የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በቀጣይ መጋቢት መጨረሻ ለሚኖረው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣራያ የጅማ የዝግጅት ቆይታ አስመልክቶ አሰልጣኞቹ ዝርዝር መረጃ ሰጥተዋል።
የዋልያዎቹ ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ እንዲሁም ረዳቶቻቸው ዐንዋር ያሲን፣ አሥራት አባተ እና የግብጠባቂ አሰልጣኝ ደሳለኝ ገብረ ጊዮርጊስ በተገኙበት የዛሬው ከሰዓት የወሎ ሰፈር ጋዜጣዊ መግለጫ በዋናነት ያተኮረው የሦስት ቀን የጅማ የብሔራዊ ቡድኑ ቆይታ ዙርያ ነበር።
የዋልያዎቹ አለቃ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በመክፈቻ ንግግራቸው “ወደ ጅማ ዝግጅት ለማድረግ ከመሄዳችን በፊት ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠት ያልቻልነው በተለያዩ ምክንያቶች ያልተሟሉ ነገሮች ስለነበሩ ዘግይተን በመሆኑ በመጀመርያ በፌዴሬሽኑም በራሴም ስም ይቅርታ እንጠይቃለሁ። በቀጥታ ወደ ጅማ ዝግጅት ሳመራ በኢትዮጵያ እግርኳስ ያልተለመደ እንግዳ የሆነ የብሔራዊ ቡድን ዝግጅት ይዘን ነው የመጣነው። በዚህም የተነሳ በሚዲያዎች ‘እንዲህ ያለ ዝግጅት ለምን አስፈለገ? ገና ሁለት ወር ለቀረው ጨዋታ እንዴት ከወዲሁ ይጠራል?’ የሚል ስለነበር ለዛ መልስ የሚሰጥ ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።” ብለዋል።
በማስከተል ሁሉንም አዲስ አበባ የነበሩ ጨዋታዎችን እንደተከታተሉ እና በየቦታው የሚመጥኑ 28 ተጫዋቾችን ጥሪ እዳደረጉ ከነዚህ መሐል 20 ነባር እና 10 አዲስ ተጫዋቾች መጠራታቸውን ተናግረው በጅማ ዝግጅት 20 ተጫዋቾች እንደተገኙና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ስድስት ከሌላ ክቦች ሁለት ተጫዋቾች እንዳልተገኙ ገልፀዋል። ለሦስት ቀን በጅማ ቆይታቸው በንድፈ ሀሳብ እና በሜዳ ላይ ተግባራት የቡድን ግንባታን አስመልክቶ ጥሩ ቆይታ ማድረጋቸውን አብራርተዋል።
በመቀጠል አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ያልተለመደ የብሔራዊ ቡድን ዝግጅትን ለመጀመር ያበቃቸው ምክንያት የክለብ አሰልጣኝ በነበሩበት ወቅት የብሔራዊ ቡድን ዝግጅት በዚህ መልክ ቢሆን ብለው የሚያስቡትን በግል የፌስቡክ ገፃቸው የግል ምልከታቸውን ከስድስት ዓመት በፊት እንደፃፉ አስታውሰው አብራርተዋል።
” ከዚህ ቀደም ለብሔራዊ ቡድኑ ዝግጅት ፕሪምየር ሊጉ ለአርባ ቀን፣ ለሁለተኛ ጊዜ ደግሞ ለአርባ አምስት ቀናት እንዲቋረጡ ተደርጓል። ይህ እንደ አሰልጣኝ ቡድን ለማዘጋጀት የሊጉን ውድድር የፉክክር ስሜቱን ጠብቆ እንዲሄድ ክለቦች ከሚያወጡት በጀት አንፃር ተጫዋቾች ላይ ከሚደርሰው ጉዳት በአጠቃላይ ከብዙ ነገር ከማየት ዝግጅቱን በዚህ መልክ ማድረግ አይቻልም ወይ? በማለት የሊጉ ውድድር ሳይቋረጥ ጊዜ ሳይባክን ብሔራዊ ቡድን በአጭር ቀናት ማዘጋጀት ለምን አይቻልም የሚል ፅሑፍ ፅፌ ነበር። ወደዚህ ኃላፊነት ስመጣ ያን ሳስብ የነበረውን ነገር ለመተግበር ማዕከል ያደረገ የሦስት ቀን ዝግጅት በጅማ እንዲዘጋጅ ማድረግ የተቻለው። ያም ብቻ ሳይሆን ዲኤስ ቲቪ ሊጉን ስለገዛው ብድግ ብሎ ማቋረጥ ስለማይቻል በሚገኙ ክፍተቶች የብሔራዊ ቡድን ዝግጅት ለማድረግ ጠርተናል።
” ይህ የአጭር ጊዜ ዝግጅት ጠቀሜታው ለተጫዋቾቹ የብሔራዊ ቡድን ዲሲፕሊን ኮድ ለማስተማር፣ አዲስ የተጠሩ ተጫዋቾች እንዲነቃቁ፣ ሊጉ ሳይቋረጥ እንዲቀጥል፣ ባለመቋረጡ ደግሞ ክለቦች እንዲያተርፉ፣ ከዚህ ቀደም ተጠርተው አሁን ያልተካተቱ ተጫዋቾች ደግሞ እንዲነሳሱ ለማድረግ እና ራሳቸውን መለስ አድርገው እንዲያዩ ጥቅሙ የጎላ ነው። ”
አሰልጣኝ ውበቱ በቀጣይ ከጥር ወር መጨረሻ በኃላ ሊጉ ለተወሰኑ ቀናት ሲቋረጥ የአምስት ቀን ዝግጅት ተደርጎ በመጨረሻም ከማዳጋስካር ጨዋታ አስቀድሞ የአስራ ሦስት ቀን የዝግጅት ጊዜ እንደሚኖር በዚህም መሐል የአቋም መለኪያ ጨዋታ እንደሚኖር ተናግረዋል።
በማስከተል ከጋዜጠኞች የተለያዩ ጥያቄዎች የቀረቡ ቢሆንም በዋናነት ዝግጅት ያለ ጨዋታ ማድረግ፣ የፊፋ ህግ ጨዋታዎች ከሌሉ በቀር ክለቦች ተጫዋቾቻቸውን እንዳይልኩ አይገደዱም በዚህ በኩል ያጋጠማቹ ችግሮች አሉ ወይ? እና በቀጣይ አሁን ያጋጠማችሁ ክፍተት በቀጣይ እንዳይኖር ምን ለመሥራት አስባችኋል? የሚሉ ጥያቄዎች ተጠይቀው ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል።
“የዝግጅት መጨረሻው ጨዋታን ማድረግ ነው። ጨዋታ ከሌለው ትርጉም የለውም። ያንን ለማድረግ ለጊዜው የተመቻቸ ነገር አልነበርም። ምክንያቱም ዘግይተን ነው ጥሪ ያደረግነው። ተጫዋቾቹ በሦስት ቀን አንዴ ጨዋታ እያደረጉ ነው የመጡት። ጉዳት ሊያስተናግዱ ቢችሉ በተጨማሪ የሊጉ ጨዋታ በቅርብ ቀናት የሚኖር በመሆኑ አላስፈላጊ ኃላፊነት ላለመውሰድ ከዚህ አንፃር ጨዋታ አላደርግንም። በቀጣይ ግን መካተት ግድ የሚለው ነው። ዋናው የብሔራዊ ቡድነ መንፈስ በተጫዋቾቹ ላይ የማስረፅ የደረግነው አላማችን የተሳካ ነበር። ያልተለመደ ነገር ማምጣታችን በራሱ የፈለገ ሙሉ ቢሆን ክፍትት ማምጣቱ የማይቀር ነው።
“የፊፋ ካላንደር ተነስቷል። የሚገርመኝ ከዚህ ቀደም አርባ ቀን አርባ አምስት ቀን ሊጉን በውድድር መሐል ሲዘጋ ሲቋረጥ የት ነበርን። ለኔ ቀላሉ ነገር በአንድ ደብዳቤ የሠላሳ ቀን ዝግጅት ይሰጠኝ ብዬ መጠየቅ እችል ነበር። ግን እኔ በፊት የክለብ አሰልጣኝ በነበርኩበት ወቅት እናገር የነበረውን ችግር አርሜ በትክክለኛው መንገድ ዛሬ መተግበር ካልቻልኩኝ ምንድነው ትርጉሙ። እኛ ፊፋ የሚለውን አንዱን ተግብረን እናውቃለን? እኛ በውድድር መሐል ልጆች ሳይጎዱ ክለቦች ተጨማሪ ወጪ ሳያወጡ ውድድር ሳይቋረጥ ታክቲካል ልምምድ ማድረጋችን ምንድነው ችግሩ? ስለዚህ ይህ በጎ ጅምራችን ሊደነቅ ሊደገፍ ይገባል።
“ቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾቹን ሳይልክ ቀርቷል። ይህን ከክለቡ አመራሮች ጋር ተነጋግረን በመጨረሻም ሁኔታውን ተረድተዋል። ጥሩ መግባባት አድርገናል። ያው ያልተለመደ አዲስ ነገር ስለሆነ መጀመርያ ያለመረዳት ሊኖር ይችላል። በመጨረሻም በጅማ ዝግጅታችን በርካታ ነገር አትርፈንበታል። ይህ ነገር መበረታታት መለመድ አለበት።
© ሶከር ኢትዮጵያ