“ቡድናችን ጨዋታዎችን ማሸነፍ የሚያስችል አቅም አለው” ኤልያስ ማሞ

በተከታታይ ሦስት ጨዋታ ሽንፈት ያስተናገደው ድሬዳዋ ከተማ ዳግም ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ዝግጁ ስለመሆናቸው አንበሉ ኤልያስ ማሞ ይናገራል። 

በአሰልጣኝ ፍስሐ ጥዑመ ልሳን እየተመሩ በዘንድሮ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ከወዲሁ አስቸጋሪ ጉዞ በማድረግ ላይ የሚገኘው ድሬዳዋ ከተማ የተለያዩ ችግሮች ለቡድኑ ውጤት አለማማር አስተዋፆኦ እንዳደረገ የሚገልፁት ተጫዋቾቹ ይህን ያጋጠማቸውን ችግር ቀርፈው በቀጣይ የአዳማ ጨዋታ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ማሰባቸውን በተለይ አንበሉ ይናገራል። ኤልያስ ማሞ በግሉ ዘንድሮ ጥሩ የውድድር ዓመት እያሳለፈ የሚገኝ ሲሆን ትናንት ከሀድያ ሆሳዕና ሽንፈት በኃላ ቡድኑ ስላለበት ወቅታዊ ሁኔታ እና በቀጣይ መሻሻል ስለማሰባቸው ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግሯል።

” እንደ አንበል ብዙ ችግሮች አሉብን። በተለይ ወደ ጅማ ከመጣን በኃላ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ችግሮች ይታዩብናል። ለምሳሌ የጥንቃቄ ጉድለት፣ የተጫዋቾች መጎዳት፣ ከኮቪድ ጋር በተያያዘ ያጋጠመን ፈተና እና የመሳሰሉት ቡድኑ ወጥ አቋም እንዳይኖረው አድርጎታል። ይህ ደግሞ በየጨዋታው ጫና እያመጣ ተጫዋቾቹን ጭንቀት ውስጥ ከቷቸዋል። በሁሉም የቡድኑ ቦታ ላይ ክፍተቶች አሉብን ይህን ደግሞ ለማስተካከል እየሰራን ነው።

” በጨዋታዎች ላይ ለማሸነፍ ካለን ጉጉት የተነሳ ያገኘነውን አጋጣሚ ያለመጠቀም ችግር አለብን። ብዙ ጊዜ ወደ ጎል እንደርሳለን፤ ግን ማግባት አልቻልንም። በዚህ ላይ እየሰራን ነው። አንዳንዴ ኳስ ነው፤ እንዲህ ያለ ነገር ያጋጥማል። ያሉብንን ያለመናበብ ችግሮች ለማስተካከል እንሞክራለን።

” ቡድናችን ጨዋቴዎችን ማሸነፍ የሚያችል አቅም አለው። ከዚህ በኃላ በሥነ ልቦና ላይ መሰራት አለበት። ምክንያቱም በሦስት ቀን አንዴ ጨዋታ የምናደርግ በመሆኑ ብዙ የተለየ ነገር መስራት አንችልም። በየጨዋታዎቹ ማሸነፍ ካልቻልክ ድካም እና ሌላ ተፅዕኖ ይመጣል። ስለዚህ አዕምሮ ላይ መሥራት ይገባናል። ሊጉ ገና መጀመርያው እንጂ ማለቂያ ላይ አይደለም። አንዳንዴ የምንስታቸው ኳሶች መከላከል ላይ የምንሰራቸው ስህተቶች ዋጋ እያስከፈሉን ነው። እነዚህን ነገሮች ማረም ከቻልን የተሻለ ነገር ማምጣት እንችላለን። በቀጣይ ከአዳማ በሚኖረው ጨዋታ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ እናስባለን።”


© ሶከር ኢትዮጵያ