ቅድመ ዳሰሳ | ሲዳማ ቡና ከ ሰበታ ከተማ

የዘጠነኛውን ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ የተመለከቱ ሀሳቦችን እንደሚከተለው አንስተናል።

በሰባተኛው ሳምንት ሽንፈት ያስተናገዱት ሰበታ እና ሲዳማ እርስ በእርስ በሚገናኙበት ጨዋታ ከሦስት ነጥብ ጋር ለመገናኘት ያፋለማሉ። 

ከነገ ተጋጣሚው በላይም ከድል ርቆ የሰነበተው ሰበታ ከአምስት ጨዋታዎች ሁለት ነጥቦችን ብቻ ማሳካቱ ሲታይ በቶሎ ወደ ውጤት ካልተመለሰ ወደ ሰንጠረዡ ግርጌ መንሸራተቱ በቀላሉ የሚቆም አይመስልም። በባህር ዳሩ ጨዋታ ጥሩ የመጀመሪያ አጋማሽ ያሳለፉት ሰበታዎች ከቀደመው የተሻለ ወደ ተቃራኒ የሜዳ ክልል የተጠጋ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ታይተዋል። ሆኖም ከተሻረባቸው ግብ በተጨማሪ ሊፈታ ያልቻለው የሁለተኛ አጋማሽ የአካል ብቃት መውረድ አሁንም የቡድኑ ስጋት ሆኖ ቀጥሏል። በነገውም ጨዋታ ቡድኑ ይህ ደካማ ጎኑ አብሮት የሚኖር ከሆነ ጥሩ አቋም ላይ ሲሆኑ ከፍ ባለ ጉልበት እና ፍላጎት ከሚጫወቱት የሲዳማ ተሰላፊዎች ፈተና እንዲገጥመው ሊያደርግ ይችላል። በሌላ በኩል ወደ ግብ ማስቆጠሩ እየተመለሰ ያለው ፍፁም ገብረማርያም እና በባህር ዳሩ ጨዋታ ተነቃቅቶ ያታየው ቡልቻ ሹራ ሰበታ ግብ ለማግኘት ተስፋ ሊጥልባቸው የሚችል መሆኑ በበጎ ጎኑ የሚነሳ ነጥብ ነው።

የአሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ቡድን ስድስተኛው ሳምንት ላይ በጉዳት ያጣቸው ቢያድግልኝ ኤልያስ እና ታደለ መንገሻ እንዲሁም በባህር ዳሩ ጨዋታ የተጎዳው ፉዓድ ፈረጃን ግልጋሎት የማያገኝ ሲሆን ያሬድ ሀሰንም በቅጣት ጨዋታው ያልፈዋል።

በሮድዋ ደርቢ ወደ ሽንፈት ለመመለስ የተገደደው ሲዳማ ወልቂጤ እና ድሬዳዋን እንዳሸነፈባቸው ጨዋታዎች ሁሉ ከፍ ባለ መነሳሳት ወደ ሜዳ ካልገባ አራት ሽንፈቶችን ያካተተው ጉዞው በቀላሉ እንዳይሻሻል መሆኑ የግድ ይመስላል። በተለይም ኋላ መስመሩ ላይ በሚሰሩ ስህተቶች ግቦችን ማስተናገዱ በድሬው ጨዋታ በቡድኑ ትጋት ቢቀለበስም ሀዋሳ ላይ ግን ሳይሳካ መቅረቱ ቡድኑ ችግሩን መቅረፍ ላይ እንዲያተኩር የሚያደርገው ነው። ይህ ካልሆነ ግን የሰበታ አማካዮች የታታሪውን የብርሀኑ አሻሞን ሽፋን ካለፉ ለአጥቂዎቻቸው የመጨረሻ ዕድል የሚፈጥሩበት በር በቀላሉ ሊከፈት ይችላል። በሌላ ጎን በማጥቃቱ ረገድ ከተጋጣሚው ዝግ ያለ የመከላከል ሽግግር አንፃር ሲዳማ ወደ ፈጣን የማጥቃት ሽግግሩ ከተመለሰ እና መስመሮችን ነአግባቡ ከተጠቀመ አደጋ የመፍጠር አቅሙ ይኖረዋል። በዚህ ሂደት ውስጥ የማማዱ ሲዲቤ እና ሀብታሙ ገዛኸኝ ብልጭ ብሎ የደበዘዘው ጥምረት ዳግም መልሶ መታየት ይኖርበታል።

በጨዋታው ሲዳማ ቡናዎች ቀደም ሲል ጉዳት ላይ የነበሩት አዲሱ አቱላ ፣ ፍቅሩ ወዴሳ ፣ ይገዙ ቦጋለ እና ጫላ ተሺታ ያላገገሙላቸው ሲሆን አሁን ደግሞ የቀኝ መስመር ተከላካያቸው ዮናታን ፍሰሀም የጉዳት ዝርዝሩን ተቀላቅሏል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– በ2002 እና 2003 የውድድር ዓመታት ቡድኖቹ አራት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ሲዳማ ቡና ሦስት ጊዜ ባለድል በመሆን የተሻለ ሪከርድ አለው። በጨዋታዎቹ ሲዳማ አራት ግቦች ሲኖሩት አንድ ጊዜ ድል የቀናው ሰበታ ደግሞ ሁለት ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሲዳማ ቡና (4-3-3)

መሳይ አያኖ

አማኑኤል እንዳለ – ፈቱዲን ጀማል – ሰንደይ ሙቱኩ – ግሩም አሰፋ

ዳዊት ተፈራ – ብርሀኑ አሻሞ – ዮሴፍ ዮሃንስ

ተመስገን በጅሮንድ – ማማዱ ሲዲቤ – ሀብታሙ ገዛኸኝ

ሰበታ ከተማ (4-3-3)

ፋሲል ገብረሚካኤል

ጌቱ ኃይለማርያም – መሳይ ጻውሎስ – አንተነህ ተስፋዬ – ኃይለሚካኤል አደፍርስ

ዳንኤል ኃይሉ – አብዱልባስጥ ከማል – መስዑድ መሀመድ

ፍፁም ገብረማርያም – እስራኤል እሸቱ– ቡልቻ ሹራ


© ሶከር ኢትዮጵያ