ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሁንም የሚቀመስ አልሆነም

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ስምንተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ቀዳሚ በነበረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና አዳማ ከተማ ጨዋታ በንግድ ባንክ 5 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ 

በሊጉ ሻምፒዮን የመሆን ዕድልን ያገኙት ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም ሲገናኙ ጠንካራ ፉክክር የሚታይበት ጨዋታ የነበረ ቢሆንም የዛሬው ጨዋታ ግን የንግድ ባንክ የበላይነት ታይቶበታል፡፡በመጀመሪያው አርባ አምስት ተመጣጣኝ የሚባል የጨዋታ መንገድን በሁለቱም ክለቦች መካከል መመልከት ብንችልም በቀኝ መስመር በአረጋሽ ካልሳ እና በመሀል ሜዳ ጥበበኛዋ ሰናይት ቦጋለ አስደናቂ ብቃት ወደ ፊት ተሰላፊዎቹ ረሂማ እና ሎዛ በመጣል የተገኙ ዕድሎችን ለመጠቀም ጥረትን አድርገዋል፡፡ በአንፃሩ አዳማ ከተማዎች ወጥነት አይኑራቸው እንጂ አልፎ አልፎም ቢሆን በምርቃት ፈለቀ ታጋይነት በሚገኙ ኳሶች ወደ ፊት ለመሄድ ቢታትሩም ቡድኑ ላይ ሁነኛ አጥቂ ያለመኖሩ ኃላ ላይ ለንግድ ባንክ ተነሳሽነትን የጨመረ ሆኗል፡፡

ረሂማ ዘርጋው እና ሎዛ አበራ በተደጋጋሚ ካደረጉት ጫና መነሻነት የአዳማን ተከላካይ ወደ በማስከፈት ወደ ጨዋታ ለመግባት ሞክረዋል፡፡ረሂማ ዘርጋው ጎል አስቆጥራ ከጨዋታ ውጪ ከተባለባት ሁለት ደቂቃዎች በኃላ ማለትም 36ኛው ደቂቃ ገደማ ከቀኝ መስመር በረጅሙ ሎዛ አበራ ወደ ግብ ክልል ስታሻግር ረሂማ በግንባር ገጭታ በማስቆጠር ቡድኗን መሪ አድርጋለች፡፡አሁንም በተሻለ አቀራረብ በማጥቃቱ የተዋጣላቸው ባንኮች ከመጀመሪያው ጎል መቆጠር በኃላ አራት ደቂቃዎች እንደተቆጠሩ ከቀኝ የአዳማ የግብ ክልል ወደ መስመር ባደላ ቦታ አረጋሽ ካልሳ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ምት በግምት ከ35 ሜትር ርቀት ሎዛ አበራ መታው ከመረብ አሳርፋ የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት አሳድጋለች፡፡ በቀሩት ደቂቃዎች አዳማዎች ኳስን በማንሸራሸር ብቻ ቢጫወቱም ወደ ጎል ለመድረስ የነበራቸው ደካማ ውሳኔ 2 ለ 0 እየተመሩ ወደ መልበሻ ክፍል እንዲያመሩ ሆኗል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ንግድ ባንኮች ተጨማሪ ጎሎችን ለማስቆጠር ከመስመር በሚነሱም ሆነ ከመሀል ሜዳ በቅብብል ከሚገኙ አጋጣሚዎችን ሲፈጥሩ የተስተዋለበት ነበር፡፡ አዳማ ከተማዎች በበኩላቸው ወደ ጨዋታ ለመመለስ በእንቅስቃሴ የማይታሙ የነበረ ቢሆንም ምርቃት ፈለቀን የሚያግዛት ሁነኛ ተጫዋች አለመኖሩ ላሰቡት አጨዋወት ምቹ አልሆነላቸውም ይሁን እንጂ የምስራች ላቀው ከግራ በኩል አልፎ አልፎ ጥቂት ሙከራን ስታደርግ ተመልክተናታል፡፡ ሆኖም የተሻለ አስፈሪ አጥቂዎች ያሉት ንግድ ባንክ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን በመሰንዘሩ የሚያክለው አልነበረም አረጋሽ ካልሳ ሁለት ጊዜ አክርራ መታ የግቡ ቋሚ የመለሰባት እና ትዕግስታ ያደታ በቀጥታ መታ እምወድሽ የመለሰችባት የሚጠቀሱ የባንክ ዕድሎች ናቸው፡፡

የሎዛ እና የረሂማን ጥምረት በሚገባ በመጠቀሙ ሲዋጣላቸው የታዩት ባንኮች ሦስተኛ ጎላቸውን አግኝተዋል፡፡ 53ኛው ደቂቃ ረሂማ ዘርጋው ሰጥታት ሎዛ አበራ ሁለት ተከላካይ እና የአዳማን ግብ ጠባቂ እምወድሽን ጭምር አልፋ ለራሷ ሁለተኛ ለቡድኗ ሦስተኛ ጎልን በድንቅ አጨራረስ አስመዝግባለች፡፡ ከዚህች ጎል መቆጠር ሦስት ደቂቃዎች በኃላ አረጋሽ ካልሳ መሬት ለመሬት የላከቻትን ኳስ ረሂማ አግኝታ መትታ የአዳማዋ ግብ ጠባቂ እምወድሽ ስትተፋው በድጋሚ ረሂማ አግኝታ ወደ ጎል ለውጣው የግብ መጠኑን ከፍ አድርጋለች፡፡ 79ኛው ደቂቃ ላይም ቶሎ ቶሎ ወደ ጎል ሲደርሱ የነበሩት ንግድ ባንኮች ሎዛ አበራ ራሷ ማሰስቆጠር የምትችለውን ኳስ ከሷ የተሻለ ነፃ ቦታ ለነበረችው ረሂማ ሰጥታት አጥቂዋም ለራሷ ሐት-ትሪክ ለቡድኗ አምስተኛ ግብ አግብታ ጨዋታው 5 ለ 0 የንግድ ባንክ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ልሳን የሴቶች ስፖርት ሐት-ትሪክ ሰሪዋ የንግድ ባንክ አምበል ረሂማ ዘርጋውን የጨዋታ ምርጥ ብሎ ሸልሟታል፡፡

ከሰዓት 10፡00 ድሬዳዋ ከተማ ከ መከላከያ የቀኑን ሁለተኛ ጨዋታ ያከናውናሉ፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ