የአሰልጣኞች አስተያየት | ፋሲል ከነማ 4-0 አዳማ ከተማ

የከሰዓት በኋላው ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኃላ ሱፐር ስፖርት ከተጋጣሚ አሰልጣኞች ጋር ያደረገው ቆይታ ይህንን ይመስላል።

አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ – ፋሲል ከነማ

ስለጨዋታው

በመጀመሪያው አጋማሽ የመቻኮል ነገር ነበረብን። እርጋታ ያስፈለግ ነበር። ጎል ብዙ ስለደከምክ ስለታከት አይደለም። የኛ አጥቂዎችም አማካዮችም ለማግባት የነበራቸው ተነሳሽነት ጥልቅ ስለነበር ከጀርባቸው ሰው እየገባ ያስቸግር ነበር። ያ ሁሉ ጥድፊያ እንዲሁ ነው የባከነው። ሁለተኛው አጋማሽ ልናደርግ የሞከርነው አንደኛ ትዕግስት ሊኖረን ይስፈልጋል ፣ ኳስ ቁጥጥራችን መጀመሪያም ጥሩ ነው ያንን ግን ወደ ጎል ለመለወጥ እርጋታ ያስፈልገዋል ከሚለው አኳያ ነው ለውጥ ያደረግነው። አሁንም ሁለተኛው አጋማሽ ላይ እነሱራፌልም በብዛት ሀሳባቸው እዛ ጋር ነው ያለው። ስለዚህ የአሰላለፍ ለውጥም አድርገን ከ4-1-4-1 ወደ 4-2-3-1 ወስደነዋል። እንደገና የተሻለ ነገር ለማድረግም አጥቂም መጨመር ፈልገናል። ዞሮ ዞሮ ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን የጎል ብልጫም ስለሚያስፈልግ ተጭነን ተጫውተናል። ከዕረፍት በኃላ ጨዋታውን ቀለል አድርገን ይዘነዋል።

ስለናትናኤል ገብረጊዮርጊስ የዕለቱ ብቃት

ናቲ የሚገርምህ ነገር እኔ ከፋሲል ከመጣሁበት ጊዜ ጀምሮ የምታይበት ነገር በጣም ያጓጓል ፤ በተለይ ልምምድ ላይ። እንደውም አሁን እዚህ 10% የሰራው ነገር የለም። ልምምድ ላይ ጉልበቱ ፣ አቅሙ የሚያደርጋቸው ነገሮች ልክ እንደበሳል ተጫዋች ነው እንቅስቃሴ የሚያደርገው። እንደዚህ ዓይነት ተጫዋቾች የሚያስፈልጋቸው የጨዋታ ልምድ ብቻ ነው። ስለዚህ ፋሲል ላይ በአንድ ጊዜ ወጣቶቹኑ እያስገባህ ትልቅ ይሆናሉ ማለት አይደለም። ግን እንዲህ ዓይነት ክፍተት እየሰጠሀቸው እንዲጠቀሙ ማድረግ ከዛ ልጁ ራሱ እያዳበረ የሚሄደው በራስ መተማመን አለ። ከሲኒየሮች ያላነሰ ብዙ ነገር የማድረግ አቅም አለው። ስለዚህ በዚህ መልኩ ከመጣ ለፋሲል ብዙ ዓመት የሚያገለግል ለሀገርም የሚያገለግል ጠንካራ ተጫዋች ይሆናል ብዬ አስባለሁ።

አሰልጣኝ አስቻለው ኃይለሚካኤል – አዳማ ከተማ

የታፈሰ እና ጀሚል ጉዳት ስለፈጠረው ተፅዕኖ

ያው የሚታወቅ ነው። በመጀመሪያው አጋማሽ የሁለት ተጫዋቾች መውጣት ያሰብነውን እንድናደርግ አላደረገንም። በተረፈ ግን ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች አለመጠቀማችን ዋጋ አስከፍሎናል ፤ ያው ጉዳቱ እንዳለ ሆኖ።

ስለቡድኑ የመጨረስ ችግር

እንደአጋጣሚ ዕድሉን ያገኙት ልጆች ከጉዳት የመጡ ናቸው ሁለቱም። ትንሽ ከጨዋታ መራቃቸው አስተዋፅዖ አድርጓል ነው የምለው ፤ ወደ ፊት ያው ተስተካክለን ለመቅረብ እንጥራለን እንግዲህ። ግን ያው ከጉዳት ማገገማቸው ለቡድናችን ጥሩ ነው። ውድድሩ ገና ነው ወደፊት ለምናደርገው ጨዋታ የእነሱ መኖር ግብዓት ይሆነናል።


©ሶከር ኢትዮጵያ