የአሰልጣኞች አስተያየት | ሰበታ ከተማ 1-4 ባህርዳር ከተማ

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኞች ከሱፐር ስፖርት ጋር ቀጣዩን ቆይታ አድርገዋል።

አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ – ሰበታ ከተማ

የፉዐድ ፈረጃ ጉዳት ስለነበረው ተፅዕኖ እና ስለዳኝነት ጉዳዮች

አዎ በትክክል ተፅዕኖ ነበረው። የመሀል ክፍሉን ፈጣሪ በሆኑ ተጫዋቾች ለመገንባት ነበር መጀመሪያ ይዘን የገባነው ፤ ልጁ ተጎድቶ ወጣ። የተጎዳበት ሁኔታ ግልፅ እየሆነ ዳኞች በአምስት ሜትር ርቀት ማየት ካልቻሉ ይሄ በጣም ጉዳት ነው። ከዚያም በኋላ ተደጋጋሚ ጥፋቶች ሲሰሩ ዳኞች ለምን ዝምታን እንደመረጡ ለእኔ ግልፅ አይደለም። ከዛ በተጨማሪ በመጀመሪያው አጋማሽ ሙሉ ለሙሉ ጨዋታውን ተቆጣጥረን ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ በእኛ በኩል መጠነኛ የአካል ብቃት መውረድ እንዳለ ሆኖ በሥነ-ልቦናም ተጎድተናል። ከዚህ በፊትም ያገባናቸው ኳሶች ናቸው የሚሻሩት አሁንም የምናገባቸው ኳሶች ይሻራሉ ፣ ዳኞች በውድድሩ ላይ ትንሽ ተፅዕኖ እያደረጉ ነው ፤ ለውጥ እያመጡ ነው። እና ያ የተጨዋቾቼን ስሜት ጎድቶታል። ተጫዋቾቼም ስሜታዊ ከሆኑ በኋላ ከዳኞች ጋር በነበራቸው ምልልስ በተለይም ከረዳር ዳኛው ጋር ያሬድ በቀይ ወጥቷል። ግን ጨዋታው በምንፈልገው መልኩ ሊሄድ አልቻለም። ስለዚህ በዚህ በኩል ስለዳኝነቱ ብዙ ማለት ባልችልም። ዳኞች የውድድሩ ህይወቶች ናቸው ስህተትም ሊሰሩ ይችላሉ። ግን እንዲህ ዓይነት ቀላል እና የወረደ ስህተት መስራት ግን በዚህ ትልቅ ሊግ ላይ አይጠበቅባቸውም ማለት እፈልጋለሁ።

አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ – ባህር ዳር ከተማ

ስለጨዋታው

ሦስት ነጥቡን ማግኘታችን ለእኔም ለተጫዋቾቼም ብዙ ነገር ማለት ነው። ጥሩ ጨዋታ ነው ከመጀመሪያውም ፤ ብዙ ጨዋታው ላይ ቅሬታ የለኝ። ግን በመጀመሪያው አጋማሽ ጎሎችን ማግኘት ነበረብን። በሁለተኛው አጋማሽ ያንን ነው ለማስተካከል የሞከርነው። በመጀመሪያው አጋማሽ ትንሽ ከመከላከል ወደ ማጥቃት ስንሄድ ትንሽ ቀዝቃዛ ነበር ፤ ስለዚህ ኳሶች ይበላሹ ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ያንን ፍጥነት ለመጨመር ነው የሞከርነው። በቶሎ ጎል ማግኘታችን ጨዋታውን እንድናሸነፍ ረድቶናል ብዬ አስባለሁ።

ፍፁም ዓለሙ ቡድኑ ወደ ጨዋታው እንዲመለስ ስለማስቻሉ

አሁን እኔ ስለ ቡድኔ ባወራ ይሻላል። ፍፁም ሁሉም ሰው የሚያውቀው ነው። ጥሩ ተጫዋች ፣ ልዩነት ፈጣሪ መሆኑን ሁሉም ሰው ያውቀዋል። ዛሬ ግን እንደቡድን ከሽንፈት ወጥተን በጥሩ ጨዋታ ወደ አሸናፊነት መግባታችን ለእኛ ብዙ ነገር ማለት ነው። በዕረፍትም የነገርኳቸው በየቀኑ ነጥቦችን መጣል እና መሸነፍ ለእኔም ለእነሱም ክብር እንደማይመጥን ነበር የነገርኳቸው። ግን በመጨረሻ ተሳክቷል እና ደስ ብሎኛል።


© ሶከር ኢትዮጵያ