የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የጥር ወር የሶከር ኢትዮጵያ ምርጦች

በጥር ወር የተካሄዱ የአምስት ሳምንታት ጨዋታዎችን መሰረት በማድረግ በ 30% የአንባቢያን እና በ 70℅ የድረገፃችን ባልደረቦች ድምፅ ተከታዮቹን ምርጦች በወሩ ኮከብነት ሰይመናል።

የወሩ ምርጥ ተጫዋች – አቡበከር ናስር ( ኢትዮጵያ ቡና)

ኢትዮጵያ ቡና ጅማ ላይ በጥር ወር ካደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ዘጠኝ ነጥቦችን መሰብሰብ ችሏል። በእነዚህ ጨዋታዎች ላይ በሙሉ አቡበከር ናስር እንደ አጥቂ ግቦችን በማስቆጠር የሚጠበቅበትን አድርጓል። ተጫዋቹ በሸገር ደርቢ ሐት-ትሪክ ሰርቶ የአዲስ አበባ ቆይታውን እንዳገባደደው ሁሉ ጅማ ላይም ሲዳማ ላይ ሦስት ግቦችን በማስቆጠር ነበር ውድድሩን ያጠናቀቀው። ከግቦቹ ውጪ ቀሪዎቹን ሁለት ግቦች አመቻችቶ አቀብሎ ከነበረበት ከዚህ ጨዋታ በፊት በነበሩት የቡድኑ ተጋጣሚዎች ባህር ዳር ከተማ፣ ወላይታ ድቻ እና ጅማ አባ ጅፋር ላይም አንድ አንድ ግቦችን ከመረብ አገናኝቷል። ይህንን ተከትሎም የቅርብ ተፎካካሪው የሆነው ሙጂብ ቃሲምን በሁለት በልጦ በ14 ግቦች ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነቱን መምራት ጀምሯል።

በአሰልጣኝ ካሣዬ አራጌ ቡድን ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ በራስ መተማመኑ እየጨመረ የመጣው አቡበከር የቡድኑ የልብ ምት እየሆነ የመጣበትን የአንድ ወር ነበር ያሳለፈው። ከግራ መስመር ከሚነሳበት የቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ በመሐል አጥቂነት ከተሰየመ በኋላም የተጋጣሚ ተከላካዮችን አምልጦ በመግባት ቡና የማጥቃት ሂደቶቹ አስፈሪ እንዲሆኑ ብሎም የፍፁም ቅጣት ምቶች እንዲያገኝ መነሻ ሲሆን ማስተዋል ችለናል። በአጠቃለይ በቡድኑ ውስጥ እየጎላ የመጣው ተፅዕኔ ፈጣሩነቱም በግቦች የታጀበ ሆኖ የወሩ ምርጥ ክብርን በድጋሚ ለመቀዳጀት አብቅቶታል። ተጫዋቹ በአንባቢያንም ሆነ በድረገፃችን ከፍተኛ ድምፅ ያገኘ ሲሆን በዚህም በድምሩ 95.8 ነጥብ በማግኘት ቀዳሚ ሆኗል።

የፋሲል ከነማው የግብ አዳኝ ሙጂብ ቃሲም በ69 አጠቃላይ ነጥብ እና የወልቂጤ ከተማው የመሐል ሜዳ ኮከብ አብዱልከሪም ወርቁ ደግሞ በአጠቃላይ 65 ነጥብ አቡበከርን ተከተለው በሶከር ኢትዮጵያ የወሩ ምርጦች ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ ተጫዋቾች ሆነዋል።

የወሩ ምርጥ አሰልጣኝ – ሥዩም ከበደ (ፋሲል ከነማ)

ሊጉን በአንደኝነት እየመሩ የሚገኙት ፋሲል ከነማዎች በጅማ በነበራቸው የአራት ጨዋታዎች ቆይታ እጅግ ስኬታማ ነበሩ። ዘጠኝ ግቦችን ከመረብ ባሳረፉባቸው ጨዋታዎች በተጋጣሚዎቻቸው መረባቸውን ሳያስደፍሩ ሙሉ ነጥቦችን አሳክተው ነበር የምዕራብ ኢትዮጵያዋን ከተማ የተሰናበቱት። ከዚህ ቀደም ብሎ ግን ቡድኑ ውስጥ በነበሩ ክፍተቶች እና በሜዳ ላይ በሚታይበት መቀዛቀዝ ምክንያት የአሰልጣኙ ወንበር መነቃነቅ ጀምሮ ነበር። ያም ቢሆን ቀጣዮቹ ጨዋታዎች ይህንን የሚያስረሱ ሆነው በድኑን ወደ ስኬት የወሰዱ ነበሩ።

በዚህ ሒደት ውስጥ የአሰልጣኝ ሥዩም ከበደን ሚና መገመት ቀላል ነው። የቡድን መንፈሱ መረበሽ ጀምሮ የነበረውን ቡድን ወደ አንድ በማምጣት በሙሉ ልብ በአሸናፉነቱ እንዲቀጥል ማድረጋቸው ከፍ ያለ ነጥብ የሚያሰጣቸው ነው። በጨዋታዎቹ ከተጠቀሙበት ብዙ ተለዋዋጭነት የማይታይበት ቡድን ውስጥም እንደ በዛብህ መለዮ ዓይነት ተጫዋቾችን አበርክቶት ከፍ በማድረግ እና ለወጣት ተጫዋቾችም ዕድሉን በመስጠት ፋሲል አዲስ አበባ ላይ ከነበረው በተለየ ሁኔታ ጠንክሮ እንዲቀርብ አድርገውታል። በዚህም በድረገፃችን በቀዳሚነት በአንባቢያን በሁለተኝነት፤ በድምር ነጥብ 86.8 የጥር ወር ምርጥ አሰልጣኝ ሆነዋል።

ኢትዮጵያ ቡናን ሰባት ነጥቦች ያስጨበጡት አሰልጣኝ ካሣዬ አራጌ በአንባቢያን ቀዳሚ ሆነው በድረገፃችን ሁለተኛ ደረጃ በመያዝ በአጠቃላይ 73.4 ነጥብ ተከታዩ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ የወላይታ ድቻን ደካማ አካሄድን ያቃኑት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው በ59.8 አጠቃላይ ነጥብ ሦስተኛ ደረጃን መያዝ ችለዋል።

የወሩ ምርጥ ግብ ጠባቂ – ሚኬል ሳማኬ (ፋሲል ከነማ)

በፋሲል ከነማ የ100℅ ድል ውስጥ የማሊያዊው ግብ ጠባቂ ሚና ሳይነሳ አይታለፍም። ግለሰባዊ ስህተቶች ቡድኖችን ነጥብ ሲያሳጡ ስንመለከት መቆየታችን በራሱ ሳማኬ ግብ አለማስተናገዱ የግብ ጠባቂነት ኃላፊነቱን በአግባቡ እንደተወጣ ማሳያ ነው። እርግጥ ነው ፋሲል ከነማ ጠንካራ የተከላካይ መስመር ይዞ መቅረቡ ነገሮችን ለተጋጣሚዎቹ ቀላል አላደረጋቸውም። በዚህ ጥንካሬ እና ቡድኑ እንደቡድን ክፍተቶችን በመዝጋት ላይ ካለው ታታሪነት በተጨማሪ ሁሉንም ጨዋታዎች በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ የተካተተው ሳማኬ አበርክቶት ከፍ ያለ ነበር። 

ከባባድ ሙከራዎችን ከማዳን ባለፈ ከሀገር ውስጥ ተጫዋቾች ጋር ባለው ተግባቦት ቡድን ይመራበት የነበረበት መንገድ ራሱን ብቻ ሳይሆን የቡድን ጓደኞቹንም ከስህተት ይጠብቃል። ከዚህ በተጨማሪ ሚኬል ሳማኬ ከአዳማ ከተማ ጋር በተደረገው ጨዋታ የፍፁም ቅጣት ምትም በማዳን ችሎታውን ያሳየበትን ወር አሳልፏል። በተመልካቾች ሁለተኛ በድረገፃችን ቀዳሚ ስፍራን በመያዝ አጠቃላይ 91 ነጥቦችን በመሰብስብም የጥር ወር ምርጥ ግብ ጠባቂ ሆኗል።

የወልቂጤ ከተማው ጀማል ጣሰው በአንባቢያን ቀዳሚ፣ በድረገፃችን ሁለተኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ በአጠቃላይ 70.6 ነጥቦች ሁለተኛ ደረጃን ሲይዝ የሰበታ ከተማው ምንተስኖት ዓሎ በ44 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ መያዝ ችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ