ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 8ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፪) – ተጫዋች ትኩረት

ስምንት ሳምንታት ባስቆጠረው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ትኩረት ሳቢ የተጫዋቾች ነክ ጉዳይን እንዲህ ተመልክተናቸዋል።

👉ሳልሀዲን ሰዒድ ወደ ግብ አግቢነቱ ተመልሷል

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ጅማ አባ ጅፋርን ሲረታ ተቀይሮ በመግባት የመጀመሪያ ጨዋታውን ማድረግ የቻለው የቅዱስ ጊዮርጊሱ አጥቂ ሳልሀዲን ሰዒድ በዚህ ሳምንት ደግሞ ለቡድኑ ከጉዳት መልስ ባደረገው ሁለተኛው ጨዋታ እጅግ ወሳኝ የሆነች ግብን ማስቆጠር ችሏል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ እጅግ በተፈተነበት ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ሳልሀዲን ሰዒድ በ83ኛው ደቂቃ ከሄኖክ አዱኛ የተሻማለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር ከጨዋታው ሦስት ነጥብ ይዞ ለመውጣት ከተጫዋቾቹ ተዓምር ይጠብቅ የነበረውን ቡድኑን ባለ ድል ማድረግ ችሏል።

ይህችም ግብ ተጫዋቹ አምና በታህሳስ 26 አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ መቐለ 70 እንደርታን ሲረቱ ካስቆጠረው ግብ በኃላ ያስቆጠራት የመጀመሪያ ግቡ ሆና ተመዝግባለች።

👉ዕድለ ቢሱ ፍፁም ገብረማርያም

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድሮች የዳኝነት ስህተቶች እዚህም እዚያም መታየታቸው የተለመ ነው ፤ ዘንድሮ ጊዜው ፈቀደና ውድድሮች በላቀ የፕሮዳክሽን ጥራት በሱፐር ስፖርት እየተላለፉ በመሆኑ የዳኝነት ስህተቶችን ከተለያየ የካሜራ አንግል ለተመልካች ቁልጭ ብለው መታየታቸው ጉዳዩ ይበልጥ የትኩረት ማዕከል እንዲሆን አስችሏል።

ታዲያ በ8ኛው ሳምንት ሰበታ ከተማ በባህርዳር ከተማ 4-1 በተሸነፈበት ጨዋታ ለሁለተኛ ጊዜ ያገባው ጎል ከጨዋታ ውጪ የተባለበት የሰበታው አጥቂ ፍፁም ገ/ማርያም ጉዳይ የጨዋታ ሳምንቱ መነጋገርያ ነበር።

በቅርብ ቀናት ልዩነት ለሁለተኛ ጊዜ ግቡ የተሻረበት ፍፁም ገብረማርያም ከዚህ ቀደም ቡድኑ በአምስተኛው ሳምንት ኢትዮጵያ ቡናን በገጠመበት ጨዋታ ከጨዋታ ውጪ በሚል ያገባው ጎል ሲሻርበት በዚህኛው ሳምንትም ተመሳሳይ ዕጣ አጋጥሞታል።

ፍፁም በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች የሰበታ እና ባህርዳር ከተማ ጨዋታ እየቀጠለ ባለበት ወቅት ቡድኑን 2-1 መምራት የምታስችል ኳስ ከመረብ ቢያገናኝም በድጋሚ ሳይፀድቅለት ቀርቷል። ያሁኑን ለየት የሚያደርገው ከቡልቻ ሹራ የተነሳችውን ኳስ ፍፁም ሳይነካት ቢቀር እንኳን ጎል ትሆን የነበረ መሆኑ ነው።

ታድያ ይህች ግብ ፀድቃ ቢሆን አጠቃላይ የጨዋታ ውጤቱ ላይ የሚኖራት ተፅዕኖ በቀላል የሚታይ አልነበረም፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ዕድለ ቢሱ ፍፁም ገ/ማርያም ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር በነበረው ቆይታ ተከታዩን ሀሳብ ሰጥቷል።

“ጎሎች ቡድንን ያነሳሉ። ስታገባ የቡድኑ በራስ መተማመን አብሮ ይነሳል። እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ተደጋገሙብን። ቡድናችን ወደ ተሻለ እንቅስቃሴ በሚገባበት ሰዓት ላይ ነው እንደዚህ ዓይነት ውሳኔዎች የሚገጥሙት። እኔም በግሌ ግቦቹ ባይሻሩ አምስተኛ ጎሌ ይሆን ነበር። ወደ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች ፉክክር ውስጥ የምጠጋበት ሁኔታ ይፈጠር ነበር። አጋጣሚዎቹ ወደ ኋላ አስቀርተውኛል። ከዚህ በኋላም ጎሎችን ለማስቆጠር እሰራለሁ።”

👉ራሱን ዳግም እያስተዋወቀ የሚገኘው ደስታ ዮሐንስ

የዛሬ ስድስት ዓመት ገደማ ነበር ወደ ሀዋሳ ከተማ ዋናው ቡድን ያደገው። በተለይም በመጣባቸው የመጀመሪያ ጥቂት ዓመታት እጅግ ድንቅ የሚባል ብቃቱን በማሳየት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተመራጭ የግራ መስመር ተከላካይ እስከመሆን ደርሶ ነበር። ሆኖም ባጋጠሙት ተደጋጋሚ ጉዳቶች በሚጠበቀው ደረጃ የእግር ኳስ ዕድገቱን ማስቀጠል ያልቻለው ደስታ እጅግ አስቸጋሪ የነበሩ ሁለት ዓመታትን አሳልፏል።

በተሰረዘው የውድድር ዘመን አጋማሽ ላይ የቀድሞው የቡድን አጋሩ ሙሉጌታ ምህረት ሀዋሳ ከተማን በዋና አሰልጣኝነት መረከቡን ተከትሎ ወደ ሀዋሳ ከተማ የተመለሰው ተጫዋቹ በዘንድሮው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የቀደመ ማንነቱን ዳግም መልሶ ያገኘ ይመስላል።

በመስመር ተከላካይነትም ሆነ ተመላላሽነት ለቡድኑ ጥሩ ግልጋሎትን እየሰጠ የሚገኘው ተጫዋቹ በተለይ ከመስመር ወደ ሳጥን ውስጥ የሚጥላቸው ኳሶች የሀዋሳ ከተማ ሁነኛ የማጥቃት አማራጮች እየሆኑ መጥተዋል። በዚህም ሒደት ባለፉት ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሦስት ግብ የሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ማቀበል ችሏል።

👉ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴን ያደረጉት ታዳጊዎቹ

በ8ኛ ሳምንት የቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ወላይታ ድቻን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ባገናኘው እና በቅዱስ ጊዮርጊስ የአንድ ለምንም አሸናፊነት በተጠናቀቀው ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ያደረጉ ታዳጊ ተጫዋቾችን ለመመልከት ችለናል።

የወትሮው ጥንካሬው እየከዳው ይገኛል በሚል ትችቶችን እያስተናገደ በሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ የተከላካይ መስመር ላይ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት አንድ አዲስ ታዳጊን አስመልክቶናል፡፡ አማኑኤል ተርፋ የተሰኘው ይህ ወጣት በመሐል ተከላካይ ስፍራ ላይ ከአስቻለው ታመነ ጋር ተጣምሮ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ዋናው ቡድን የመጀመሪያውን የፉክክር ጨዋታውን አድርጓል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ምንም እንኳን እንደ ቡድን ይህ ነው የሚባል ጫናን ከወላይታ ድቻ አቻው ባያስተናግድ የወጣቱ ተከላካይ እንቅስቃሴ ግን በቀላሉ የሚታይ አልነበረም። በጣም የተረጋጋ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ያደረገው ተጫዋቹ በተለይ በረጃጅሙ የሚጥላቸው ኳሶች እጅግ የተዋጣላቸው ነበሩ።

በተቃራኒው ደግሞ ዋነኛው የፊት አጥቂያቸው ስንታየሁ መንግሥቱን በጉዳት ያጡት ወላይታ ድቻዎች ይህን ክፍተት ለመድፈን የተለያዩ አማራጮችን እየተመለከቱ ይገኛል። የዚህ ሒደት አካል በሆነው ውሳኔ ቡድኑ ቅዱስ ጊዮርጊስን ሲገጥም ወጣቱ አጥቂ ቢኒያም ፍቅሬ የመጀመሪያ ጨዋታውን በቀዳሚው አስራ አንድ ውስጥ ተካቶ ተሰልፏል። ከፀጋዬ ብርሃኑ ጋር በመሆን የድቻን የአጥቂ መስመር የመራው ተጫዋቹ በ60ኛው ደቂቃ ተቀይሮ እስኪወጣ በግሉ ከቡድኑ የተነጠለ በነበረው የወላይታ ድቻ የአጥቂ መስመር ከጊዮርጊስ የተከላካይ ክፍል ጋር ከፍተኛ ፍልሚያ ሲያደርግ ተስተውሏል።

👉ግብ አስቆጣሪው ሳላምላክ ተገኝ

ከዓመታት በፊት በሀገር ዓቀፍ ደረጃ ከሚካሄደው የትምህርት ቤት ውድድሮች ኢትዮጵያ ቡናን የተቀላቀለው ሳላምላክ ተገኝ በተለይ በአሰልጣኝ ድራጋን ፖፓዲች የሹመት ዘመን በመስመር ተከላካይነት ሚና ጥሩ ግልጋሎትን መስጠት ችሏል። ወደ ትውልድ ከተማው ክለብ ባህር ዳር ከተማ ካቀና ወዲህ በግራም በቀኝም የመስመር ተከላካይነት ያለፉትን ሦስት የውድድር ዘመናት እያገለገለ ይገኛል፡፡

በዘንድሮው የውድድር ዘመን የአህመድ ረሺድን ወደ ባህርዳር ከተማ ማምራት ተከትሎ በተለይ በመጀመሪያዎቹ የጨዋታ ሳምንታት የመሰለፍ ዕድልን ለማግኘት ተቸግሮ የነበረው ተጫዋቹ የባህር ዳር ከተማ የመስመር አጥቂ ተጫዋቾች በጉዳት እና በቅጣት በተደጋጋሚ አለመኖራቸውን ተከትሎ ያገኘውን አጋጣሚ በሚገባ እየተጠቀመ ይገኛል።

ከዚህ ቀደም ይጫወትበት ከነበረው የመስመር ተከላካይነት ሚና በተለየ ወደ ፊት በተገፋ ኃላፊነት እየተጫወተ የሚገኘው ተጫዋቹ እስካሁን በአዲሱ ሚናው ሦስት ጨዋታዎችን አድርጎ ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።

👉ወንድማማቾቹን በተቃራኒ ያፋለመው የወንድማማቾች ደርቢ

በ8ኛ ሳምንት ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሀዋሳ ከተማን ከሲዳማ ቡና ያገናኘው የወንድማማቾች ደርቢ ጨዋታ በሀዋሳ ከተማ የ2-0 የበላይነት ተጠናቋል።

ኤፍሬም አሻሞን በሀዋሳ ከተማ እንዲሁም ታናሹን ብርሃኑ አሻሞን በሲዳማ ቡና በኩል በተቃራኒ ያፋለመው ጨዋታው በሀዋሳ ከተማ አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ኤፍሬም አሻሞ ለመጀመሪያዋ የብሩክ በየነ ግብ መቆጠር ምክንያት የነበረችውን ኳስ አመቻችቶ ማቀብል ችሏል።

👉 እያደር እየጣፈጠ የመጣው ዊሊያም ሰለሞን

የቀድሞው የመከላከያ ታዳጊ ህይወት ዳግም የሰጠችውን ዕድል በአግባቡ እየተጠቀመ ያለ ይመስላል። ከእግር ኳስ ጋር ከመለያየት ደርሶ የነበረው ወጣቱ አማካይ ዳግም ወደ ስፖርቱ ከተመለሰ እና ከመከላከያ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ከመጣ በኋላ ተቀይሮ በመግባት የተለየ ችሎታ እንዳለው ማሳየት ከጀመረባቸው ጨዋታዎች በኋላ በአሰልጣኞቹ ዕምነት ተጥሎበት የሸገር ደርቢን ጨምሮ ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ መግባት ከጀመረ በኋላ ትናንት ሦስተኛ ጨዋታውን አድርጓል።

በቀዳሚዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ታታሪነት እና ክህሎትን በቀላቀለ መልኩ በተለይ በአንድ ለአንድ አጋጣሚዎች ለተጋጣሚዎች አስቸጋሪ ሆኖ መታየት ችሏል። ትናንት ኢትዮጵያ ቡና ጅማ አባ ጅፋርን 3-1 በረታበት ጨዋታ ደግሞ ቀደም ሲል ባሳየው ብቃት ላይ ውጤታማነትን መጨመር ችሏል። ዊልያም በጨዋታው የመጀመሪያውን ጎል ለአቡበከር ናስር አመቻችቶ ሲያቀብል ሦስተኛውን ራሱ በማስቆጠር በኢትዮጵያ ቡና ማለያ የጎል አካውንቱን ከፍቷል። ዊልያም ባለፉት ጨዋታዎች ስላሳየው መሻሻል እና ስለትናንቱ ጥሩ ውሎው ለሶከር ኢትዮጵያ ይህንን ብሏል።

” ወደ ኢትዮጵያ ቡና ስመጣ በፍጥነት የመሰለፍ እድል አገኛለው ብዬ አላሰብኩም። ተቀይሮ በመግባት በአንዳንድ ጨዋታዎች ላይ እሰለፋለው ብዬ ነበር የማስበው። ምስጋና ለአሰልጣኞቹ ይሁንና በኔ አምነውብኝ አሁን መጫወት ችያለው። ይህ ለኔ በጣም ትልቅ ዕድል ነው። በኢትዮጵያ ቡና ማልያ የመጀመርያ ጎሌን ማስቆጠሬ ትልቅ ደስታ ፈጥሮብኛል። ይህን ማንም ተጫዋች የሚመኘው ነገር ነው። ይህም በመሳካቱ ደስ ብሎኛል። በራስ መተማመኔ እየጨመረ የተሻለ ነገር አውጥቼ ለመጫወት የዛሬው ጎል ይረዳኛል። አብረውኝ እንዲጫወቱ ከምፈልጋቸው ተጫዋቾች ጋር መጫወቴ ነገሮች ቀለውልኛል። ከዚህ በኃላም ከኔ ብዙ ነገር ይጠበቃል።”


© ሶከር ኢትዮጵያ