ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና መከላከያ ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቀቀ

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ሰባተኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን 10:00 ሰዓት ላይ በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና መከላከያ ያለጎል ተለያይተዋል፡፡

ተጠባቂነቱ ከጨዋታው ቀደም ብሎ ግምት ያገኘ ቢሆንም በሜዳ ላይ የተመለከትነው ፉክክር ግን እጅጉን የተቀዛቀዘ ነበር፡፡ ተመሳሳይ ይዘት በነበረው የመጀመሪያው አርባ አምስት ሁለቱም ቡድኖች የተፈራሩ ስለመምሰለቸው ያሳዩት እንቅስቃሴ ማሳያ ነበር፡፡ ረጃጅም ኳሶች ወደ አጥቂ በመጣል ለማጥቃት አስበው የነበረ ቢሆንም ፍፁም ደካማ የነበረው የፊት መስመራቸው ዕቅዳቸውን የሚያሳካ አልሆነም፡፡

የመከላከያዋ አጥቂ ሴናፍ ዋቁማ በግንባር ገጭታ ትዕግስት አበራ የያዘችባት ሙከራ አስፈሪ የነበረ ሲሆን በአንፃሩ ከመሰሉ አበራ የቅጣት ምት ኳስ ውጪ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራን ማድረግ ያልቻሉት ኤሌክትሪኮች አብዛኛው የኳስ ፍሰታቸው መሀል ሜዳ ላይ የተገደበ ነበር፡፡ በቀሪዎቹ ደቂቃዎች በተወሰነ መልኩ በግራ በኩል በመሳይ ተመስገን አማካኝነት የተሻለ ቅርፅ ለመያዝ መከላከያዎች ቢሞክሩም ተጫዋቿ በጉዳት ከሜዳ ከወጣች በኃላ ግን እንቅስቃሴያቸው ሲባክን ተስተውሏል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ ሆነው የቀረቡት ኤሌክትሪኮች የነበሩ ሲሆን አዲሷን የክለቡ ፈራሚ ዮርዳኖስ ምዑዝን የሚያግዛት ተጫዋች ባለመኖሩ በግሏ የፈጠረቻቸውን ግልፅ ኳሶች ወደ ግብነት መለወጥ አልተቻለም፡፡ አሰልጣኞቹን እና ቡድን መሪውን በቅጣት ለማጣት የተገደደው መከላከያም በሌሎች ጊዜያዊ አሰልጣኞች እየተመራ ያሳየው የሜዳ ላይ ተነሳሽነት ወጥነት የጎደለው ነበር፡፡

በአጥቂዎቻቸው ደካማ የውሳኔ አሰሳጥ ወጣ ገባ ሲሉ የነበሩት መከላከያዎች በ68ኛው በቀይ ካርድ ተጫዋች ካጡ በኃላ በይበልጥ ተቸግረው ታይተዋል፡፡ በክስተቱ መዲና ዐወል ከኳስ ውጪ የኤሌክትሪኳን አማካይ ፂሆን ፈየራን በክርን በመማታቷ የዕለቱ ዋና ዳኛ ብዙወርቅ ኃይሉ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ አስወጥታታለች፡፡ በቀሪዎቹ ደቂቃዎች በልደት ቶሎአ ፣ ቤዛዊት ተስፋዬ እንዲሁም በትጋት ስትጫወት በነበረችው ዮርዳኖስ ምዑዝ ጎል ለማስቆጠር ኤሌክትሪኮች ቢንቀሳቀሱም ሳይሆንላቸው ቀርቷል፡፡ ጨዋታውም 0-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የኤሌክትሪኳ አዲስ ፈራሚ ዮርዳኖስ ምዑዝ በልሳን የሴቶች ስፖርት የጨዋታው ምርጥ ተብላ ተሸልማለች፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ