የጊዮርጊስ እና ድቻ አሰልጣኞች ከሱፐር ስፖርት ጋር ያደረጉት የድህረ ጨዋታ ቆይታ ይህንን ይመስላል።
አሰልጣኝ ማሂር ዴቪድ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
4-3-3ን ምርጫቸው ስለማድረጋቸው
4-3-3ንም ሆነ 4-4-2ትን ለመጫወት የተለየ ምርጫ የለኝም። እንደሁኔታው ይወሰናል ፤ ጨዋታውን በምንቀርብበት መንገድ እና ተጋጣሚያችን በሚያደርገው ነገር ላይ ይወሰናል። ስለዚህ እንደሁኔታው ተለዋዋጭ መሆን ይኖርብናል እንደ ሳላሀዲን ፣ ንግላንዴ እና አቤል ያሉ ተጫዋቾች ገብተው ልዩነት እንዲፈጥሩ ማድረግም ነበረብን።
አቤል ያለው በአቤል እንዳለ መለወጡ ታክቲካዊ ስለመሆኑ
አዎ ታክቲካዊ ነበር። የሚያገናኝ ብቻ ሳይሆን ወደ ውስጥ ሰብሮ የሚገባ ተጫዋች ያስፈልገን ነበር። ተጋጣሚያችን ከኋላ የሚታይ ባለ አምስት የተከላካይ ክፍል ነበረው። በሦስቱ ተከላካዮች መሀል በጣም ጠባብ ክፍተት ነበር የነበረው። ስለዚህም መሀል ላይ ኳስ ይዞ ወደ ውስጥ የሚገባ ሰው ያስፈልገን ነበር። እንዲህ ዓይነት ተጨዋች ሁሌም የሚገኝ ዓይነት አይደለም። እምብዛም እየተጫወት ያልነበረ ቢሆንም ዛሬ ጥሩ አስተዋፅኦ በማድረጉ ምስጋና ይገባዋል።
ድሉ ለቀጣይ ጨዋታ ስለሚፈጥረው መነሳሳት
እንዳለፈው ጨዋታ ነው። ከባድ ጨዋታ ነበር ፤ ከታች ካሉ ቡድኖች ጋር መጫወት። ያላቸውን ሁሉ ይሰጣሉ ፣ ያላቸውን ተጫዋቾች በሙሉ ከኳስ ጀርባ ያደርጋሉ። እኛም ይህን ተላምደን መፍትሄ መፍጠር ይጠበቅብናል።
አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው – ወላይታ ድቻ
ጥንቃቄ ስለመምረጣቸው
በትክክል ምክንያቱም አንደኛ እንደሚታወቀው ቅዱስ ጊዮርጊስ ለቻምፒዮንነት ከሚጫወቱ ቡድኖች ውስጥ አንዱ ነው። ሁለተኛ መጀመሪያ የራስህን ቡድን ነው የምታየው። የእኛ ስብስብ ከፊት ላይ ትንሽ የመሳሳት ነገር ስላለው ጥንቃቄው ላይ ትኩረት አድርገን በምናገኘው አጋጣሚ የምናስቆጥርበትን መንገድ ነው የመረጥነው። ለዚህም ደግሞ የነደፍነው ስትራቴጂ በተለይ ከመስመር የሚመጡ ተሻጋሪ ኳሶች ላይ ጥንቃቄ እንድናደርግ ነው የነበረው። መጨረሻ አካባቢ በሰራነው ስህተት ግን ጎል እንዲቆጠርብን ሆኗል።
ከኋላ በርካታ ተጫዋቾች ስለመጠቀማቸው
ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአብዛኛው የሚታወቁት በመስመር አጨዋወታቸው ነው። የእኛ የመስመር አማካዮች ወደ ኋላ ተለጥጠው እየተጫወቱ ምንአልባት የተከላካዮቹ ቁጥር ከበድ ያለ ሊመስል ይችላል። ከዛ በተረፈ አጥቂ ላይ በቂ ሰው የለንም አሁን ባለው ሁኔታ። ቀይረን ያስገባነው አጥቂ አድርገን ያጫወትነው እንኳን ተከላካይ ነው። እነዚህ ነገሮች እንደአጠቃላይ የፈጠሩብን ችግሮች ናቸው። ከመሀል ሜዳ አደራጅተን ወደፊት ለመሄድ ፊት መስመር ላይ ያለን ነገር የሳሳ ስለሆነ በምንፈልገው መንገድ አይሄድም። ኳሶች ተመልሰው ይመጣሉ አሁንም ኳሶች እናሸንፋለን አሁንም ተመልሰው ይመጣሉ። የሆነ ሆኖ በታክቲኩ ረገድ ጨዋታውን ለመቆጣጠር ሞክረን ነበር አልተሳካም።
© ሶከር ኢትዮጵያ