ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና ከዕረፍት መልስ አሸናፊነቱን አስቀጥሏል

የስምንተኛው ሳምንት ማሳረጊያ የነበረው የቡና እና የጅማ ጨዋታ በኢትዮጵያ ቡና 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ሁለቱ ቡድኖች ከጊዮርጊስ ጋር ካደረጓቸው የመጨረሻ ጨዋታዎች በተመሳሳይ የአንድ ተጫዋች ለውጥ አድርገዋል። በዚህም ኢትዮጵያ ቡና ከጉዳት የተመለሰው አማኑኤል ዮሃንስን በሬድዋን ናስር ቦታ ሲጠቀም ጅማ አባ ጅፋር ደግሞ በሳምሶን ቆልቻ ቦታ አብርሀም ታምራትን ተክቷል።

የተመጣጠነ እንቅስቃሴ የሚታይበት መስሎ የጀመረው ጨዋታ አፍታም ሳይቆይ እንቅስቃሴው ወደ ጅማ አባ ጅፋር ሜዳ አድልቷል። የኳስ ቁጥጥሩ በኢትዮጵያ ቡና ስር መቆየቱን ተከትሎ ጅማዎች በራሳቸው የግብ ክልል ለመቆየት ተገደዋል። በሳጥኑ ዙሪያ ክፍተቶችን ፍለጋ ኳስ ሲያንሸራሽሩ የቆዩት ቡናዎች ሙከራዎችን ለማድረግ ብዙ ደቂቃ ቢወስድባቸውም ሰብረው የገቡበት የመጀመሪያው አጋጣሚ ጎል አስገኝቶላቸዋል። በዚህም 22ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ናስር ዊልያም ሰለሞን በተከላካዮች መሐል የሰነጠቀለትን ኳስ ተጥቀሞ ከተከላካዮች አምልጦ በመግባት ጄኮ ፔንዜንም በማለፍ ጭምር ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል።

ከግቡ መቆጠር በኋላ ጅማዎች በመጠኑ ወደ ፊት ለመሄድ ጥረት የማድረግ አዝማሚያ ቢታይባቸውም የተደራጀ ጥቃት ሲሰነዝሩ አልታዩም። ቡናዎችም ቢሆኑ የኳስ ቁጥጥር ብልጫቸውን የሚመጥን ቁጥር ያላቸው የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ባይችሉም በተለይም ከዊልያም በሚነሱ ኳሶች ወደ ውስጥ ዘልቀው ለመግባት ሲጥሩ ተስተውለዋል። በሙከራ ደረጃ ግን 32ኛው ደቂቃ ላይ ዊልያም ከአቡበከር የደረሰውን ኳስ በግራ የሳጥኑ ክፍል ይዞ በመግባት ሞክሮ የሳተው እና 32ኛው ደቂቃ ላይ በግቡ አግዳሚ የተመለሰው ኃይሌ ገብረትንሳይ ወደ ግራ ያደላ ቅጣት ምት ብቻ የሚጠቀሱ ነበሩ።

ከዕረፍት ሲመለሱ ቡና መሪነቱን በጊዜ ማስፋት የሚችልበትን ቀላል ዕድል አምክኗል። 50ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ናስር ፣ አቤል እንዳለ እና ታፈሰ ሰለሞን በቅብብል የጅማን ተከላካዮች አልፈው ከግብ ጠባቂው ጋር ቢገናኙም ታፈሰ የመታው ኳስ ለፔንዜ በጣም ቀላል ሆኖለታል። በተቃራኒው ጅማዎች ወደ ቡና ሳጥን የደረሱበት የመጀመሪያው አጋጣሚ ግብ አስገኝቶላቸዋል። በዚህም ወንድሜነህ ደረጄ ሱራፌል ዐወል ላይ በሰራው ጥፋት ምክንያት የተሰጠውን ፍፁም ጣት ምት ብዙአየሁ እንዳሻው 57ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ አድርጓል። በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ጨዋታው እንደመጀመሪያው ሁሉ በቡናዎች የኳስ ቁጥጥር ቀጥሎ በስባዎቹ ደቂቃዎች መገባደጃ ላይ ከፍተኛው ጡዘት ላይ ደርሷል።

በሁለቱም ግቦች መዳረሻ ላይ ተከታታይ ክስተቶችን ያስመለከቱን ደቂቃዎች 78ኛው ደቂቃ ላይ አስራት ቱንጆ ከግራ መስመር ወደ ውስጥ አጥብቦ በመታው እና ፔንዜ ባዳነው ከባድ ሙከራ ጀምረዋል። በቀጣዩ ደቂቃ ደግሞ ጅማዎች ለማመን የሚከብዱ ሁለት ኳሶችን ወደ ውጤት መቀየር ተስኗቸዋል። በዚሁ 79ኛ ደቂቃ ብዙዓየሁ እንዳሻው ከቤካም አብደላ የደረሰውን ድንቅ ኳስ ይዞ በቀኝ በኩል ወደ ግብ ቢደርስም አገባው ተብሎ ሲጠበቅ ወደ ውጪ ልኮታል። በዚሁ ደቂቃ ንጋቱ ገብረስላሴ በቡና ተከላካዮች መዘናጋት ያገኘውን ዕድል በተክለማርያም ሻንቆ አናት ላይ አሳለፈ ተብሎ ሲጠበቅ እሱም ወደ ላይ ልኮታል።

ኢትዮጵያ ቡናዎች ከእነዚህ አስደንጋጭ ሙከራዎች በኃላ ያገኟቸውን ዕድሎች ግን በአግባቡ ተጠቅመዋል። 81ኛው ደቂቃ ላይ ዊልያም ወደፊት የላከውን ኳስ አቡበከር አመቻችቶለት ሀብታሙ ታደሰ ሲመታ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ሲመለስ መላኩ ለማውጣት ሞክሮ ኳስ ወደግብ አምርታ ድጋሚ በብረቱ ስትመለስ አግኝቶ አስራት ቱንጆ ወደ ግብነት ቀይሯታል። ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ከቀኝ የግማሽ ጨረቃው አካባቢ ኃይሌ ገብረትንሳይ ያመቻለትን ድንቅ ሆኖ የዋለው ዊልያም ሦስተኛ ግብ አድርጎታል። በመጨረሻ ደቂቃዎች የተፋፋመው ጨዋታም ሌላ የቤካም አብደላን ብቃት ያሳየ እና በተክለማርያም የተመለሰ ሌላ አስገራሚ ሙከራ አሳይቶን በኢትዮጵያ ቡና 3-1 አሸናፊነት ፍፃሜውን አግኝቷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ