የከፍተኛ ሊግ ዕለተ ሐሙስ ውሎ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ ለ እና ሐ ጨዋታዎች ዛሬ ሲካሄዱ የምድብ ለ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። አርባምንጭ ከተማ መሪ የሆነበትን ድል አስመዝግቧል። 

4፡00 ሲል ሀላባ ከተማን ከ ጅማ አባቡና አገናኝቷል፡፡ በመጀመሪያው አርባ አምስት ኳስን ይዞ በመጫወት ሀላባ ከተማዎች ተሽለው የታዩ ሲሆን ከጎል ጋር ለማድረግ የሚጥሩበት መንገድ ግን እምብዛም ስኬታማ አደለም ተጋጣሚው ጅማ አባቡና በበኩላቸው መሀል ሜዳው ላይ ያመዘነ እንቅስቃሴን ያደረጉ ሲሆን በሀላባ የሽግግር ወቅት የሚገኙ የቅብብል ስህተቶችን ሲያገኙ የተሳካ ባይሆንም ለማጥቃት ጥቂት ጥረቶች ይታይባቸው ነበር፡፡ 30ኛው ደቂቃ ላይ የአንድ ሁለት ቅብብልን መሠረት አድርገው ወደ መስመር ባደላ አጨዋወት የተገኘችን ኳስ አቡሽ ደርቤ ሲያሻማ እዩኤል ሳሙኤል ከመሀል ሾልኮ በመውጣት ጎል አስቆጥሮ ሀላባን መሪ አድርጓል፡፡

ከእረፍት መልስ በቀጠለው ጨዋታ ጅማ አባቡናዎች ተሻሽለው ወደ ጨዋታ ሪትም በሚገባ የተመለሱበት፤ ሀላባ ከተማዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ ኳስን ይዞ ከመጫወት ተሻጋሪ በሆኑ ዕድሎችን ወደ መጠቀሙ ገብተዋል፡፡ ተመሳሳይ የግብ ሙከራን በሁለቱም ክለቦች ላይ መመልከት ብንችልም አባቡናዎች የነበራቸው ተነሳሽነት እጅጉን አስገራሚ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ከመሀል ክፍሉ በሚነሱ ኳሶች ወደ አጥቂው አሸናፊ እንዳለ አድልተው ሲጫወቱ የነበሩት ሀላባ ከተማዎች በተጫዋቹ ሁለት ያለቀላቸውን ዕድሎች አግኝተው የግቡ ቋሚ ብረት መልሶበታል፡፡ በተለይ አቡሽ ደርቤ ሲያሻማ አሸናፊ እንዳለ በቀጥታ እንዳገኛት መቶ በግቡ ቋሚ ታካ የወጣበት አስቆጪ አጋጣሚ ነበረች ደቂቃው እየገፋ ሲመጣ በጨዋታ እንቅስቃሴ ብልጫን መውሰድ የጀመሩት አባቡናዎች በርካታ አጋጣሚን ቢያገኙም በአጨራረስ ድክመት ብቻ ያገኟቸውን በሙሉ እንዳይጠቀሙ አግዷቸዋል፡፡ የመጨረሻዎቹን ሀያ ደቂቃዎች ተሽለው የታዩት ቡናማዎቹ ተሳክቶላቸው መደበኛ የጨዋታው ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ አንድ ብቻ ሲቀረው ሱራፌል ፍቃዱ እጅግ ግሩም ጎል ከመረብ አዋህዶ ቡድኑን አቻ አድርጓል፡፡ ጨዋታው በዚሁ ተጨማሪ ጎል ሳይታይበት 1 ለ 1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል፡፡ 

የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በሶዶ ከተማ እና ጋሞ ጨንቻ መካከል የተደረገ ነበር፡፡ ብርቱ ፉክክር በታየበት በዚህ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ወላይታ ድቻዎች ረጃጅም ኳሶችን ወደ ማጥቃት ወረዳው በመላክ ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል ለመድረስ የሞከሩበት ጋሞ ጨንቻዎች ከመስመር በሚነሱ ተሻጋሪ ኳሶች የማጥቂያ መንገዳቸውን አድርገዋል፡፡ ከእንቅሴቃሴ በዘለለ ብዙም የጠሩ ዕድሎችን መመልከት ያልቻልንበት ጨዋታ ቀጥሎ አጨዋወታቸው በዚህ መልኩ ይሁን እንጂ ጋሞ ጨንቻዎች በተወሰነ መልኩ ወደ ግብ በመድረሱ ሻል ያሉ ነበሩ፡፡ 33ኛው ደቂቃም ተሳክቶላቸው ለገሰ ዳዊት ከቀኝ በኩል የሰጠውን ኳስ አሸናፊ ተገኝ ከመረብ አዋህዶ የውድድር ዓመቱ ሦስተኛ ጎሉን አስቆጥሮ ክለቡን መሪ አድርጓል፡፡ በቀሩትም ደቂቃዎች ምንም የተለየ ነገርን መመልከት ሳንችል ወደ መልበሻ አምርተዋል፡፡

ከእረፍት መልስ በቀጠለው ጨዋታ ሶዶ ከተማዎች የተሻለ ቅርፅን ይዘው የገቡ ሲሆን ጋሞ ጨንቻዎች ያስቆጠሯትን ጎል አስጠብቆ ለመውጣት በሚመስል አጨዋወት ሜዳ ላይ ቀርበዋል፡፡ እስከ 70ኛው ደቂቃ ድረስ የግብ አጋጣሚን ሳንመለከት ከተጓዝን በኃላ በዚህኛው ደቂቃ ላይ ግን ሶዶ ከተማዎች ከነበራቸው ብልጫ መነሻነት ባደረጉት ፈጣን ሽግግር ጎል አስቆጥረዋል ካለፉት ጨዋታዎች ዛሬ ቀዝቀዝ ብሎ ለደቂቃዎች የቆየው ፈጣኑ የመስመር ተጫዋች ሰለሞን ግታቸው ከቀኝ አቅጣጫ ያሻገረለትን ኳስ ዳግም ማቲዮስ ወደ ጎልነት ለውጧት ቡድኑን አቻ ወደ አቻ ውጤት አሸጋግሯል፡፡ በቀሪዎቹ ደቂቃዎች በሜዳ ላይ በነበረው ከፍተኛ ውጥረት የተነሳ ተጫዋቾች በሚሰሩት አላስፈላጊ ጥፋት ሁለት ቀይ ካርዶችን ተመልክተናል፡፡ 72ኛው ደቂቃ ላይ የጋሞ ጨንቻው መኮንን መና ከኳስ ንክኪ ውጪ የሶዶ ከተማውን ጥላሁን ቦቱን በመማታቱ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል፡፡ ጋሞ ጨንቻዎች በአሸናፊ ተገኝ እንዲሁም ሶዶዎች የመሀል ክፍሉ ላይ በፈጠሩት ድንቅ ጥምረት ለቡድኖቻቸው መልካም እንቅስቃሴ ማድረግ ቢችሉም ውጤታማ ሊያደርጎቸው ግን አላስቻሉም፡፡ 86ኛው ደቂቃ ላይ የሶዶ ከተማው የመስመር አጥቂ ሰለሞን ጌታቸው በደሳለኝ አሎ ላይ በሰራው አደገኛ አጨዋወት በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል፡፡ በተቀሩት ደቂቃዎች ምንም ጎል ሳንመለከት ጨዋታው 1 ለ 1 ተጠናቋል፡፡
የምድብ ለ የሁለተኛ ቀን የመጨረሻ ጨዋታ ውጥረቶች የበዙበት የነቀምት ከተማ እና ኢኮስኮ ጨዋታ በተጋጋለ የተጫዋቾች የዕርስ በዕርስ ሽኩቻዎች ታጅቦ ገና ከጅምሩ የቀጠለ ነበር፡፡በመጀመሪያው አጋማሽ በተደጋጋሚ በሚሰሩ ጥፋቶች ሲቆራረጥ ኳሱ የተስተዋለበት ከሜዳ ላይ እንቅስቃሴዎች ይልቅ ጩኸቶች በርክቶ የታየበት ከዚህ ባለፈ የዕለቱ ዳኛ ጨዋታውን ለማረጋጋት ያደረጉበት ጥረት ደካማ የነበረበትን ክስተት አስመልክቶናል፡፡ አምስተኛው ደቂቃ ላይ በቦካ ቦና አማካኝነት ነቀምት ከተማዎች ግብ ያስቆጥራሉ ሆኖም የመስመር ዳኛው ከጨወታ ውጪ ነው በሚል ግቧን በመሻራቸው የነቀምት ከተማ ተጫዋቾች ዳኛው ላይ ከፍተኛ ተቃውሞን አሰምተዋል፡፡ በተለይ አምበሉ ዘነበ ተንታ ከዳኛው ጋር በተደጋጋሚ አላስፈላጊ ንግግሮች ሲያደርግ የነበረበት መንገድ ሊደገም የማይገባ እና እጅጉን የጨዋታውን መንፈስ የለወጠበት ነበር፡፡

በአጥቂው የኃላሸት ሰለሞን ላይ ያነጣጠረው የኢኮስኮ የጨዋታ እንቅስቃሴ በተደጋጋሚ የነቀምትን የተከላካይ ክፍል ስህተት በመጠቀም ወደ ጎል ለመቅረብ የታተሩበት ነበር፡፡ 18ኛው ደቂቃ ላይ የዕለቱን ዋና ዳኛ ቅሬታ በአላስፈላጊ ሁነቶች ሲገልፁ የነበሩት ነቀምቶች ተጠባባቂ ወንበር ላይ የተቀመጠው አጥቂውን ኢብሳ በፍቃዱ የዳኛን ውሳኔ በቃላት በመግለፁ የዕለቱ አራተኛ ዳኛ ለዋና ዳኛው ባቀረቡት አቤቱታ መነሻነት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል፡፡

ጨዋታው አሰልቺነቱ እንዳለ ሆኖ ነቀምቶች ቀዳዳ ፍለጋ በሚመስል መልኩ ረጃጅም ኳሶች ላይ ባደረጉት አጨዋወት በተለየ መልኩ ቦካ ቦና ከመሀል ሾልኮ በመውጣት በመጠቀም ሙከራዎችን ሲያደርግ አስተውለናል፡፡ 36ኛው ደቂቃ ላይ ከሚል ረሺድ ከማዕዘን ሲያሻማ ኳሷ አቅጣጫዋን ቀይራ ወደ ጎል ስትሄድ አላዛር መርኔ እንደምንም አውጥቷታል፡፡ የነቀምት ነቅሎ መጫወት ያስተዋሉት ኢኮስኮዎች 42ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አስቆጥረዋል፡፡ የነቀምት ተከላካዮች መዘናጋት ተደምሮ ቤዛ መድህን ከግራ አቅጣጫ በፍጥነት የላከውን ኳስ የኃላሸት ሰለሞን በድንቅ አጨራረስ ወደ ጎልነት ቀይሮታል፡፡ በሌላ አጋጣሚ ከክፍት የጨዋታ ፍሰት የኃላሸት በድጋሚ ያገኘውን ዕድል መጠቀም ሳይችል ቀርቷል፡፡ መደበኛው የመጀመሪያ አርባ አምስት ሊጠናቀቅ ጭማሪ ደቂቃ እየቀረው ከቀኝ የኢኮስኮ የግብ አቅጣጫ የተገኘውን የቅጣት ምት ከሚል ረሺድ በቀጥታ ወደ ጎል አክርሮ ሲመታ ጉቱ መላኩ ነካ በማድረግ ወደ ጎል ቀይሮት ነቀምት 1 ለ 1 ማድረግ ችሏል፡፡

ከመጀመሪያው አጋማሽ አሰልቺ እና ያልተገቡ አጨዋወቶች ተቆጥቦ በቀጠለው ሁለተኛ አርባ አምስት ነቀምት ከተማ በአንፃራዊነት ቶሎ ቶሎ ተጋጣሚን በማስጨነቁ የተዋጣላቸው ቢሆኑም ለሚያገኞቸው ግልፅ ዕድሎች ግን የአጨራረስ ክፍተት ዋጋ ያስከፈላቸው ነበር። መስመር በሚነሱ ፈጣን ተጫዋቾቻቸው እየታገዙ አስጨናቂነታቸውን የቀጠሉት ነቀምቶት በብሩክ ብርሀኑ እና ከሚል ረሺድ አማካኝነት ያለቀላቸውን ንፁህ ዕድሎች ሳይጠቀሙበት ቀርተውታል፡፡ በኃላሸት ፍቃዱ ላይ አነጣጥረው ሲጫወቱ የታዩት ኢኮስከኮዎች በአጥቂው አማካኝነት ሁለት አስቆጪ ዕድሎችን አግኝተው አልተጠቀሙም። የመጨረሻ አስር ደቂቃዎችን ነቀምቶች በተደጋጋሚ ወደ ኢኮስኮ የግብ ክልል መድረስ ቢችሉም የማሸነፊያ ግባቸውን ማግኘት ሳይችሉ ጨዋታው 1 ለ 1 ተጠናቋል፡፡

ምድብ ሐ

አምስተኛ ሳምንት በደረሰው የምድብ ሐ ዛሬ ሦስት ጨዋታዎችተደረጉ ሲሆን ኮልፌ ቀራኒዮ ነገሌ አርሲን 5-0 በመርታት የእለቱን ከፍተኛ ድል አስመዝግቧል። አንዋር ዳባ በመጀመርያው ደቂቃ ቡድኑን ቀዳሚ ሲያደርግ ሀይከን ዳዋሙ ሦስት ጎሎች አስቆጥሮ ሐት-ትሪክ መስራት ችሏል። ሮቤል ጥሃላሁን የቀሪዋ ጎል ባለቤት ነው።

ቡታጅራ ከተማ ኢትዮጵያ መድንን 2-1 አሸንፏል። አብዱራዝቅ ቃሲም እና ሙሪድ እንድሪስ ለቡታጅራ ሲያስቆጥሩ መሀመድኑር ናስር የመድንን ጎል አስቆጥሯል።

አርባምንጭ ከተማ ጌዴኦ ዲላን 2-0 ማሸነፍ ችሏል። አሸናፊ ኤልያስ እና ማርቲን ኡጅላ የአዞዎቹ የድል ጎሎችን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው።


© ሶከር ኢትዮጵያ