የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ስምንተኛ ሳምንት ጨዋታዎችን በመመርኮዝ ይህንን የምርጦች ቡድን ሰርተናል።
አሰላለፍ 4-3-3
ግብ ጠባቂ
ሚኬል ሳማኬ – ፋሲል ከነማ
በጨዋታ ሳምንቱ ብዙ ጫና ደርሶባቸው የተለየ ብቃት ያሳዩ ግብ ጠባቂዎች ባይኖሩም የፋሲሉ ሳማኬ ኮከብ ለመሆን በቂ እንቅስቃሴ አድርጓል። ግብ ጠባቂው አዳማን ቀዳሚ ሊያደርግ ይችል የነበረውን የቅርብ ርቀቱን የአብዲሳ ጀማልን ሙከራ ያዳነበት እንዲሁም በመጨረሻ ደቂቃ የተገኘው ፍፁም ቅጣት ምት በፍሰሀ ቶማስ ሲመታ ያመከነበት መንገድ በጨዋታው ላይ የነበረውን ተፅዕኖ ያሳያሉ።
ተከላካዮች
እንየው ካሣሁን – ፋሲል ከነማ
የቀኝ መስመር ተከላካዩ እንየው የሰዒድ ሁሴንን ጉዳት ተከትሎ ባገኘው የመሰለፍ ዕድል እስካሁን ጥሩ ብቃት ሲያሳይ ቆይቷል። ቡድኑ አዳማን በገጠመበት እና አራት ግቦች ባስቆጠረበት ጨዋታ ደግሞ ከፍተኛ የማጥቃት ተሳትፎው ውጤት ታይቷል። ፋሲል በእንየው እንቅስቃሴ መነሻነት ሁለት ፍፁም ቅጣት ምቶችን ሲያገኝ የናትናኤል ጎል እንዲቆጠርም የመስመር ተከላካዩ ድርሻ በግልፅ የሚታይ ነበር።
ላውረንስ ላርቴ – ሀዋሳ ከተማ
ባለፈው የጨዋታ ሳምንት በማማዱ ሲዲቤ እየተመራ አስፈሪ እንቅስቃሴ ያደረገውን የሲዳማን የፊት መስመር መቆጣጠር ቀላል አልነበረም። ጋናዊው የመሀል ተከላካይ በዙሪያው ካሉ የቡድን አጋሮቹ ጋር ሆኖ በልበ ሙሉነት ሲያደርገው የነበረው እንቅስቃሴ ግን ሀዋሳን ረድቶታል። በተለይም 72ኛው ደቂቃ ላይ ከአበባየሁ ዮሃንስ የተነሳውን ኳስ ያቋረጠበት መንገድ ሀዋሳን ወደ አቻ ውጤት እና ወደ ጫና ከመግባት የታደገ ነበር።
ቴዎድሮስ በቀለ – ሀዲያ ሆሳዕና
የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ቡድን ባለፈው ሳምንት ሦስት የመሀል ተከላካዮችን ሲጠቀም ወደ አሰላለፍ የተመለሰው ቴዎድሮስ በዚህም ሳምንት ሙሉ ጨዋታ አድርጓል። ግዙፉ ተከላካይ ከአይዛክ ኢሲንዴ ጋር ድንቅ ጥምረትን በመፍጠር የድሬዳዋ አጥቂዎች በርካታ የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን እንዳያገኙ ኳሶችን ያፀዳ የነበረበት መንገድ ሀዲያ ሆሳዕና በጊዜ ያገኘውን የአንድ ግብ መሪነት ጠብቆ እንዲወጣ አስችሎታል።
አሥራት ቱንጆ – ኢትዮጵያ ቡና
አስራት ቡድኑ ጅማ አባ ጅፋርን በረታበት ጨዋታ በማጥቃት ላይ የነበረው ተሳትፎ ለቡድኑ ውጤት ቀጥተኛ አስተዋፅዖ አድርጓል። በፈጣን ሽግግር በተገኘው የመጀመሪያ ጎል የግቡን እንቅስቃሴ ከተጋጣሚ ኳስ በመቀማት ሲያስጀምር ሁለተኛውን ግብ ደግሞ ራሱ አስቆጥሯል። ጃኬ ፔንዜ በድንቅ ሁኔታ አዳነበት እንጂ አስራት ሁለተኛ ግብም ለማስቆጠር ተቃርቦ ነበር።
አማካዮች
ተስፋዬ አለባቸው – ሀዲያ ሆሳዕና
በተክለ ቁመናው ከርቀት የሚለየው ተከላካይ አማካዩ ከጉዳት ነፃ ሆኖ ለተከታታይ ሳምንታት በወጥነት ቡድኑን እያገለገለ ይገኛል። ተስፋዬ ሀዲያ ሆሳዕና በድሬዳዋ ለብዙ ደቂቃዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ተወስዶበት በነበረባቸው ደቂቃዎች የተጋጣሚን አማካዮችን በመቆጣጠር ተፈላጊውን በቂ ሽፋን ለተከላካይ ክፍሉ በመስጠት የድሬ ኳስ መያዝ ፍሬ እንዳያፈራ አድርጎ ውጤት አስጠብቆ የመውጣቱን ሂደት አግዟል።
ዊልያም ሰለሞን – ኢትዮጵያ ቡና
ወጣቱ አማካይ በሁሉም ረገድ የጨዋታው ኮከብ የሚያስብለውን እንቅስቃሴ መከወን ችሏል። አንድ ግብ አስቆጥሮ አንድ ደግሞ ለአቡበከር ያመቻቸው ዊልያም የአስራት ጎል የተቆጠረበት የጨዋታ ሂደትም ከእሱ እግር ስር የተነሳ ነበር። ከግቦቹ ውጪም በቀሪው የጨዋታ ጊዜ ተጨዋቹ የነበረው የቅብብል ስኬት እና ታታሪነቱ ቀልብ የሚስብ ነበር።
ፍፁም ዓለሙ – ባህር ዳር ከተማ
የባህር ዳሩ የልብ ምት ፍፁም ተቀዛቅዞ ከነበረባቸው ጥቂት ጨዋታዎች በኋላ ራሱን ሆኖ የታየበትን የሁለተኛ አጋማሽ እንቅስቃሴ በሰበታው ጨዋታ አሳይቷል። ወሳኟን የቡድኑን አቻነት ግብ ያሬድ ሀሰን በራሱ መረብ ላይ እንዲያስቆጥር መነሻ የነበረው ፍፁም ሁለተኛውን ግብ ደግሞ ለሳለምላክ ተገኝ አመቻችቶ ማቀበል ችሏል።
አጥቂዎች
ኤፍሬም አሻሞ – ሀዋሳ ከተማ
ባሳለፍነው ሳምንት ተቀይሮ ገብቶ ግብ ያስቆጠረው ኤፍሬም በዚህ ሳምንት ደግሞ በጫና ውስጥ ሆኖ ለብሩክ በየነ ግብ ጥሩ ኳስ ማመቻቸት ችሏል። ራሱም ለማስቆጠር ተቃርቦ በግቡ ብረት የተመለሰበት ኤፍሬም በድኑ 1-0 እየመራ በዘለቀባቸው ረጅም ደቂቃዎች በታታሪነት የሲዳማን የመስመር እንቅስቃሴ ለመግታት ከፍ ያለ የመከላከል ተሳትፎም ነበረው።
ብሩክ በየነ – ሀዋሳ ከተማ
ትክክለኛው ቦታ ላይ በመገኘት እና ድንቅ ጨረሽ መሆኑን ያሳየበትን የዓመቱን አራተኛ ግብ አስቆጥሮ ሀዋሳን በጊዜ መሪ ያደረገው ብሩክ ከመስፍን ታፈሰ ጋር ጥሩ ጥምረት በማሳየት እንደወትሮው በታታሪነት አሳልፏል። በተለይም ሁለት የሲዳማ ተከላካዮችን ጥሎ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ተቃርቦ የነበረበት ቅፅበት በመሳይ አያኖ ባይከሽፍ ቀኑ ከዚህም በላይ በደመቀለት ነበር።
ምንይሉ ወንድሙ – ባህር ዳር ከተማ
ተቀይሮ በመግባት በብዛት ከመስመር እየተነሳ አልፎ አልፎ ደግሞ መሀል ላይ ሆኖ እንዲያጠቃ ይደረግ የነበረው ምንይሉ የባዬን ጉዳት ተከትሎ በብቸኛ አጥቂነት ጨዋታውን ጀምሯል። ዕድሉን በአግባቡ በመጠቅመ የሰበታን ተከላካዮች እንቅስቃሴ ሲረብሽ ቆይቶም የቡድኑን ሦስተኛ ግብ ከሳጥን ውጪ መትቶ ከመረብ ሲያገናኝ ግርማ ዲሳሳ ያስቆጠረው ፍፁም ቅጣት ምትም የተገኘው ምንይሉ ላይ በተሰራ ጥፋት ነበር።
አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ – ፋሲል ከነማ
በድቻ እና በባህር ዳር ጨዋታ ቡድኑ ባሳየው አቋም ጫና ውስጥ ገብተው የነበሩት አሰልጣኝ ስዩም ሦስት ተከታታይ ድል ማስመዝገብ ችለዋል። በዚህ ሳምንት አዳማን ሲገጥሙም በአንድ ግብ ሊገደብ ይመስል የነበረውን ቡድን ለውጦችን በማድረግ በተረጋጋ ሁኔታ ጨዋታውን ጉልበት ሳያባክን በሰፊ የግብ ልዩነት እንዲያሸንፍ አድርገዋል።
ተጠባባቂዎች
ሜንሳህ ሶሆሆ – ሀዋሳ ከተማ
አይዛክ ኢሲንዴ – ሀዲያ ሆሳዕና
ደስታ ዮሐንስ – ሀዋሳ ከተማ
ሀይደር ሸረፋ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
አማኑኤል ጎበና – ሀዲያ ሆሳዕና
አቡበከር ናስር – ኢትዮጵያ ቡና
ሳላሀዲን ሰዒድ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
© ሶከር ኢትዮጵያ