በኢትዮጵያ እግርኳስ በዳኝነት ዘርፍ ያለፉትን ዓመታት እያገለገለች የምትገኘው እና በአሁኑ ወቅት በባላገሩ ምርጥ የድምፅ ተሰጥኦ ውድድር እየተሳተፈች ከምትገኘው ፌዴራል ዳኛ ብዙወርቅ ኃይሉ ጋር ቆይታ አድርገናል።
ከመምርያ አንድ ጀምራ አሁን በፌደራል ዳኝነት በሴቶች ፕሪምየር ሊግ በጥሩ ብቃት እያገለገለች ትገኛለች። አስቀድማ በረዳት ዳኝነቱ ያለፉትን አምስት ዓመታት ሰርታለች። ካለፈው ዓመት ጀምሮ የምትዳኝበት ቦታን በመቀየር ከረዳት ዳኝነት ወደ ከመሐል ዳኝነት በመገባት እያገለገለች የምትገኘው ብዙወርቅ በሁለተኛ ዲቪዚዮን የጀመረው የዋና ዳኝነት አገልግሏቷ በማስከተል ወደ አንደኛ ዲቪዚዮን የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ከፍ በማለት በትናንትናው ዕለት ለመጀመርያ ጊዜ ኢትዮ ኤሌትሪክ ከመከላከያ ያደረጉትን ጨዋታ መምራት ችላለች።
የዛሬው ትኩረታችን ዋና ዓላማ ከዳኝነት ውጭ ስላለውና በውስጧ አቆይታው አሁን መታየት ስለጀመረው ሌላኛውን ተስጥዖ ልናወራቹ ወደን ነው። ብዙወርቅ ኃይሌ በባላገሩ ምርጥ የድምፅ ተስዕጦ ውድድር ላይ እየተካፈለች ሲሆን በዚህ ሳምንት ለዕይታ በበቃው የመጀመርያው ዙር ውድድር ላይ ቀርባ በቢጫ ካርድ ማለፏን መመልከት ችለናል። ይህን አስመልክቶ ከብዙወርቅ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙርያ ቆይታ አድርገን እንዲህ አቅርበነዋል።
ወደ ሙዚቃው እንዴት ልትገቢ ቻልሽ ?
በነገራችን ላይ የሙዚቃ ሥራን ወደ ስፖርቱ ከመግባቴ በፊት እሰራ ነበር። በመሐል ትምህርት ጀመርኩና ሙዚቃውን አቋረጥኩ። ከዳኝነቱ በተጨማሪ በነርሲንግ ዲፕሎማ አለኝ። ትምህርት ውስጥ ስገባ ጫና በዛና ሙዚቃውን ተውኩት እንጂ በአካባቢዬ ሰበታ ከተማ አዮ ከሚባል ባንድ ጋር እሠራ ነበር። ከዛ ውጭ የተለያዩ ሠርጎችን እሠራ ነበር። አሁን ወደ ዳኝነቱ ከገባው በኃላ ለተለያዩ ወድድሮች ለመጓዝ ሰብሰብ ስንል እንደ መዝናኛ እዘፍንላቸው ነበር። ጓደኞቼ ይሄን ይሰሙና “ድምፅሽ ያምራል ጥሩ ነው” ይሉኛል። ቤተሰቦቼም ወደ ሙዚቃው እንድመለስ ግፊት ሲያደርጉብኝ ለምን አልሞክርም ብዬ ሄድኩ። ያያችሁት ሆኗል።
በባላገሩ ምርጥ ቢጫ ካርድ አይተሽ ወደ ቀጣዩ ዙርም አልፈሻል። አንቺ የማስጠንቀቂያ ቢጫ ካርድ ለተጫዋቾች ትሰጫለሽ። አንቺ ቢጫ ሲሰጥሽ ምን ተሰማሽ ? የተሰጠሽ ቀይ ካርድ ቢሆንስ ኖሮ ?
(እየሳቀች) በዛ ሰዓት በጣም ደንግጫለሁ። በጣም ሰርቼ መጥቻለው ብዬ ስላሰብኩ አረንጓዴ ይሰጠኛል ብዬ ነበር ያሰብኩት፤ ቢጫ ተሰጠኝ። ግን ስሜቱ በጣም ይከብዳል። ይበልጥ የተሰማኝ ደግሞ ለተጫዋቾቹ ነው። ውጤት ላይ ሆነው ቢጫ በምንሰጣቸው ሰዓት የሚሰማቸው ስሜት በጣም ያስደነግጣል። ቀይማ ከሆነ በቃ አታስበው በጣም ከባድ ነው። ‘ካርድ የሚሰጥ ሰው ለራሱም ይሰጠዋል ለካ’ ብዬ ራሴን ታዘብኩት። ምንም ማድረግ አይቻልም መቀበል ብቻ ነው።
የባላገሩ ዳኞች ‘ለተጫዋቾች ቀይ ካርድ ስትሰጪ ምን ይሉሻል?’ ብለው ሲጠይቁሽ ‘አፈርፍረሽ ብዪው ይላሉ’ ብለሽ ተናግረሽ ነበር። ትናንት የመጀመርያ ቀይ ካርድ መዲና ዐወል ላይ ስትመዢ ተጫዋቿ ምን አለችሽ ?
(በጣም እየሳቀች) ጥፋቷን ስላወቀች አጎንብሳ ነው የወጣችው። ምንም አላለችም። ደስ የሚለው ይህ ነገር ነው። ‘አፈርፍረሽ ብይው’ አላለችም።
በውድድሩ የመጀመርያውን ዙር አልፈሻል። በቀጣይ በሙዚቃው ዘርፍ ምን ለማሳካት ታስቢያለሽ ?
የባላገሩ ውድድር አሁን ተጀምሯል። ይህ ብቻ አይደለም ሌላው ደግሞ በቀርቡ በፋና ላምሮት ለመወዳደር ተመዝግቤያለው። በእርሱም እሞክራለው። በዚህ ብቻ አላበቃም አንዳንድ ሰዎች እያናገሩኝ ነው። በእርግጠኝነት በባላገሩ እና በፋና ላምሮት ውድድሮች ባይሳካ እንኳ አንድ የራሴን ሙዚቃ እንደምሰራ አስባለሁ። ቢያንስ በእርግጠኝነት አንድ ነጠላ ዜማ እሰራለው።
ምን አልባት ጨዋታ እያጫወትሽ ተጫዋቾች በዳኝነት ውሳኔዎች ደስተኛ ሳይሆኑ ቀርተው በሙዚቃው ሙያሽ ተንተርሰው ሜዳ ውስጥ ቢቀልዱ? ያልሆነ ነገር ሊናገሩሽ ቢችሉስ ?
ያው ሊቀልዱ የሚችሉት በስራዬ ስህተት ብሰራ ነው። ለዚህም ምን አልባት አዝናኚኝ ሊሉኝ ነው የሚችሉት ወይም ደግሞ ‘ሙዚቃ መሰለሽ?’ ሊሉኝ ይችላሉ። ይህ የሚጠበቅ ሊሆን ይችላል። ግን እኔ ደግሞ በጣም የማያሳፍር ተስዕጦ ነው ያለኝ። ይህ ዝም ብሎም አይመጣም። እንኳን ለመዝፈን ለማውራትም መታደል ያስፈልጋል። ስለዚህ ተጫዋቾች ምንም ቢሉ ብዙም አይሰማኝም።
በዳኝነቱ ጥሩ እድገት እያሳየሽ ነው። በቀጣይ የተሻለ ደረጃ ለመድረስ ምን ታቅጃለሽ ?
ከፈጣሪ ጋር በዋና ዳኝነቱ ፌዴሬሽኑም ጥሩ እያገዘን ወደ ላይ እየወጣን ነው። ፌዴሬሽኑ ከሚያደርግልን በተጨማሪ ባለሁበት አካባቢ ኢንተርናሽናል ዳኞች አሉ እንደ አስናቀች ገብሬ ያሉ። ከእነርሱ የተሻለ ነገር ተምሬ ከፈጣሪ ጋር ትልቅ ዕራይ አለኝ። በእርግጠኝነት እርሱንም አሳካለሁ።
© ሶከር ኢትዮጵያ