የነገ ከሰዓት በኋላውን ጨዋታ የተመለከቱ ነጥቦችን እንዲህ አንስተናል።
በተለያዩ የውጤት ፅንፎች ላይ የሚገኙት ሁለቱ ቡድኖችን በሚያገናኘው ጨዋታ ፋሲል የተሻለ የአሸናፊነት ግምት አግኝቷል። ከተጋጣሚያቸው አራት እጥፍ የሆነ ነጥብ የሰበስቡት ፋሲሎች ከሁለት ተከታታይ ድሎች በኃላ ለጨዋታው ሲደርሱ በአንፃሩ አዳማዎች አሁንም ከመጀመሪያ ጨዋታቸው በኋላ ድልን ማጣጣም አልሆነላቸውም።
በወልቂጤው ጨዋታ ከእስካሁኑ የተሻለ መነቃቃት ታይቶበት የነበረው አዳማ ከተማ በነገው ጨዋታ ጥንቃቄ ላይ ያተኮረ አቀራረብ እንደሚኖረው ይገመታል። ወደ ራስ ሜዳ ተስቦ ከመከላከል ባለፈ በመልሶ ማጥቃት ረገድ ግን ቡድኑ ፊት መስመር ላይ ያለበት ክፍተት አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ቀላል እንዳይሆንለት የሚያደርግ ነው። ሆኖም የተጋጣሚውን የማጥቃት እንቅስቃሴ በማቋረጥ በቶሎ ጎል ላይ ለመድረስ መሞከር የቡድኑ አማራጭ የማጥቃት መንገድ ሊሆን ይችላል። በዚህ ረገድ በማጥቃት ወቅት በተጋጣሚው ሜዳ ላይ በቁጥር በርክቶ ለመገኘት ቡድኑ ምን ዓይነት መፍትሄ ይዞ እንደሚመጣ ከጨዋታው የምንጠብቀው ይሆናል። ሌሎች አማራጮችን ከመጠቀም አንፃር ግን የአብዲሳ ጀማል እና ፍሰሀ ቶማስ መልካም ጤንነት ላይ መገኘት ለአሰልጣኝ አስቻለው ኃይለሚካኤል እፎይታ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። በጨዋታው አዳማ ከሱለይማን መሀመድ በቀር በጉዳት የሚያጣው ሌላ ተጫዋች አይኖርም።
ፋሲል ከነማ ካለበት ወቅታዊ አቋም አንፃር በነገው ጨዋታ ከተጋጣሚው ጠንካራ መከላከል ሊገጥመው ይችላል። ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ጎል ያላስተናገዱት ፋሲሎች አብዛኛውን ጊዜያቸውን በተጋጣሚ ሜዳ ላይ እንደሚያሳልፉ ሲታሰብ የኋላ ክፍላቸው መልካም አቋም ላይ መገኘቱ ከመልሶ መጠቃት ሊጠብቃቸው እንደሚችል ይገመታል። ክፍተት ላለመስጠት ሊጠነቀቅ ከሚችለው ተጋጣሚው አንፃርም ፋሲል ሽመክት ጉግሳ ከሚሰለፍበት መስመር እና ከሱራፌል ዳኛቸው የመሀል ሜዳ ጥቃት በተጨማሪ እየጎላ የመጣው የእንየው ካሳሁን የቀኝ መስመር የማጥቃት ተስትፎ ተጨማሪ ኃይል እንደሚሆንለት ይጠበቃል።
ለአምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ግብ አስቆጣሪነቱ ያልነጠፈው ሙጂብ ቃሲምም በቀድሞው ክለቡ ላይ ተመሳሳይ አቋም አሳይቶ ኳስ እና መረብን ያገናኛል ወይ የሚለው ጉዳይም የጨዋታው ተጠባቂ ነጥብ ነው። አጥቂው ከቀድሞው የቡድን ጓደኛው እና አዳማ ከወልቂጤ ጋር ባደረገው ጨዋታ አስደማሚ ብቃት በማሳየት የሰባተኛ ሳምንቱ የሶከር ኢትዮጵያ ምርጥ ግብ ጠባቂ መሆን ከቻለው ዳንኤል ተሾመ ጋር የሚገናኝባቸው ቅፅበቶች ትኩረትን ይስባሉ፡፡
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን ሰባት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ሪከርዳቸውም ተመጣጣኝነት ይስተዋልበታል። አንድ አንድ ጊዜ የተሸናነፉ ሲሆን ሌሎቹ አምስት ጨዋታዎች አቻ የተለያዩባቸው ናቸው። በሰባቱ ግንኙነታቸውም እያንዳንዳቸው ሦስት ሦስት ጎሎችን አስቆጥረዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ፋሲል ከነማ (4-2-3-1)
ሚኬል ሳማኬ
እንየው ካሳሁን – ከድር ኩሊባሊ – ያሬድ ባየህ – አምሳሉ ጥላሁን
ይሁን እንዳሻው – ሀብታሙ ተከስተ
ሳሙኤል ዮሐንስ – ሱራፌል ዳኛቸው – ሽመክት ጉግሳ
ሙጂብ ቃሲም
አዳማ ከተማ (4-2-3-1)
ዳንኤል ተሾመ
ታፈሰ ሰረካ – ደስታ ጌቻሞ – ትዕግስቱ አበራ – እዮብ ማቲያስ
ሙጃይድ መሀመድ – ደሳለኝ ደባሽ
ፍሰሀ ቶማስ – በቃሉ ገነነ – የኋላእሸት ፍቃዱ
አብዲሳ ጀማል
© ሶከር ኢትዮጵያ