ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ 7ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፫) – አሰልጣኞች ትኩረት

በሰባተኛ ሳምንት የተመለከትናቸው አሰልጣኝ ነክ ጉዳዮች እና ዐበይት አስተያየቶች እነሆ!

👉የሙሉጌታ ምህረት እና ማሔር ዳቪድስ ውጤታማ ቅያሬዎች

ሀዋሳ ከተማ ከመመራት ተነስቶ ባህርዳር ከተማን በረታበት ጨዋታ አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት በመጀመሪያው አጋማሽ በ3-5-2 በሆነ አደራደር በተለይ በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ከፍ ባለ ትጋት ተጋጣሚን ጫና ውስጥ በመክተት ለመጫወት ጥረት የሚያደርገው ባህርዳር ከተማን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር በቁጥር በርከት ብሎ ከመከላከል የተሻለ አማራጮችን በሚሰጣቸው የተጫዋቾች አደራደር የባህርዳርን ስጋት ለመቀንስ ጥረት አድርገዋል። ምንም እንኳ 1-1 በሆነ ውጤት ሁለቱ ቡድኖች ወደ እረፍት ቢያመሩም ከሞላ ጎደል እቅዱ ውጤታማ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው በተሻለ ሜዳ ላይ ራሳቸውን ለመግለፅ የፈለጉ የሚመስሉት ሀዋሳ ከተማዎች ከሦስቱ የመሀል ተከላካዮች አንዱ የነበረውን ወንድማገኝ ማዕረግን አስወጥተው የመስመር አማካዩ ኤፍሬም አሻሞን በማስገባት ቅርፃቸውን ወደ 4-3-3 በመቀየር የተሻለ የማጥቃት ፍላጎትን በማሳየት ተደጋጋሚ እድሎችን ለመፍጠር ጥረዋል። ይህም ቅያሬያቸው ፍሬ አፍርቶ በ59ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ኤፍሬም አሻም ባስቆጠራት አስደናቂ ግብ ከጨዋታው ወሳኝ ሦስት ነጥብ ይዘው ለመውጣት በቅተዋል።

በተመሳሳይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጅማ አባጅፋርን 3-2 በረታበት ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ አሰልጣኝ ማሒር ዳቪድስ ያደረጋቸው ቅያሬዎች ቁልፍ ነበሩ። በመጀመሪያው አጋማሽ ከዚህ በፊት በሚቀርቡበት 4-2-3-1 / 4-3-3 አደራደር የቀረቡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በዚሁ ቅርፅ በመጀመርያው አጋማሽ ኳስን ከመቆጣጠር ውጪ ይህ ነው የሚባል እድል ለመፍጠር ተቸግረው ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ በሁለት መስመሮች ይከላከል የነበረውን የጅማን የመከላከል አደረጃጀት ለማስከፈት እንዲረዳቸው አሰልጣኝ ማሒር በሁለተኛው አጋማሽ ጋዲሳ መብራቴ እና ሄኖክ አዱኛን ወደ መስመር ተመላላሽነት በመቀየር እንዲሁም የአጥቂ አማካዩ ሮቢን ንጋላንዴን አስወጥተው አጥቂው ሳላዲን ሰዒድን በማስገባት በ3-4-3 ወደ ጨዋታው የገቡ ሲሆን በዚህም በሜዳው ቁመትም ሆነ ስፋት የጅማን የመከላከል አደረጃጀት ለመስበር የተሻለ አማራጭ ፈጥሮላቸው ተደጋጋሚ ሙከራ በማድረግ ጨዋታውን 3-2 ለማሸነፍ በቅተዋል።


👉የመጀመሪያ ተመራጮቹን ለመለየት የተቸገረው አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ

አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ከረጅም ዓመታት ቆይታ በኃላ ዳግም በክለብ ደረጃ ሰበታ ከተማን በአንድ ዓመት ውል ከተረከቡ ወዲህ ከአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የተረከቡት ስብስብ ላይ ማሻሻያዎችን በማድረግ በአዲሱ የውድድር ዘመን 7ኛ ሳምንት ድረስ ተጉዘዋል።

ታድያ በሰባት ሳምንት የሊጉ ቆይታ ስድስት ጨዋታዎችን ያደረጉት ሰበታ ከተማዎች ከጨዋታ ጨዋታ የሚቀያየር የመጀመርያ አስራ አንድን የቡድን ስብስብን እያስመለከቱን ይገኛል። በሊጉ የእስካሁኑ ጉዞ በሰበታ ደረጃ በመጀመሪያ 11 ስብስብ ውስጥ ብዙ ተጫዋቾችን የተጠቀመን ቡድን ፈልጎ ማግኘት አዳጋች ነው።

እርግጥ ነው ውድድሩ ገና የመጀመሪያው ዙር አኩሌታ ላይ ቢገኝም አሰልጣኙ በሁሉም የሜዳ ክፍሎች የተለያዩ ጥምረቶችን ለመጠቀም ሲሞክሩ ተስተውሏል። ለማሳያነትም በተለይ በመሐል ተከላካይ ስፍራ ቢያድግልኝ ኤልያስን ከመሳይ ጳውሎስ ፣ አንተነህ ተስፋዬን ከቢያድግልኝ ኤልያስ ፣ አንተነህ ተስፋዬን ከአዲሱ ተስፋዬ ፣ አንተነህ ተስፋዬን ከመሳይ ጳውሎስ… መሰል ጥምረቶችን የተመለከትን ሲሆን በመስመር ተከላካይ እንዲሁም በተከላካይ አማካይ ስፍራ ላይ እንዲሁ ከጨዋታ ጨዋታ የተለያዩ ተጫዋቾችን ሲጠቀሙ ተስተውሏል። ይህ ነው የሚባል አስገዳጅ የተጫዋቾች ጉዳት ባይኖርም በተከላካይ ስፍራ ላይ የሚገኙ ተጫዋቾች የሚሰሩት ስህተት ለተደጋጋሚ ለውጦች ምክንያት ሊሆናቸው ይችላል። በተጨማሪም የውድድሩ መርሐ ግብር ከቀደሙት ዓመታት በተለየ ጠቅጠቅ ያለ በመሆኑ ቡድኖች ተጫዋቾቻቸውን በማፈራረቅ መጠቀማቸው የሚጠበቅ ቢሆንም በዚህ ደረጃ ግን በብዛት የሚደረጉ ለውጦች በሽግግር ውስጥ የሚገኘው ቡድኑ ተጫዋቾቹ ከጨዋታ ጨዋታ ሊያዳብሩት የሚገባ የእርስ በእርስ ተግባቦት ላይ ጫና በማሳደር የቡድኑን ውህደት ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩ እሙን ነው።


👉የዘላለም ሽፈራው ድቻ ምን ሊመስል እንዲችል ፍንጭ የሰጠው ጨዋታ

በ2006 የውድድር ዘመን ወደ ሊጉ ካደገ አንስቶ በተለይ በአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ እየተመራ በጥብቅ መከላከል እንዲሁም በቀጥተኛ አጨዋወት በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክፍል መድረስ መለያው የነበረው ቡድኑ አሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀ ቀጥሎም ገብረክርስቶስ ቢራራ እና በቅርቡ የተሰናበቱት አሰልጣኝ ደለለኝ ደቻሳ መለያው ከነበረው ቀጥተኝነት በማውጣት በኳስ ቁጥጥር ላይ የተመሰረተ ቡድን ለመገንባት ጥረቶችን ቢያደርግም ውጤታማ ለመሆን ተቸግሯል።

ድቻ ከሰበታ ከተማ ጋር አቻ በተለያየበት ጨዋታ በደለለኝ ደቻሳ አሰልጣኝነት ጊዜ ኳስን ለመቆጣጠር አብዝቶ ከመፈለግ እሳቤ ወጥቶ ኳስን ለተጋጣሚያቸው በመልቀቅ ቀጥተኛ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርግ በስፋት ተስለውሏል። ምንም እንኳ አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ጨዋታውን በሜዳው ጠርዝ ተገኝተው ባይመሩም በእርሳቸው ተመራጭ በሆነው የጨዋታ መንገድ የተቃኘ እንደነበር ግን የቡድኑ እንቅስቃሴ ላይ በጉልህ ታይቷል።


👉 አሸናፊ በቀለ በአለባበስ ማስገረማቸውን ቀጥለዋል

ባለፈው ሳምንት የገና በዓልን በማስመልከት በባህል ልብስ ወደ ሜዳ የመጡት የሀዲያ ሆሳዕናው አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በዚህ ሳምንት ደግሞ የግዕዝ ፊደላት የታተመበት ከረባት አድርገው ትኩረትን ስበዋል።


ዓበይት አስተያየቶች

👉አብርሀም መብራቱ ቡድኑ ጥንቃቄ ላይ ስለማተኮሩ

“በትክክል የጥንቃቄ ጨዋታ ነው የመረጥኩት። ምክንያቱም ያልተዘጋጀ ቡድን ልክ እንደተዘጋጀ ቡድን ደፍሮ መንቀሳቀስ ስለሌለበት ማለት ነው። ስለዚህ ትልቁ ስራችን የነበረው በተቻለ መጠን ግብ እንዳይቆጠርብን ማድረግ ነው። ከዚያ በኋላ ግን በምናገኛቸው አጋጣሚዎች እና ቀይረን ባስገባናቸው አጥቂዎች ለመጫወት ነበር። ያው አንድ አጥቂ ሳልቀንስ ቀርቻለሁ። ከአካል ብቃት ጋር ተያይዞ ቢያድግልኝ በጉዳት ነው የወጣብን። እንደገና ደግሞ በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች አብዱልባስጥም ተጎድቷል። ‘ቀይረኝ !’ እያለ ‘ቅያሪ ጨርሻለሁ’ ብዬው ነው። ከዛ አንፃር የመጀመሪያው ስራችን ግብ እንዳይገባብን ማድረግ ነበር። ያንን አሳክተን ወጥተናል ማለት እችላለሁ እንጂ ፈጣሪ ተጫዋቾችን ቀንሰን ነው የገባነው።”

👉ዘላለም ማቲዮስ ከጥንቃቄ አንፃር ቡድኑ ያሰበውን ስለማሳካቱ

“አዎ ! ያሰብኩትን አሳክቻለሁ ብዬ ነው የማስበው ፤ የጎል ዕድሎችንም ፈጥረናል። አምስት ጨዋታዎችን ተሸንፈን ነው የመጣነው። ያንን ሥነ-ልቦና ለመገንባት አንድ ነጥብ ማግኘት አለብን የሚለውን ሀሳብ አሳክቻለሁ።”

👉ጳውሎስ ጌታቸው ስለ ቤካም አብደላ

“እንግዲህ ወደ ጅማ ከመጣሁ በኃላ ያወጣሁት ልጅ ነው። አሁንም ተቀይሮ ሲገባ በቢጫ ቴሴራ ነው። ቴሴራ ወጥቶለት ምናምን እንዳይመስላችሁ። እና ከጅማ እነደዚህ ዓይነት ልጆች ማውጣት ነው የእኔ ትልቁ ነገር። ቡድኑን በተረጋጋ መንገድ ለማስቀጠልም የምችለውን ሁሉ አደርጋለው።”

👉ማሒር ዴቪድስ ስለጌታነህ ከበደ የዕለቱ ብቃት…

“ስለእሱ ምን ማለት እችላለሁ ? ጌታነህ ባለፉት ዓመታትም የተረጋገጠለት ግብ አስቆጣሪ ነው ፤ ቡድኑንም ይመራል። ነገር ግን አሁንም የምደግመው ውጤቱ የቡድን መሆኑን ነው። ጌታነህ ግቦችን አስቆጥሯል ፤ ግን አማካይ ላይ ካልሰራን ፣ መከላከል ላይ ካልሰራን ፣ በመስመሮች ካልሰራን ውጤቱ አይመጣም። ለምሳሌ እንዳልከው ሳልሀዲን ተቀይሮ ገብቶ ልዩነት ፈጥሯል። ስለዚህ እውነት ነው ጌታነህ በምርጥ ብቃት ሦስት ግቦችን አስቆጥሯል። ቡድኑ ግን እንደአጠቃላይ ሦስት ነጥቦችን አሳክቷል።”

👉አስቻለው ኃይለሚካኤል ስለ ቡድኑ መሻሻል

“ከዚህ በፊትም እንደገለፅኩት ነው። እንደ አቅማችን መሻሻሎች አሉን። ሲጀምርም እንደ አቅማችን ሆነን ነው ትልቁን አዳማ ለመገንባት እየሞከርን ያለነው። ግን ጊዜ ያስፈልገናል። ምንም ቢሆን ግን ከዕለት ዕለት ለውጦች አሉ። አብዛኞቹ ተጫዋቾች ወጣቶች ናቸው። ቡድኑም አዲስ ነው። እኔ በሐሒደት ጥሩውን አዳማን ለመሥራት ነው እየጣርኩ ያለሁት።”

👉ደግአረገ ይግዛው በአዳማው ጨዋታ ያደረጉት የአጨዋወት ለውጥ ስለመኖሩ

“መጀመሪያ ያሰብነውን ነገር በጨዋታው ለውጠናል ብዬ አላስብም። መጀመሪያም በጋራ ኳስን የመጫወት እቅድ ይዘን ነበር ስንጫወት የነበረው። ማለትም ኳስን ይዘን መስርተን ለመጫወት። በዚህ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ደግሞ የሚፈጠሩ ክፍተቶችን አህመድ ፍጥነቱን ተጠቅሞ እንዲጠቀም ነበር ያደረግነው። ምክንያቱም አዳማዎች ግጥግጥ ብለው ስለነበር ሲከላከሉ የነበሩት እነሱን ለመዘርዘር ወደ መስመር ኳሱን ማውጣት ነበረብን። ከዚህ በተጨማሪ ግን ተጋጣሚን ማስከፈት ስለነበረብን አልፎ አልፎ ረጃጅም ኳሶችን ተጠቅመናል።”

👉አሸናፊ በቀለ ጥንቃቄን መርጠው ስለመጫወታቸው እና የተጫዋቾች ጉዳት በዛሬ ጨዋታ ስለፈጠረባቸው ጫና

“ለዚህ የዳረገን አብዘኛዎቹ ተጫዋቾች ህመም ላይ መገኘታቸው ነው ለምሳሌ ግብ ጠባቂያችን ከአልጋ ተነስቶ ነው የመጣው። ስለዚህ የተጎዱብን ልጆችን ታሳቢ በማድረግ ስናጠቃም ስንከላከልም የምንበዛበትን መንገድ ታሳቢ አድርገን ነበር የገባነው።”

“ምንም ጥያቄ የለውም። ምክንያት እንዳይንብኝ እንጂ ሳሊፉ ፎፋና እና ቢስማርክ አፒያን የመሰሉ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾችን ማጣት በእርግጥም ጉድቶናል።”

👉ዘርዓይ ሙሉ በቶሎ ወደ ጨዋታው ስለመመለሳቸው እና ስለማሸነፋቸው

“የሚገርመው ተነጋግረን ነበር። ‘ግብ ቀድሞ እንኳን ቢቆጠርብን ከዚህ በፊት እንደነበረው መውረድ የለብንም። ምክንያቱም ዛሬ ሀዋሳ ከተማ ትናንትም ቅዱስ ጊዮርጊስ ተመርተው አሸንፈዋል።’ ብለን እሱን እሱን አንስተን አውርተን ነበር። እና ወዲያው ነው የታነሳሳነው። ከዚያ በኋላ በእንቅስቃሴ የተሻልን ስለነበርን እንደውም ብዙ ኳሶች ሳትን እንጂ ከዚህም በላይ ማስቆጠር እንችል ነበር። ቡድኑ ጭንቀት ውስጥ የቆየ ቡድን አይመስልም ነበር። ያጣነው የፊት መስመራችንም ከሞላ ጎደል ዛሬ የተሻለ ነው ብዬ ነው የማስበው። ሲዲቤ ዛሬ ከቡድኑ ጋር መሆኑ የፊት መስመሩን ጠንካራ አድርጎታል ብዬ ነው የማስበው። የተሻልን ነበርን ዛሬ ውጤቱ ይገባናል።”

👉ፋሲል ተካልኝ ሀዋሳ አምስት አማካዮች መጠቀም ባህርዳርን ክፍተት ስለማሳጣቱ

“በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ሰፋፊ ክፍተቶች ነበሩ። በቂ የመጫወቻ ሜዳ አግኝተናል። የግብ ዕድሎችንም መፍጠር ችለን ነበር፤ ግን አልተጠቀምንበትም። ምንም እንኳን የመስመር ተጫዋቾቼ እንደ ተመላላሽ (wing back) ቢሆኑም አጥቂዎቼ ከእነሱ ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅሞች እያገኙ አይደለም። ስለዚህ እዚህ ላይ ጠንክረን መሥራት ይኖርብናል።”


© ሶከር ኢትዮጵያ