ከፍተኛ ሊግ | የምድብ ለ እና ሐ የዘጠነኛ ሳምንት የዛሬ ውሎ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ ለ እና ሐ የዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ሲጀምሩ የምድብ ለ ላይ መሪው አዲስ አበባ ከተማ ጋሞ ጨንቻን ሶዶ ከተማ ደግሞ አቃቂ ቃሊቲን በተመሳሳይ 2-1 ሲረቱ ሀምበሪቾ ዱራሜ ከነቀምት ከተማ ያለ ጎል ተለያይተዋል፡፡ በምድብ ሐ ደግሞ አርባምንጭ ከተማ ፣ ኢትዮጵያ መድን እና ደቡብ ፖሊስ ሙሉ ሦስት ነጥብ አሳክተዋል፡፡

ምድብ ለ

4፡00 ሲል የአንድ ሣምንት ተስተካካይ ጨዋታ የቀረው የምድብ ለ መርሐግብር በመሪው አዲስ አበባ ከተማ እና በጠንካራው ጋሞ ጨንቻ መካከል ተከናውኗል፡፡ እጅግ ማራኪ የሆነ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በታየበት በዚህ ጨዋታ ጋሞ ጨንቻዎች እስካሁን ካደረጓቸው ጨዋታዎች ላቅ ባለ ደረጃ ተሽለው ሲታዩ የመልሶ ማጥቃት እና ረጃጅም ኳሶቻቸው ለአዲስ አበባ ከተማዎች ፈተና ሆነው ነበር፡፡ አዲስ አበባ ከተማዎች በአንፃሩ ከሌላው ጊዜ በእጅጉ ተቀዛቅዘው ቢመጡም የአቡበከር ወንድሙ ከጉዳት መመለስ በደንብ የጠቀማቸው በሚመስል መልኩ አብዛኛውን ጊዜ ተጫዋቹ ወደ ተሰለፈበት ቀኝ መስመር አዘንብለው በመጫወት የጋሞ ጨንቻን የመከላከል ስህተት በመጠቀም ጎል ለማስቆጠር ጥረዋል፡፡ ይህም ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ በ19ኛው ደቂቃ ሮቤል ግርማ ከማዕዘን ሲያሻማ የጋሞ ጨንቻ ተከላካዮች ዝንጉነት ተጨምሮበት አቡበከር ወንድሙ በግንባር በመግጨት የመዲናይቱን ክለብ መሪ አድርጓል፡፡

ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ የሙከራ የበላይነቱን በእጃቸው ያስገቡት ጨንቻዎች ረጃጅም ኳሶቻቸው በይበልጥ ተጠቃሚ በሚያደርጋቸው መልኩ በመንቀሳቀስ በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ሰንዝረዋል፡፡ 27ኛው ደቂቃ ታደለ ፈለቀ ከቀኝ አቅጣጫ በረጅሙ ያገኘውን ኳስ ወደ ጎል ሲያሻማ ሲሳይ ማሞ በግንባር ገጭቶ ሳምሶን አሰፋ ከጎሉ ጫፍ እንደምንም ያወጣበት አጋጣሚ ምናልባት ጋሞ ጫንቻን አቻ ሊያደርግ ይችል የነበረ ቢሆንም በግብ ጠባቂው ጥረት መክኗል፡፡

ከዕረፍት መልስ ጋሞ ጨንቻዎች በተሻለ የመስመር አጨዋወት በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ብልጫን መውሰድ የቻሉ ቢሆንም የመከላከል ድክመታቸው ፈጣን ለሆኑን የአዲስ አበባ ተጫዋቾች የተመቸ ሲሆን በተደጋጋሚ መመልከት ችለናል፡፡ በዚህም 59ኛው ደቂቃ ዘላለም በየነ ከመስመር ያሻገራትን ኳስ ሳምሶን አሰፋ በአግባቡ መቆጣጠር ሳይችል በመቅረቱ በቅርብ ርቀት የነበረው ለገሰ ዳዊት በቀላሉ ወደ ጎልነት ለውጦ ጨንቻን ወደ 1-1 አሸጋግሯል፡፡ 

ሆኖም በሜዳ ላይ እንቅስቃሴያቸው ባይታሙም የተከላካይ እና የግብ ጠባቂ የአቋቋም ስህተት የሚንፀባረቅባቸው ጋሞ ጨንቻዎች 81ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት የተገኘችን አጋጣሚ አቡበከር ወንድሙ በግራ አቅጣጫ ከግብ ክልል ውጪ አክርሮ በመምታት ማራኪ ጎል ለራሱም ሆነ ለአዲስ አበባ አስቆጥሮ ጨዋታው በ2-1 ውጤት በአሰልጣኝ እስማኤል አቡበከር ቡድን አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡

የቀኑ ሁለተኛ መርሐ ግብር በወላይታ ሶዶ ከተማ እና አቃቂ ቃሊቲ መካከል 8፡00 ሰዓት ሲል ጀምሯል፡፡ አጨቃጫቂ የዳኝነት ውሳኔዎች ባየንበት በዚህ ጨዋታ አቃቂ ቃሊቲዎች ተሽለው በቅብብል ወደ ፊት ለመሄድ የሚያደርጉት ጥረት ስኬታማ የነበረ ቢሆንም የኋላ መስመራቸውን ደፍነው ባለመቅረባቸው በቀላሉ ለሶዶ አጥቂዎች የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ተጋልጠዋል፡፡ 
ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር አቃቂዎች አጥቂዎቻቸው በሳጥን ውስጥ ኳስን ይዘው ከግብ ጠባቂ ጋር አንድ ለአንድ በሚገናኙበት ወቅት በሁለት አጋጣሚዎች ግልፅ ዕድልነን አግኝተው በሶዶ ተከላካዮች በመጠለፋቸው ፍፁም ቅጣት ምት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ቢጠይቁም በዝምታ ማለፋቸው ሲያስቆጣቸው ታይቷል። ሆኖም ለመልሶ ማጥቃት ምቹ የነበሩት አቃቂዎች በሶዶ ከተማ ቀዳሚ ጎል ተቆጥሮባቸው፡፡ 

25ኛው ደቂቃ ላይ በዚሁ ሂደት የተገኘችን ኳስ ከቀኝ በኩል ታደለ ዳልጋ ሲያሻማ የአቃቂ ተከላካዮች ስህተት ረድቶት አላዛር ፋሲካ ወደ ጎልነት ለውጧት ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡ በ42ኛው ደቂቃ ሳምሶን ደጀኔ ላይ የአቃቂ ተከላካዮች በሰሩበት ጥፋት የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ሰለሞን ጌታቸው ቢመታውም ሰሚር ናስር በቀላሉ ይዞበታል፡፡ የጨዋታ ብልጫ የነበራቸው አቃቂዎች አጋማሹ ሊጠናቀቅ ጭማሪ ደቂቃ ላይ ከቀኝ የሶዶ ግብ ክልል አካባቢ የተገኘውን ቅጣት የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና አማካይ ጥላሁን ወልዴ በቀጥታ ሲያሻማ ከወልዋሎ አቃቂን የተቀላቀለው ብሩክ ሰሙ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር አቃቂን አቻ በማድረግ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ተመጣጣኝ የሆነ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ብናስተውልም አመዛኙን የጥቃት መንገድ ግን አቃቂ ቃሊቲዎች ይይዛሉ፡፡ በተለይ ከመሀል ሜዳ በሚነሱ እና በግራ እና ቀኝ ባዘነበለ የጨዋታ ሲስተም የአሰልጣኝ ዳዊት ታደለው ቡድን ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ ክልል የሚደርስበት ሂደት እጅጉን አስገራሚ ነበር፡፡የሁለቱ ቡድኖች እንቅስቃሴ ውበትን የተላበሰ ቢሆንም የዕለቱ ዳኛ ኃይል የተቀላቀለበትን አጨዋወት መፍቀዳቸው ጨዋታውን ያደበዘዘ እንደነበር መመልከት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ በመልሶ ማጥቃት የአቃቂን የመከላከል ስህተት በሚገባ ሲጠቀሙ የተስተዋሉት ሶዶዎች 65ኛው ደቂቃ ላይ በረጅሙ የተሻገረን ኳስ የአቃቂው ተከላካይ አዲሱ ሠይፉ መቆጣጠር የሚችላትን ኳስ ባለመቆጣጠሩ ከኋላው የነበረው ሠለሞን ጌታቸው በፍጥነት ኳሷን አግኝቷት ወደ ጎልነት በመለወጥ ሶዶ ከተማን ወደ 2-1 መሪነት አሸጋግሯል፡፡ በቀሩት ደቂቃዎች አቃቂዎች ተጭነው በመጫወት ጫናን መፍጨር ቢችሉም ጎል ማስቆጠር ባለመቻላቸው ጨዋታው በሶዶ አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የዕለቱ ዋና ዳኛ አሸናፊ በላይን ተበድለናል በማለት ሊያናግሩት በተጠጉበት ወቅት የአቃቂ ቃሊቲ የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ጋር ቃላትን ሲመላለስበት የነበረበት መንገድ ሊታረም የሚገባው ነው። በዳኛው የቃላት ምልልስ የተበሳጩት የአቃቂ ቃሊቲ አሰልጣኞችም በዳኛው ላይ ከፍተኛ አቤቱታን ሲያሰሙ የታዩ ሲሆን ዳኛውም የአቃቂ ረዳት አሰልጣኝ ሺፈራው መላኩን ቀይ ካርድ ሰጥቶታል፡፡

10፡00 ሀሞበሪቾን ከ ነቀምቴ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቋል፡፡ተመጣጣኝ ፉክክር በታየበት እና አመዛኙ የጨዋታ እንቅስቃሴ መሀል ሜዳ ላይ ብቻ ጎልቶ በታየበት የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ሀምበሪቾ ዱራሜዎች በተወሰነ መልኩ ብልጫን ማሳየት ቢችሉም የአጥቂዎቻቸው ደካማ የአጨራረስ ብቃት ያገኟቸውን ዕድሎች እንዳይጠቀሙ አድርጓቸዋል፡፡

ከርቀት ዋቁማ ዲንሳ ሞክሯት አብርሀም ይርጉ ባወጣበት አስቆጪ ሙከራ ሀምበሪቾዎቾ ቀዳሚ የነበሩ ሲሆን 41ኛው ደቂቃ ላይ ዳግም በቀለ የነቀምቴን የተከላካይ ክፍል ስህተት ተመልክቶ የሰጠውን ቢኒያም ጌታቸው አገባው ሲባል መጠቀም ሳይችል አጋጣሚዋን አምክኗታል፡፡

ረጃጅም ኳሶች ላይ ትኩረት ያደረጉት ነቀምቶች ወደ ኢብሳ በፍቃዱ በሚጣሉ ዕድሎችን ለመፍጠር ቢሞክሩም ኢላማውን የጠበቀ እና ግብ ጠባቂውን የፈተነ አልበረም፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ነቀምቴ ከተማዎች እስከ 75ኛው ደቂቃ ድረስ በፈጣን ሽግግር ጥሩ ቢንቀሳቀሱም በዚህም አጋማሽ ሀምበሪቾዎች የተሻሉ ነበሩ።

60ኛው ደቂቃ የሀምበሪቾው አማካይ ንስሀ ታፈሰ በነቀምቴው አስቻለው ኡታ ላይ በሰራው አደገኛ ጥፋት በቀይ ካርድ ከሜዳ ሊወገድ ችሏል፡፡ 83ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ደግሞ የነቀምቴው አጥቂ ቦና ቦካ የሀምበሪቾው አጥቂ ቢኒያም ጌታቸውን በክርኑ በመማታቱ በረዳት ዳኛው ጥቆማ በቀይ ከሜዳ ተወግዷል፡፡በጨዋታው ቀሪ ደቂቃዎች ሀምበሪቾ ብልጫን በመውሰድ ጎል ለማስቆጠር ቢጣጣሩም በመከላከሉ በቀሩት ደቂቃዎች ላይ የተጠመዱት ነቀምቶች አንዷን ነጥብ በማስጠበቅ ያለ ጎል ጨዋታው 0-0 ተፈፅሟል፡፡

በጨዋታው ላይ የኮቪድ 19 ቫይረስ የተገኘባቸው የነቀምቴ ከተማ ተጫዋቾች በማቆያ መቀመጥ ሲገባቸው ሜዳ ውስጥ ከተመልካች ጋር ቁጭ ብለው በመታየታቸው ከሜዳ እንዲወጡ የተደረገ ሲሆን በቀጣይም ይህ ድርጊት በመፈፀሙ ለጤና ማዕከሉ ሪፖርት ለማድረግ እንደሚገደዱ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡ ክለቡም የፈፀመው ድርጊት ያልተገባ በመሆኑ መታረም አለበት የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ እንወዳለን፡፡

ምድብ ሐ

ድሬዳዋ ላይ የዘጠነኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ተጀምሯል፡፡ ማለዳ 2፡00 ሲል ኢትዮጵያ መድን እና በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ኮልፌ ቀራኒዮን አገናኝቶ ከሽንፈት በተመለሰው ኢትዮጵያ መድን 2 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ መሐመድኑር ናስር እና አብዱልቃድር ነስሩ የመድንን የማሸነፊያ ጎሎች ከመረብ ያሳረፉ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

4፡00 ሲል የምድቡ ሁለተኛ ጨዋታ በመሪው አርባምንጭ ከተማ እና የካ ክፍለ ከተማ መካከል የተካሄደ ሲሆን በአርባምንጭ ከተማ 2 ለ 0 አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡ አርባምንጭ ከተማ ቀይሮ ወደ ሜዳ ባስገባው ተጫዋች ታግዞ ነው ድል ያስመዘገበው። 73ኛው ደቂቃ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው የቀድሞው የጋሞ ጨንቻ አጥቂ ፍቃዱ መኮንን በ80 እና በ85ኛው ደቂቃ ከመረብ ያሳረፋቸው ሁለት ግቦች አርባምንጭ ከተማ ነጥቡን ከፍ በማድረግ ምድቡን እንዲመራ አስችሏል፡፡

በምድቡ ሦስተኛ ጨዋታ 9:00 በደቡብ ፓሊስ እና ስልጤ ወራቤ መካከል ተደርጎ 20ኛው ደቂቃ ይድነቃቸው ለማ ከመረብ ያገናኛት ብቸኛ ኳስ ደቡብ ፖሊስን አሸናፊ አድርጋለች፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ