የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የዛሬ ውሎ…

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዛሬ በምድብ ሀ እና ለ በተደረጉ ሰባት ጨዋታዎች ሲደረጉ መከላከያ ወደ መሪነት የተመለሰበትን ድል አሳክቷል። የምድብ ለ መሪዎቹ አዲስ አበባ እና ሀምበሪቾም ድል አስመዝግበዋል።

ምድብ ሀ

ባቱ ላይ የሚደረገው የምድብ ሀ መርሐ ግብር አምስተኛ ሳምንት ሁሉም ጨዋታዎች ዛሬ ከረፋድ ጀምሮ ተካሂደዋል። 03:00 ላይ ፌዴራል ፖሊስ የከዚህ ቀደሙ ጥንካሬው ላይ የማይገኘው ለገጣፎ ለገዳዲን 2-1 ማሸነፍ ችሏል። ታምራት ኢያሱ በ17ኛው ደቂቃ ፖሊስን ቀዳሚ ሲያደርግ ዳዊት ቀለመወርቅ በፍፁም ቅጣት ምት ለገጣፎን አቻ ቢያደርግም ከሦስት ደቂቃ በኋላ አንተነህ ተሻገር ፌዴራል ፖሊስን አሸናፊ ያደረገች ጎል አስቆጥሯል።

ቀጥሎ የተደረገው የወልዲያ እና ሰሜንሸዋ ደብረብርሀን ጨዋታ በደብረብርሀን 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። አትክልት ንጉሤ በ 30ኛው፣ ካሣሁን ሰቦቃ በ68ኛው ደቂቃ የደብረብርሃንን ጎሎች አስቆጥረዋል። ደካማ አጀማመር ያደረገው ወልዲያ እስካሁን ያረጋቸውን ጨዋታዎች በሙሉ ተሸንፎ ግርጌ ላይ ተቀምጧል።

8:00 ላይ መከላከያ ወሎ ኮምቦልቻን ገጥሞ 4-2 አሸንፏል። የ2009 የከፍተኛ ሊግ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ዘካርያስ ፍቅሬ ሁለት፣ አቤል ነጋሽ እና ካርሎስ ዳምጠው አንድ አንድ ጎል ለመከላከያ አስቆጥረዋል። ጫላ ድሪባ እና ነቢዩ አህመድ የኮምቦልቻ ጎል አስቆጣሪዎች ናቸው። ድሉን ተከትሎ መከላከያ የምድቡ መሪነትን መልሶ ተረክቧል።

የዕለቱ የመጨረሻ የምድቡ ጨዋታ የተደረገው እስካሁን ሽንፈት ያላስተናገዱት ደሴ ከተማ እና ገላን ከተማን ያገናኘው ሲሆን ያለ ጎል ጨዋታው ተጠናቋል።

ምድብ ለ

2፡00 ሲል አቃቂ ቃሊቲን ከ ሻሸመኔ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ ብርቱ ፉክክር አሳይቶ በአቃቂ ቃሊቲ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። የአቃቂዎች ብልጫ በታየበት ጨዋታ በተደጋጋሚ ወደ ሻሸመኔ ከተማ የግብ ክልል ኳስን መሠረት ባደረገ ፍሰት መድረስ ቢችሉም አጋጣሚዎችን ወደ ጎልነት የመለወጥ ከፍተኛ ክፍተት በመጀመሪያው አጋማሽ ቡድኑ ላይ ይታይ ነበር፡፡ በአንፃሩ ረጃጅም ኳሶች ላይ ትኩረት ያደረጉት ሻሸመኔዎች ከወትሮው ፈጣን የመልሶ ማጥቃት የአጨዋወት መንገዳቸው ተቆጥበው መቅረብ የቻሉ ሲሆን ከአማካይ ክፍሉ ወደ አጥቂዎች ኳስን በአግባቡ ማድረስ የሚችሉ ተጫዋቾች አለመኖራቸው አንድ ጎል ሳንመለከት ይህኛው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡

ከእረፍት መልስ በቀጠለው ጨዋታ አቃቂዎች አሁንም በቅብብል ከቀኝ እና ከግራ መስመር በሚነሱ አጋጣሚዎች ለመፍጠር ታትረዋል፡፡ሆኖም ረጃጅም ኳስ ለአጥቂዎቹ ማናዬ ፋንቱ እና በኃይሉ ወገኔ ቶሎ ቶሎ ማድረስ ላይ ትኩረት ያደረጉት ሻሸመኔዎች ቀዳሚ ግብ አስቆጣሪዎቹ ነበሩ፡፡ 52ኛው ደቂቃ ላይ ከድር አድማሱ በበሀይሉ ወገኔ ላይ ጥፋት በሳጥን ውስጥ ፈፅመሀል በሚል አወዛጋቢ ውሳኔ መነሻነት የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ማናዬ ፋንቱ አስቆጥሮ ሻሸመኔን መሪ አድርጓል፡፡ ግብ ካስተናገዱ በኃላ ወደ ማጥቃት በስፋት መሳተፍ የጀመሩት የአሰልጣኝ ዳዊት ታደለ አቃቂ ከስድስት ደቂቃዎች መመራት በኃላ የመጀመሪያ ጨዋታን ባደረገው እስማኤል አደም ጎል ወደ ጨዋታ ተመልሰዋል፡፡ አሁንም ትጋት ያልተለያቸው አቃቂዎች 63ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት በተመለሰው አጥቂው ብሩክ ሰሙ ግሩም ጎል ከመመራት ወደ መሪነት ተሸጋግረዋል፡፡

ጨዋታው በዚህ ሁኔታ ቀጥሎ 80ኛው ደቂቃ ላይ አስደንጋጭ ክስተት አስተናግዷል፡፡ የአቃቂው ተከላካይ ከድር አድማሱ ከሻሸመኔ ተጫዋቾች ጋር ኳስን ለመንጠቀም ጥረት በሚያደርግበት ወቅት ተጋጭቶ ምላሱ የመተንፈሻ አካሉን በመዝጋቱ ምክንያት ብዙዎችን ድንጋጤ ውስጥ ከቶ የነበረ ቢሆንም በርካቶች ወደ ሜዳ ገብተው ባደረጉት ርብርብ ተጫዋቹን አትርፈውታል፡፡ተጫዋቹ በወደቀበት ወቅት የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ወደ ሜዳ ገብቶ ልጁን ለማዳን ያደረገበት መልካም ተግባር የሚያስመሰግን መሆኑን በዚህ አጋጣሚ እንገልፃለን። ይሁን እንጂ በሜዳ ላይ አምቡላንስ አለመኖሩ እና ከድርጊቱ መፈፀም በኃላ የመጣበት መንገድ ሊታረም የሚገባው እና ተመሳሳይ ድርጊቶች ሊኖሩ ስለሚችሉ በተጠንቀ አምቡላንስ መኖር እንዳለበት ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡ ጨዋታውም በቀሩት ደቂቃዎች ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠር በአቃቂ 2 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

የመጀመሪያው ጨዋታ በጊዜ ባለመጠናቀቁ ከተያዘለት መደበኛ የማስጀመሪያ ሰዓት ሀያ ደቂቃ ዘግይቶ በጀመረው የሀምበሪቾ እና ካፋ ቡና ጨዋታ በአርባ አምስቱ የመጀመሪያ የጨዋታ ደቂቃዎች ኳስን በማንሸራሸራሸርም ሆነ ወደ ግብ ክልል በመድረሱ ሀምበሪቾ ዱራሜዎች የተሻሉ የነበሩ ቢሆንም ደካማ የነበረው የአጥቂ ክፍላቸው የተገኙትን መልካም አጋጣሚዎች መጠቀም አልቻሉም፡፡

ከእረፍት መልስ በቀጠለው ጨዋታ ካፋ ቡናዎች በመጀመሪያው አጋማሽ የተመለከቱትን ክፍተት ለመድፈን በአማካዩ እና አጥቂ ቦታ ላይ ተጫዋች ለውጠው ካስገቡ በኃላ ወደ ጨዋታ ቅርፅ በሚገባ መመለስ የቻሉ ሲሆን በአንፃሩ ሀምበሪቾ ዱራሜዎች የመስመር አጥቂ አስወጥተው ቢኒያም ጌታቸውን ከቀየሩ በኃላ በይበልጥ ከግብ ጋር ያላቸው ዝምድና ጠንክሯል፡፡ 53ኛው ደቂቃ ላይም ቅያሬያቸው ፍሬ አፍርቶ ከቀኝ መስመር በኩል ጋናዊው አጥቂ አትራም ኩዋሜ መሬት ለመሬት የላካትን ኳስ ቢኒያም ጌታቸው ወደ ሜዳ ከገባ ከአምስት ደቂቃ ቆይታ በኃላ ግሩም ጎል አስቆጥሮ ሀምበሪቾን ቀዳሚ አድርጓል፡፡ አሁንም ከመስመር ወደ ቢኒያም ጌታቸው በሚጣሉ ኳሶችን ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር የሞከሩት ሀምበሪቾዎች ሁለተኛ ጎላቸውን አግኝተዋል፡፡61ኛው ደቂቃ ላይ አቤኔዘር ኦቴ ከግራ አቅጣጫ የሰጠውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ቢኒያም ጌታቸው ለራሱ እና ለክለቡ ሁለተኛ ግብ አክሏል፡፡

ሁለት ጎል ካስተናገዱ በኃላ በፍጥነት ምላሽ ለመስጠት ተሻጋሪ ኳስ እና የሀምበሪቾን የመከላከል ስህተት በሚገባ ለመጠቀም የጣሩት ካፋ ቡናዎች ከቅጣት ምት ከተገኘ ኳስ ተካልኝ መስፍን በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር ካፋን ወደ ጨዋታ መልሷል፡፡ በእንቅስቃሴ የተዳከሙ ቢመስሉም ወደ ጎል ለመድረስ ያልተቸገሩት ሀምበሪቾዎች በቢኒያም እና አትራም ኩዋሜ አማካኝነት ንፁህ ዕድሎችን አግኝተው መጠቀም ግን ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ 85ኛው ላይ ግን ንስሀ ታፈሰ አምረላ ደልታታ ያመቻቸለትን ኳስ ከሳጥን ውጪ በግራ አቅጣጫ ካለ ቦታ አክርሮ መቶ በማስቆጠር ሀምበሪቾ ዱራሜ 3 ለ 1 አሸናፊ እንዲወጣ አድርጓል፡፡

የዕለቱ ሦስተኛ ጨዋታ ቤንች ማጂ ቡናን ከአዲስ አበባ ከተማ አገናኝቷል፡፡ 10፡00 በጀመረው ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ የአዲስ አበባ የበላይነት የታየበት በአንፃሩ ቤንች ማጂ ቡናዎች ጥንቃቄ የተሞላበትን ጨዋታ በመጫወት በሚያገኙት ቀዳዳ ለማጥቃት አልፎ አልፎ የሞከሩበት ነበር፡፡ ይሁንና በመስመር አጨዋወታቸው በፍፁም እና አቡበከር ፋታ የለሽ እንቅስቃሴን ሲያደርጉ የተስተዋሉት የመዲናይቱ ልጆች በተደጋጋሚ አስከፍቶ አልያም በተጫዋቾች የግል አቅም ሰብሮ ለመግባት ሙከራን አድርገዋል፡፡ ጥንቃቴ ላይ ትኩረት አድርገው በዚህኛው አጋማሽ የታዩት ቤንች ማጂዎች ሀቁምንይሁን ገዛኸኝ ከቅጣት ምት አክርሮ መቶ ሳምሶን አሰፋ ከያዘበት ኳስ ውጪ አብዛኛዎቹን ደቂቃዎች በራሳቸው የግብ ክልል አካባቢ ተቆጥበው ቆይተዋል፡፡ አዲስ አበባ ከተማዎች ጎል አስቆጥረው በገዛኸኝ በልጉዳ አማካኝነት ከጨዋታ ውጪ ከተባለች በኃላ ከማጥቃት ተቆጥበው ታይተዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ተመጣጣኝ ይመስል የነበረ ቢሆንም ግብ ለማስቆጠር አዲስ አበባ በሚገባ ተንቀሰቅሰዋል። በዚህም አቡበከር ወንድሙ ከቀኝ መስመር ከሳሙኤል የተሻማችን ኳስ በግንባር ገጭቶ ብረት ከመለሰበት ከሁለት ደቂቃ በኃላ 58ኛው ደቂቃ ላይ የግል አቅሙን በሚገባ ተጠቅሞ የቤንች ማጂ ተከላካዮች ስህተት ተጨምሮበት ጎል አስቆጥሮ አዲስ አበባን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡

ጎል ካገቡ በኃላ በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው የቀጠሉት አዲስ አበባዎች 63ኛው ደቂቃ አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ከቅጣት ምት ሲያሻማ ብዙአየው ሰይፍ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችለዋል፡፡ 67ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ ከቀኝ አቅጣጫ በግምት ከ25 ሜትር ርቀት አቡበከር ወንድሙ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሶስተኛ እጅግ አስገራሚ ጎል አግብቷል፡፡

አአ ከተማዎች ተጨማሪ ግብ የሚሆኑ ዕድሎችን ቢያገኙም የቤንች ማጂ ተነሳሽነት ይበልጥ ባየለበት የመጨረሻዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች ተጭነው በመጫወት ወደ ጨዋታ ለመመለስ ታትረዋል፡፡ ቀላል የሚባል ሙከራዎችን በወንድማገኝ ኪራ እና ጆንቴ ገመቹ ካደረጉ በኃላ ጌታሁን ገላዬ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ክለቡን ከባዶ መሸነፍ ያዳነች ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው 3 ለ 1 በሆነ ውጤት በአዲስ አበባ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ከሀምበሪቾ ጋር በእኩል አስር ነጥቦች በግብ ክፍያ በልጦ ምድብ ሀን መሪነቱን አስቀጥሏል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ