ስምንተኛው ሳምንት የሚጀምርበትን ጨዋታ የተመለከተው ዳሰሳችን ይህንን ይመስላል።
ጨዋታው አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ በብሔራዊ ቡድን አብረዋቸው ከሰሯቸው ባልደረቦቻቸው ጋር የሚገናኙበት ሁለተኛው አጋጣሚ ይሆናል። ሦስተኛው ሳምንት ላይ ከአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት አሁን ደግሞ ከአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ጋር። ሆኖም ግንኙነታቸው ሁለቱም ጥሩ ሁኔታ ላይ ባልሆኑበት ወቅት ላይ ነው ያረፈው። በወጣ ገባ አቋም ሦስተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ባህር ዳርም ሆነ ከአንድ ድል ውጪ ማስመዝገብ ያልቻለው ሰበታ መጠኑ ይለያይ እንጂ ጥሩ የውድድር ዓመት እያሳለፉ ነው ማለት አይቻልም። በመሆኑም የነገው ግጥሚያ በመሸናነፍ ከተጠናቀቀ አንዳቸውን ወደ መጠነኛ እፎይታ ሌላኛቸውን ደግሞ ጫና ውስጥ ወደ መግባት ሊያደርሳቸው ይችላል።
ባህር ዳር በቂ የግብ ዕድል የመፍጠር ችግሩን መፍታት የቻለ በመሰለባቸው የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የተገኙትን ዕድሎች መጠቀም ሳይችል ለሀዋሳ እጅ ሰጥቷል። በቀሪዎቹ ረጅም ደቂቃዎች ቡድኑ አጋጣሚ በመፍጠር ተግባሩ አለመቀጠሉ ደግሞ በነገውም ጨዋታ ላይ ፈተና እንዳይሆንበት የሚያሰጋው ነጥብ ነው። ከአጥቂ ጀርባ የሚሰለፉ የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን አማካዮች ቁጥር ከሦስት ወደ አራት ከፍ በማድረግ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ለዚህ ችግሩ መፍትሄ ለማበጀት እየሞከረ ያለው ቡድኑ የሚፈልገውን ስኬት ያገኘ አይመስልም።
ከአሰልጣኙ ትዕግስት የተላበሰ አቀራረብ በመነሳት ስንመለከተው ግን ነገም ባህር ዳር በተመሳሳይ መልኩ ወደ ሜዳ በመግባት ውጤታማ ለመሆን እንደሚጥር መገመት ይቻላል። በተመሳሳይ ተዳክሞ እየታየ ካለው የተጋጣሚው አማካይ ክፍል ጋር ሲነፃፀር ወደ ፊት መሄድን ቅድሚያ የሚሰጥ እና በተሻለ ጉልበት የሚጫወት የመሐል ክፍል መያዙ እንደመጀመሪያዎቹ ጨዋታዎች የመስመር ተከላካዮች የማጥቃት ሚና ከፍ ማለት ከተጨመረበት በጨዋታው የተሻሉ የመጨረሻ ኳሶችን የመፍጠር ዕድል ይኖረዋል።
እንደ አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ አስተያየት በቂ ልምምድ ባለማድረጉ ጥንቃቄን መሰረት አድርጎ በመግባት ከድቻ ጋር ነጥብ የተጋራው ሰበታ ነገ ከፍ ያለ ፈተና ሊገጥመው ይችላል። ከሁሉም በላይ ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ለመግባት የሚያመነታ እና ለረጅም ደቂቃዎች መሀል ሜዳ ላይ ኳስ መያዝ የሚያዘወትር ዓይነት ቡድን ሆኖ መታየቱ ለጥቃት ሊዳርገው የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው። ነፃ የማጥቃት ሚና ያለው እንደ ፍፁም ዓለሙ ዓይነት ተጫዋቾች ያሉት ተጋጣሚው ኳስ መንጠቅ ከቻለ ከወላይታ ድቻ የተሻሉ ጥቃቶችን ሊሰነዝር እና ግቦችን ሊያገኝም ይችላል። ቡድኑ በተደጋጋሚ በመጀመሪያ አሰላለፉ ላይ ለውጦችን ሲያደርግ መታየቱ ደግሞ በየቦታው ለደካማ ጥምረቶች የዳረገው መሆኑ ሲታሰብም ይበልጥ የቅብብል ስህተቶችን ላለመስራቱ ማረጋገጫ አይሆንም። ሰበታ ከተጋጣሚ ባህሪ አንፃር አቀራረቡን የማይቀይር ከመሆኑም አንፃር በራሱ ሜዳ በሚሰራቸው ስህተቶች ነገም እንዳይቀጣ ያሰጋዋል።
ሰበታ ከተማ በሰባተኛው ሳምንት ባደረገው ጨዋታ ጉዳት ጨክኖበት ሦስት ተጫዋቾቹን አጥቷል። ከእነዚህ ውስጥ ታደለ መንገሻ እና ቢያድግልኝ ኤልያስ ለነገው ጨዋታ የማይደርሱ ሲሆን የአብዱልባሲጥ ከማል የህክምና ውጤትም እየተጠበቀ ይገኛል። በተመሳሳይ በባህር ዳር ቤትም የጉዳት ዜና በርከት ብሏል። ጉዳት ላይ የሰነበቱት ሳምሶን ጥላሁን እና አቤል ውዱን ጨምሮ ዜናው ፈረደ ፣ በረከት ጥጋቡ እና የቡድኑ ዋነኛ አጥቂ ባዬ ገዛኸኝ ለጨዋታው እንደማይደርሱ ሰምተናል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– በተሰረዘው የውድድር ዓመት በባህር ዳር ከተማ የ 3-2 አሸናፊነት የተጠናቀቀው ጨዋታ ከግምት የማይገባ በመሆኑ ቡድኖቹ ነገ የመጀመሪያ የሊግ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ግምታዊ አሰላለፍ
ሰበታ ከተማ (4-2-3-1)
ፋሲል ገብረሚካኤል
ጌቱ ኃይለማርያም – መሳይ ጻውሎስ – አንተነህ ተስፋዬ – ያሬድ ሀሰን
ዳንኤል ኃይሉ – መስዑድ መሐመድ
ፉዓድ ፈረጃ – ዳዊት እስጢፋኖስ – ቡልቻ ሹራ
እስራኤል እሸቱ
ባህር ዳር ከተማ (4-1-4-1)
ሀሪስተን ሄሱ
ሚኪያስ ግርማ – ሰለሞን ወዴሳ – መናፍ ዐወል – አህመድ ረሺድ
ፍቅረሚካኤል ዓለሙ
ሳላምላክ ተገኝ – አፈወርቅ ኃይሉ – ፍፁም ዓለሙ – ግርማ ዲሳሳ
ምንይሉ ወንድሙ
© ሶከር ኢትዮጵያ