በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሣር ሜዳ የዕለቱ ሁለተኛ የስምንተኛ ሳምንት ጨዋታ በመከላከያ እና ድሬዳዋ መካከል ተደርጎ መከላከያ ቀይሮ ባስገባቸው ተጫዋቾች ታግዞ 3 ለ 2 አሸንፏል፡፡
10:00 ሲል የጀመረው የመከላከያ እና ድሬዳዋ ጨዋታ ለተመልካቹ አዝናኝ እግር ኳስን ቀላቅሎ የተደረገ ነበር፡፡ ቀዳሚው የአርባ አምስት ክፍል ጊዜ ተመሳሳይ የአጨዋወት መንገድ ማለትን ኳስ መሠረት ባደረገ ፍሰት ክለቦቹ ለመጫወት የሞከሩበት መከላከያዎች በዚህ አጋማሽ መሐል ሜዳቸው ተቀዛቅዞ መቅረቡ ለድሬዳዋዎቹ እታለም አመኑ እና ማዕድን ሳዕሉ የተመቹ በመሆናቸው አማካዮች በቶሎ ወደ ፊት በሚጣሉ ኳሶች ለማጥቃት ጥረዋል፡፡ 11ኛው ደቂቃ ላይ ተመጣጣኝ ፉክክር ቢያደርጉም የተወሰነ የመነቃቃት ችግር ይስተዋልባቸው የነበሩት መከላከያዎች ቀዳሚ የሆኑበትን ጎል አግኝተዋል፡፡ሴናፍ ዋቁማ ራሷ ላይ በተሰራ ጥፋት በድሬዳዋ ግብ ክልል ፊት ለፊት ባለው ቦታ ላይ የተገኘውን ቅጣት ምት ራሷ ሴናፍ አክርራ መታው የግቡ የላይኛው ብረት ሲመልሰው መስከረም ካንኮ የድሬዳዋ ተከላካይ እና ግብ ጠባቂዋ ሂሩት ደሴ የአቋቋም ስህተት ላይ በነበሩበት ወቅት የተመለሰችውን ኳስ በግንባር ገጭታ አስቆጥራዋለች፡፡
መሐል ሜዳ ላይ አመዝነው ሲጫወቱ የነበሩት ድሬዳዋዎች በአጋማሹ ወደ መከላከያ የግብ ክልል ሰብሮ ለመግባት ያደረጉት የአጨዋወት መንገድ ያዋጣቸው አልነበረም በተለይ በአንድ ሁለት አልያም ከመስመር በኩል በፀጋነሽ የሚመጡ ዕድሎችን የሚጠቀም ሁነኛ ተጫዋች ባለመኖሩ በጊዜ ቡድናቸው ወደ ጨዋታ እንዳይገባ እክል የሆኑ ሀነቶች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ በመስመር አጨዋወታቸው አደገኛ የነበሩት ድሬዳዋዎች 32ኛው ደቂቃ አቻ ሆነዋል፡፡ የግራ መስመር ተከላካይዋ ፀሀይነሽ በቀለ ኳሱን እየገፋች ወደ ሳጥን ከገባች በኃላ የመከላከያ ተጫዋቾችንም ጭምር አልፋ የታሪኳ በርገና የአቋቋም ስህተት ታክሎበት ጎል አግታ ቡድኗን 1 ለ 1 አድርጋለች፡፡ ምላሽ ለመስጠት በቶሎ ጥቃት ሲሰነዝሩ የነበሩት መከላከያዎች ሁለት ጥሩ ዕድልን በሴናፍ ዋቁማ እና ህይወት ረጉ አማካኝነት ቢያደርጉም ወደ ጎልነት ሊለወጥ ግን አልቻለም በተለይ ሴናፍ ከሂሩት ደሴ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝታ ሂሩት የመለሰችባት ዋነኛ እና መልካም አጋጣሚ ነበር፡፡ የመከላከያን የቀኝ በኩል የመከላከል አደራደር ስህተትን ለመጠቀም በቀኝ አቅጣጫ አድልተው ሲንቀሳበሱ የነበሩት ድሬዎች የመጀመሪያው አጋማሽ ሊፈፀም ሁለት ደቂቃ ሲቀረው ፀጋነሽ ወራና በግራ በኩል በረጅሙ የላከቻትን ኳስ ፀሀይነሽ በቀለ በግንባር ገጭታ በማስቆጠር ለራሷም ለቡድኗም የጎል መጠኑን ሁለት አድርጋለች፡፡
አሁንም አዝናኝነቱ ሳይጠፋ በቀጠለው ሁለተኛው አጋማሽ መከላከያዎች ሁለት ተጫዋቾችን ቀይረው ካስገቡ በኃላ ይበልጥ መነቃቃት ታይባቸዋል፡፡ ህዳት ካሱ እና ገነት ኃይሉን አስወጥተው ኤልሻዳይ ግርማ እና ዐይዳ ዑስማንን ወደ ሜዳ ካስገቡ በኃላ በማጥቃቱ ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ሰንዝረዋል፡፡ ድሬዳዋ ከተማዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ጊዜ ያስቆጠሩት ጎል አስጠብቆ ለመውጣት በሚመስል መልኩ የተንቀሳቀሱ ሲሆን ኳስን ማንሸራሸሩን ግን አልተውትም በተለይ ከፀጋነሽ ወራና የሚነሱ አደገኛ ኳሶች በቀሪው አርባ አምስት ታሪኳ በርገናን የፈተኑ ነበሩ፡፡ 72ኛው ደቂቃ ላይ የድሬዳዋዋ አማካይ ማዕድን ሳህሉ መሀል ሜዳው ላይ ጉዳት አጋጥሟት ድምፆን በሀይል በምታሰማበት ወቅት የድሬዳዋ የህክምና ባለሙያ ለተጫዋቿ የህክምና ዕርዳታ ለመስጠት የዘገየበት አጋጣሚ መደገም የሌለበት እና ሊታረም የሚገባው ጉዳይ ነው በአንፃሩ አምበሏ ሀሳቤ ሙሶ ለተጫዋቾቹ በግሏ የህክምና ዕርዳታን ከባለሙያው ጋር ተባብራ ስታደርግበት የነበረው ሒደት ደግሞ ሊመሰገን የሚገባው ጉዳይ መሆኑን ለመጠቆም እንወዳለን፡፡
የአጥቂ ቁጥራቸውን የጨመሩት እና ፈዛ ለረጅም ደቂቃ በሜዳ ላይ የታየችው ህይወት ረጉ ወደ መነቃቃት የገባችላቸው መከላከያዎች ወደ አቻ ውጤት ተመልሰዋል፡፡ 75ኛው ደቂቃ ላይ ቤተልሄም በቀለ በረጅሙ ስታሻማ ቁመተ አጭሯ ተቀይራ የገባችሁ ኤልሻዳይ ግርማ አስደናቂ የግንባር ጎል አግብታ ቡድኗን ወደ ጨዋታ መልሳለች፡፡ ጥቃት መሰንዘራቸው ቀጥሎ ህይወት ረጉ ከሴናፍ ዋቁማ እንዲሁም ከርቀት ህይወት መታ የሞከራቻቸው መከላከያን ያነቃቁ ኢላማቸውን የጠበቁ ዕድሎች ናቸው፡፡ 82ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸው ወደ መሪነት ተሸጋግረዋል፡፡ ሴናፍ ዋቁማ ከመስመሩ የድሬዳዋ ግብ አካባቢ ስታሻማ ተቀይራ የገባችሁ ሌላኛዋ አጥቂ ዐይዳ ዑስማን በግንባሯ ገጭታ አስቆጥራ መከላከያን ወደ መሪነት አሸጋግራለች፡፡
የመጨረሻዎቹን አስራ አምስት ደቂቃዎች ድሬደዳዋ ከተማዎች አቻ ለመሆን በርካታ ጊዜ ወደ መከላከያ ግብ ክልል ደርሰዋል፡፡ በተለይ ከቀኝ መስመር እየተነሳች ፀጋነሽ ወራና አክርራ የምትመታቸው ኳሶች አስፈሪዎች ነበሩ፡፡ 88ኛው ደቂቃ ከርቀት መትታ ታሪኳ በርገና በአስገራሚ መልኩ ተወርውራ ያወጣችባት እና ራሷ ፀጋነሽ ከቅጣት ምት መታ ድንቅ የነበረችው የመከላከያ ግብ ጠባቂ ታሪኳ አሁንም አውጥታባታለች፡፡ ጨዋታውን ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠርበት በመከላከያ 3 ለ 2 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የመከላከያዋ ግብ ጠባቂ ታሪኳ በርገና በልሳን የሴቶች ስፖርት የጨዋታው ምርጥ ተብላ ተሸልማለች፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ