በውድድር ዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ ያገባው ጎል ከጨዋታ ውጪ የተባለበት የሰበታው አጥቂ ስለዛሬው ጨዋታ አነጋጋሪ ክስተቶች አስተያየቱን ሰጥቷል።
የዘንድሮው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የቀጥታ ስርጭት ሽፋን ማግኘቱን ተከትሎ የእግር ኳስ ቤተሰቡ ጨዋታዎችን በቴሌቪዥን መስኮት መከታተል መቻሉ ሜዳ ላይ የሚሰሩ ስህተቶች በቶሎ መነጋገሪያ እንዲሆኑ በር የከፈተ ይመስላል። በዚህ ረገድ በቅርብ ጊዜያት ልዩነት ለሁለተኛ ጊዜ ግብ የተሻረበት ፍፁም ገብረማርያም ደግሞ የዛሬው ጨዋታ መነጋገሪያ ሆኗል።
አምስተኛው ሳምንት ላይ ኢትዮጵያ ቡና እና ሰበታ ከተማ ባደረጉት ጨዋታ ላይ ያስቆጠረው ጎለል ከጨዋታ ውጪ በሚል የተሻረበት የሰበታው አጥቂ ፍፁም ዛሬም ተመሳሳይ ዕጣ ገጥሞታል። ቡድኑን 2-1 መምራት የምታስችል ኳስ ከመረብ ቢያገናኝም በድጋሚ ሳይፀድቅለት ቀርቷል። የዛሬውን ለየት የሚያደርገው ከቡልቻ ሹራ የተነሳችውን ኳስ ፍፁም ሳይነካት ቢቀር ኖሮ ጎል ትሆን የነበረ መሆኑ ነው። ፍፁም አጋጣሚው የፈጠረበትን ስሜት እንዲህ ነግሮናል።
“እኔ ከጀርባቸው እንደወጣሁ እያየሁት ነበር። ተከላካዮቹ ለበረኛው ቅርብ ስለነበሩ ራቅ ብዬ ነበር የቆምኩት። ያው እግር ኳስ ላይ የሚፈጠር ነገር ነው። ኳሷ ትወጣለች የሚል ነገር ነው ውስጤ የነበረው ለዛ ነበር ቀድሜ የተንሸራተትኩት። የግቡን ቋሚ ትገጫለች የሚል ሀሳብ ውስጤ ነበር። ያው ውጤትም እያጣን ስለነበር ወደ ድል የመመለስ ስሜት ውስጥ ነበርኩ። አሁን ምስሉን ስመለከተው ግን መግባት የምትችል ኳስ ነበረች። ሁኔታው ትንሽ አናዶኛል፤ ውጤትም ስላጣን። ”
“ጎሎች ቡድንን ያነሳሉ። ስታገባ የቡድኑ በራስ መተማመን አብሮ ይነሳል። እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ተደጋገሙብን። ቡድናችን ወደ ተሻለ እንቅስቃሴ በሚገባበት ሰዓት ላይ ነው እንደዚህ ዓይነት ውሳኔዎች የሚገጥሙት። እኔም በግሌ ግቦቹ ባይሻሩ አምስተኛ ጎሌ ይሆን ነበር። ወደ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች ፉክክር ውስጥ የምጠጋበት ሁኔታ ይፈጠር ነበር። አጋጣሚዎቹ ወደ ኋላ አስቀርተውኛል። ያም ሆኖ ከዚህ በኋላ ጎሎችን ለማስቆጠር እሠራለሁ።
“ረዳት ዳኞች የሚወስኗቸው ውሳኔዎች ላይ ግብ የተቆጠረባቸው ግብ ጠባቂዎች እና ተከላካዮች በቶሎ ድምፃቸውን የማሰማት ነገር አላቸው። ይህ ነገር የዳኞች ውሳኔ ላይ ተፅዕኖ ያለው ይመስለኛል። ከቡና ጋርምጋርም ሆነ አሁን ያገባሁት ኳስ በግልፅ የሚታይ ነው። እንዲህ ዓይነት ውሳኔዎች ጨዋታው ካለቀ በኋላም ቪዲዮዎች እየታዩ ዳኞች ትምህርት እንዲወስዱባቸው ቢደረግ መልካም ነው። ምክንያቱም እዚህ ጋር የሚከሰትን ስህተት ሌላው እንዲማርበት ያደርጋል።”
© ሶከር ኢትዮጵያ