደት ሌላው ከቅድመ ዝግጅት አንፃር የተመለከትነው ክፍተት ነው።
በተመሳሳይ ከ50ሺህ በላይ ሰዎችን ለማስተናገድ የተገነባው ስታዲየም ፕሪምየር ሊጉን ለማስተናገድ በነበረው የቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ወቅት ለክብር እንግዶችም ሆነ ቁጥራቸው አነስተኛ ለሆኑት ደጋፊዎች የሚሆን ምንም አይነት መፀዳጃ ቤት አለመኖሩ አግራሞትን የሚፈጥር ነው። በስታዲየሙ በተጋጣሚ ቡድኖች መልበሻ ቤት ከሚገኘው መፀዳጃ ቤት ውጭ ለሌሎች አካላት አገልግሎት እንዲሰጥ ተብሎ የተዘጋጀ መፀዳጃ ቤት አለመኖሩ አወዳዳሪው አካል ከቀጣይ የጨዋታ ቀናት በፊት አፋጣኝ እልባት ሊሰጠው ይገባል።
የኮቪድ 19 ፕሮቶኮልን በማክበር ረገድ አሁንም በጅማው ውድድር መሻሻሎችን መመልከት አልቻልንም። ስታዲየሙ መቀመጫ ወንበር የሌለውን መሆኑን ተከትሎ በስታዲየሙ ጨዋታውን ለመከታተል የሚገኙ አካላት እጅግ ተጠጋግተው ሲቀመጡ ተስተውሏል። ይህም ጉዳይ አሁንም ትኩረት ተሰጥቶበት በጨዋታዎች ወቅት ሊሰራበት ይገባል።
👉የሊጉ ትልቅ የጫማ ቁጥር…?
ከዚህ ቀደም በመከላከያ እንዲሁም በአዳማ ከተማ ሲጫወት የምናውቀው ቴዎድሮስ በቀለ ዘንድሮ በሀዲያ ሆሳዕና እየተጫወተ ይገኛል። በቁመቱ ገዘፍ ያለው እና አሁን ላይ በተወሰነ መልኩ ክብደቱ ቀነሰ እንጂ ጠቅጠቅ ያለ አካላዊ ቁመና ያለው ተጫዋቹ በመሐል ተከላካይነት እንዲሁም በግራ መስመር ተከላካይነት ሚናን ሲወጣ ይስተዋላል በተለይም በቁመት ረዘም ያሉ ተጫዋቾች እምብዛም በማይደፈረው እና ከፍተኛ ፍጥነት፣ ትጋትና አካላዊ ብርታት በሚጠይቀው የመስመር ተከላካይ ስፍራ ግዙፉን ቴዎድሮስ በቀለ በብቃት ሲከወን መመልከት አግራሞትን የሚያጭር ነው።
ታድያ ተጫዋቹ ሌላኛም አስገራሚ መለያ አለው። ይህም በአብዛኛው የእግርኳስ ተጫዋቾች በተለምዶ ከ42-43 ቁጥር ያልዘለለ የመጫወቻ ጫማን ሲጫሙ በተቃራኒው ቴዎድሮስ በቀለ ግን 46 ቁጥር ጫማን መጫማቱ አስገራሚ ያደርገዋል።
👉የሊጉ ብቸኛዋ ሴት የጨዋታ ኮሚሽነር
ሲዳማ ቡና ድሬዳዋ ከተማን ከመመራት ተነስቶ በረታበት ጨዋታ ሣራ ሰዒድ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ለሁለተኛ ጊዜ በኮሚሽነርነት የታዘበችው ጨዋታ ነበር።
አነስተኛ የሴቶች ተሳትፎ በሚስተዋልበት የሀገራችን የእግርኳስ እንቅስቃሴ ኢንተርናሽናል አልቢትር ሊዲያ ታፈሰ በዳኝነት እንዲሁም የቀድሞዋ ኢንተርናሽናል ዳኛ ሣራ ሰዒድ በኮሚሽነርነት ሚና በሀገሪቱ ትልቁ የክለቦች ውድድር ላይ በኃላፊነት ሲሰሩ መመልከት ብሎም ኃላፊነታቸውን በብቃት መወጣት ሌሎች ሴት ባለሙያዎች ላይ የሚኖረው በጎ ተፅዕኖ ቀላል የሚባል አይደለምና ሁለቱ እንስቶች መበረታታት ይኖርባቸዋል።
👉ምስጋና የሚገባው አክሲዮን ማኅበሩ
ከተመሰረተ ሁለተኛ ዓመቱ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማህበር በሀገራችን እግርኳስ ያልተለመዱ አዳዲስ ነገሮችን በማስተዋወቁ ቀጥሏል።
የዓለምአቀፍ መርሃግብሮችን ያላማከለ፣ ያለ በቂ ምክንያት የጨዋታ ቀናት ለውጦች፣ መርሃግብሮች አስቀድመው አለመታወቅ እና ሌሎች ያልዘረዘርናቸው ችግሮች ከሊጋችን የመርሃግብር አወጣጥ ጋር ተቆራኝተው የሚነገሩ ጉዳዮች ነበሩ። ነገርግን ካለፈው ዓመት አንስቶ ምስጋና ለአክሲዮን ማህበሩ ይሁንና መሻሻሎችን እየተመለከትን እንገኛለን።
ዘንድሮ ደግሞ ገና የመጀመሪያው ዙር ሊጠናቀቅ አራት የጨዋታ ሳምንታት እየቀሩት የመጀመሪያው ዙር የሚጠናቀቅበት ወቅት፣ በመሐል የሚኖረው እረፍት እና ሁለተኛው ዙር የሚጀመርበት ቀን ከወዲሁ ይፋ መደረጉ ሌላኛው አዲሱ በጎ ጅምር ነው። በተጨማሪም የቀን መሸጋሸጎች በድንገት ከመግለፅ ይልቅ ሳምንታት ሲቀሩ መታወቁ ቅሬታን የሚቀንስ በጎ ጅምር ነው።
© ሶከር ኢትዮጵያ