ቅድመ ዳሰሳ | ባህር ዳር ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

የውድድር ዓመቱን ሀምሳኛ ጨዋታ የተመለከተው ዳሰሳችን ይህንን ይመስላል።

እስካሁን አራት ድሎችን ያሳኩት የጣና ሞገዶቹ አንዴም ተከታታይ ድል ማግኘት አልቻሉም። ይህንን እርግማን ለመስበርም ስበታ ከተማን ካሸነፉበት ጨዋታ በኋላ ነገ ቅዱስ ጊዮርጊስን የሚጋፈጡ ይሆናል።

ባህር ዳር ከተማ ሰበታን ከረታበት ጨዋታ በርከት ያሉ ጠንካራ ጎኖችን ወደ ነገው ጨዋታ ይዞ ይመጣል። ከእነዚህ ውስጥ የምንይሉ ወንድሙ ግብ ማስቆጠር እና ጥሩ መንቀሳቀስ የሳላምላክ ተገኝ ከዕይታ ርቆ የግብ እፋፍ ላይ መገኘት እና ግቦችን ማስቆጠር መቀጠል በጥቂቱ የሚጠቀሱ ነጥቦች ናቸው። አማካይ ክፍል ላይ በጉዳት ተደጋጋሚ ለውጦችን ለማድረግ መገደዱ ደግሞ በተለይም ከተከላካይ መስመሩ ፊት ባለው ቦታ ላይ ወደ መስመር የሚሄዱ ቅብብሎችን የማቋረጥ አቅሙን ሊቀንሰው ይችላል። በተጨዋችነት እና በአሰልጣኝነት ያገለገሉት የቅዱስ ጊዮርጊስን የመስመር አጨዋወት ጠንቅቀው የሚረሱት አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ይህንን የተጋጣሚያቸውን ጠንካራ ጎን ለማክሸፍ ይዘውት የሚገቡት ስትራቴጂ ምን ዓይነት ሊሆን እንደሚችል ተጠባቂ ነው።

በማጥቃቱ በኩል ደግሞ ወደ መሀል ሜዳ የሚጠጋውን የጊዮርጊስን የኋላ ክፍል ከመፈተን አንፃር ፍፁም ዓለሙ ራሱን ነፃ የሚያደርግባቸው ቅፅበቶች እንደእስከዛሬው ሁሉ ነገም ለባህር ዳር ወሳኝ መሆናቸው አይቀርም። የቡድኑ መስመር ተከላካዮች የማጥቃት እገዛ ሊቀንስ በሚችልበት በነገው ጨዋታ ባህር ዳር ከፍፁም ቀጥተኛ ሩጫዎች ዕድሎችን ለመፍጠር ቀሪዎቹን አማካዮቹን በፈጣን ሽግግር ወደ ተጋጣሚው ሜዳ ለማድረስ እንደሚጥርም ይገመታል።

በሸገር ደርቢ የደረሰበትን ሽንፈት ትዝታ በሁለት ተከታታይ ድሎች ማራቅ የቻለው ቅዱስ ጊዮርጊስ በሁለቱም አጋጣሚዎች ተፈትኖ ያሸነፈ ሲሆን ነገም ቀላል ጨዋታ አይጠብቀውም።

የኋላ ክፍላቸው ላይ የነበረባቸውን ክፍተት በወጣቱ አማኑኤል ተርፋ የሸፈኑት ጊዮርጊሶች የቦታውን ሌሎች ተሰላፊዎች ዕርፍት ከመስጠትም ይሁን በአማኑኤል ላይ ያላቸውን ዕምነት ከማሳየት አንፃር ውሳኔያቸው ጥሩ ሆኖ አልፏል። የቡድኑ የኋላ ክፈተት መፍትሄ ስለማግኘቱ ግን እርግጠኛ ለመሆን እንደነገው ጨዋታ የተሻለ የፊት መስመር ጥራት ባለው ቡድን መፈተን ይኖርበታል። በሌላኛው ፅንፍ ደግሞ የሳላሀዲን ሰዒድ ወደ ግብ አስቆጣሪነቱ መምጣትም አሰልጣኝ ማሂር ዴቪድ ከጌታነህ ከበደ ጋር ሁለቱን ዘጠኝ ቁጥሮች በአንድ ላይ ለማስጀመር ካሰቡ ምን ስዓይነት አማራጮችን ሊወስዱ እንደሚችሉ የሚጠቁም ጨዋታ ሊሆን ይችላል።

ከለውጦች አንፃር እንደአማኑኤል ገብረሙካኤል እና አቤል እንዳለ ያሉ ተጫዋቾች ዕድሎችን ማግኘታቸው በቀጣይ ጊዜያት ቡድኑ መሰል ቅይጥ የተጫዋቾች አጠቃቀምን ሊያዘወትር እንደሚችል አመላክቷል። በነገው ጨዋታም ካልተጠበቁ ለውጦች በተጨማሪ ጊዮርጊስ አሁንም ቀጥተኛነቱ እና የተሻጋሪ ኳሶች አስፈሪነቱን መልሶ እያገኘ መሆኑ በቅርብ ጨዋታዎች እየላላ የመጣው የሰለሞን ወዴሳ እና መናፍ ዐወል ጥምረት ስጋት ሊሆን ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ በድቻው ጨዋታ ቀዝቀዝ ብሎ የነበረው የአቤል ያለው እና ጋዲሳ መብራቴ የቡድኑ ጥቃት ምንጭነት ተሻሽሎ ሊቀርብ እንደሚችልም ይታሰባል።

ባህር ዳር ከተማዎች በሰበታው ጨዋታ ጀምሮ በድጋሚ የተጎዳባቸው ሳምሶን ጥላሁንን ጨምሮ በረከት ጥጋቡ ፣ ደረጄ መንግስቱ እና አቤል ውዱን በጉዳት ሲያጡ የባዬ ገዛኸኝ መድረስም አጠራጣሪ ሆኗል። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ፓትሪክ ማታሲ በቡናው ጨዋታ ያየው ቀይ ካርድ የመጨረሻ ጨዋታ ቅጣት በመሆኑ ካለመግባቱ በቀር ሌሎች የቡድን ዜናዎችን ከክለቡ ማግኘት አልቻልንም።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ዓምና ቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 ያሸነፈበት ውጤት ከውድድር ዓመቱ ጋር አብሮ በመሰረዙ አሁንም ባህር ዳር ከተማ በተገናኙባቸው ሁለቱም ጊዜያት 1-0 በማሸነፍ የእርስ በእርስ የበላይነቱን እንደያዘ ነው።

ግምታዊ አሰላለፍ

ባህር ዳር ከተማ (4-1-4-1)

ጽዮን መርዕድ

ሚኪያስ ግርማ – ሰለሞን ወዴሳ – መናፍ ዐወል – አህመድ ረሺድ

ፍቅረሚካኤል ዓለሙ

ሳላምላክ ተገኘ – አፈወርቅ ኃይሉ – ፍፁም ዓለሙ – ግርማ ዲሳሳ

ምንይሉ ወንድሙ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-2-3-1)

ለዓለም ብርሀኑ

ሄኖክ አዱኛ – አማኑኤል ተረፋ – አስቻለው ታመነ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ

ሀይደር ሸረፋ – የዓብስራ ተስፋዬ

ጋዲሳ መብራቴ – ሮቢን ንግላንዴ – አቤል ያለው

ጌታነህ ከበደ


© ሶከር ኢትዮጵያ