ሁለቱ የሀዋሳ ክለቦችን ያገናኘው የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ረፋድ ላይ ተከናውኖ ሀዋሳ ከተማ በሁለቱ ወጣት አጥቂዎች የመጀመርያ እና መጨረሻ ደቂቃ ጎሎች 2-0 አሸንፏል።
ሀዋሳዎች ባህር ዳር ከተማን ማሸነፍ ከቻለው ቡድናቸው ውስጥ ኤፍሬም አሻሞን በወንድምአገኝ ማዕረግ ብቻ ለውጥ በማድረግ ለጨዋታው ሲቀርቡ ሲዳማዎች በአንፃሩ ድሬዳዋ ከተማን ሲረቱ ከተጠቀሙበት አሰላለፍ ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ ገብተዋል።
ሀዋሳዎች በሁሉም ረገድ የተሻሉ በነበሩበት የመጀመርያ አጋማሽ በርካታ የጎል ዕድል መፍጠር የቻሉ ሲሆን ጎል ማስቆጠር የቻሉትም ገና ከጅምሩ ነበር። በሦስተኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር ኤፍሬም አሻሞ ያሻገረውን ኳስ ብሩክ በየነ ኳሱ መሬት ሳይነካ በቀጥታ በመምታት ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል።
ስኬታማ የሚባል የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን የቀጠሉት ሀዋሳዎች በመጀመርያው አጋማሽ ጨዋታውን ለመጨረስ የሚያስችል ዕድሎች ፈጥረው ነበር። በ24ኛው ደቂቃ ደስታ ያቀበለውን ኳስ ነፃ አቋቋም ላይ የነበረው መስፍን በአግባቡ ባለመምታቱ ግሩም አሰፋ ተደርቦበት የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ሲወጣ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ደስታ ከግራ መስመር በቀጥታ መትቶ የጎሉ አግዳሚ ሲመልስበት ያገኘው ኤፍሬም መትቶ በድጋሚ ቋሚው የመለሰበት ሙከራዎች አስቆጪ እድሎች ነበሩ። በአጋማሹ መጠናቀቂያ ደቂቃ ብሩክ ከቀኝ መስመር ሰብሮ በመግባት ግብ ጠባቂው ባጠበበበት በኩል መትቶ መሳይ ያዳነበትም ሌላው ተጠቃሽ ሙከራ ነበር።
ኳስን ከመቀባበል በዘለለ ይህ ነው የሚባል የማጥቃት እንቅስቃሴ ያልነበራቸው ሲዳማዎች ገና በ34ኛው ደቂቃ በአማካይ ክፍሉ ለውጥ በማድረግ ወደ ጨዋታው ቅኝት ለመግባት ቢጥሩም የጎል ሙከራ ሳያደርጉ አጋማሹ ተጠናቋል።
ሁለተኛ አጋማሽ ሲጀምር አማካይ ክፍላቸው ላይ ጉልበት ለመጨመር በሚመስል መልኩ ዮሴፍ ዮሐንስን በዳዊት ተፈራ ቀይረው ያስገቡት ሲዳማዎች ጫን ብለው የመጫወት ምልክት አሳይተዋል። አጋማሹ እንደጀመረ አካባቢ አበባየሁ ዮሐንስ በቀኝ መምሰር ገብቶ ከሳጥን ውስጥ ያደረገው ሙከራም ይህንን የሚያሳይ ነበር። ሆኖም ቀስ በቀስ ሀዋሳዎች ሁለቱን መስመሮች በአግባቡ በመዝጋት የሲዳማን ጥቃት አቅም ማሳጣት ችለዋል።
ሀዋሳዎች ሙሉ ለሙሉ ውጤት ማስጠበቁ ላይ ብቻ ትኩረት ባያደርጉም የሲዳማን የፊት መስመር ተሰላፊዎች በቅርብ ርቀት በመቆጣጠር በመልሶ ማጥቃት የፊት አጥቂዎቻቸውን ለማግኘት ጥረት ማድረጋቸው ግን አልቀረም። ይህ አካሄዳቸው ፍሬ ያፈራው ግን ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት ነበር። በዚህም ወጣቱ አጥቂ መስፍን ታፈሰ ከመሐል ሜዳ የግራ አቅጣጫ ደስታ ዮሐንስ በጥሩ ሁኔታ የጣለለትን ኳስ ተቆጣጥሮ ግሩም ጎል በማስቆጠር የሀዋሳን መሪነት አስተማማኝ አድርጓል። ጨዋታውም በሀዋሳ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ