ሪፖርት | የሳሊፉ ፎፋና ጎል ሆሳዕናን ወደ ድል መልሷል

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ስምንተኛ ሳምንት ድሬዳዋ ከተማን ከሀዲያ ሆሳዕና ያገናኘው የረፋድ መርሐ ግብር በሆሳዕና 1-0 አሸናፊነት ተደምድሟል። 

ሀዲያ ሆሳዕና ባለፈው የጨዋታ ሳምንት በፋሲል ከነማ የዓመቱ የመጀመርያ ሽንፈት ከገጠመው ስብስብ መካከል ካሉሻ አልሀሰን ፣ ሚካኤል ጆርጅ እና ተስፋዬ በቀለን በማሳረፍ አዲስ ህንፃ ፣ ቢስማርክ አፒያ እና ሳሊፉ ፎፋና ወደ አሰላለፍ ተመልሰዋል። በድሬዳዋ በኩች በሲዳማ ሽንፈት ካስተናገደው ስብስብ አራት ተጫዋቾች ለውጥ ተደርጎ ዘነበ ከበደ፣ ፍሬዘር ካሣ፣ ኩዌኩ አንዶህ እና አስጨናቂ ሉቃስ ገብተው ፍቃዱ ደነቀ፣ በረከት ሳሙኤል፣ ሄኖክ ኢሳይያስ እና ሱራፌል ጌታቸው አርፈዋል።


ጎል ከጅምሩ ባስተናገደው ጨዋታ ሀዲያ ሆሳዕና መሪ የሆነበትን ጎል በአራተኛው ደቂቃ ላይ አግኝቷል። ከሆሳዕና የሜዳ አጋማሽ በረጅሙ የተላከውን ኳስ ሳሊፉ ፎፋና ከድሬዳዋ ተከላካዮች ጋር ታግሎ በማሸነፍ ጎሉን ለቆ በወጣው ፍሬው ጌታሁን መረብ ላይ አሳርፎ ነብሮቹን መሪ አድርጓል።
ጨዋታው ከጎሉ በኋላ ጥሩ ፉክክር እንደሚታይበት ቢጠበቅም የተቀዛዘቀ ይልቁንም በርካታ ጥፋቶች እና የጨዋታ ውጪ አቋቋሞች የበዙበት ሆኖ አልፏል። ከቆሙ ኳሶች ከሚገኙ አጋጣሚዎች ውጪም በሁለቱም ቡድኖች በኩል ይህ ነው የሚባል የጠራ እድል ከክፍት ጨዋታ ሳይፈጠር የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል።

የተሻለ የጎል ሙከራ ባስተናገደው ሁለተኛው አጋማሽ ድሬዳዋ ከተማዎች ኳስ በመቆጣጠር ለማጥቃት ቢሞክሩም ዕድሎች መፍጠር የተሳናቸው ሲሆን በአንፃሩ ሆሳዕናዎች ጥሩ ጥሩ ሙከራዎች በመሌሶ ማጥቃት ፈፅመዋል። በ50ኛው እና 61ኛው ደቂቃ በተመሳሳይ ሒደት ከቀኝ የሳጥኑ ክፍል ዳዋ ሆቴሳ አክርሮ መትቶ ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣበት ሙከራዎች፣ በ53ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ ሳሊፉ ፎፋና በግንባሩ ገጭቶ ወደ ውጪ የወጣበት እና በጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ተቀይሮ የገባው ሚካኤል ጆርጅ በሁለት አጋጣሚዎች ያደረጋቸው ሙከራዎች ነብሮቹ ተጨማሪ ጎል ሊያስቆጥሩባቸው የሚችሉባቸው ዕድሎች ነበሩ።

ከመጀመርያው አጋማሽ በባሰ መልኩ ጥፋቶች በበረከቱበት በዚህ አጋማሽ ስምንት የማስጠንቀቂያ ካርዶች ተመዘውበት በጅምሩ የተቆጠረችው ጎል ላይ ለውጥ ሳይታይ ጨዋታው በሀዲያ ሆሳዕና 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ