ሪፖርት | ባህር ዳር እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለ ጎል ተለያይተዋል

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዘጠነኛ ሳምንት ሁለተኛ ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተለያይተዋል። 

ባህር ዳር ከተማዎች ሳምሶን ጥላሁን እና ወሰኑ ዓሊን አሳርፈው አፈወርቅ ኃይሉ እና ግርማ ዲሳሳን የተጠቀሙ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊሶች በበኩላቸው አቤል ያለው እና የአብስራ ተስፋዬን አሳርፈው ሮቢን ንጋሌንዴ እና ናትናኤል ዘለቀን አሰልፈዋል።

አንዴ ሞቅ አንዴ ቀዝቀዝ እያለ የተከናከነው ጨዋታ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የታየበት ሲሆን ከሁለቱም በኩል የጠሩ የጎል ሙከራዎች ለማድረግ የተቸገሩበት ጨዋታ ሆኖ አልፏል። ከሌላው ጊዜ በተለየ ጥንቃቄን ጨምረው የቀረቡት ባህር ዳሮች በመጀመርያው አጋማሽ በማጥቃት ሽግግር ጥቂት ዕድሎችን መፍጠር ችለውየነበረ ሲሆን በ22ኛው ደቂቃ ሳለአምላክ ተገኘ ከርቀት ሞክሮ ለዓለም ብርሀኑ የለመሰበት የሚጠቀስ ነው። ሀይደር ሸረፋ በመጎዳቱ ገና ከእረፍት በፊት ለውጥ ለማድረግ የተገደዱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በኳስ ቁጥጥር የተሻሉ የነበሩ ቢሆንም የባህር ዳርን የኋላ ክፍል ሰብረው ለመግባት ተቸግረው ታይተዋል። ጋዲሳ እና ሄኖክ ከመስመር ወደ ሳጥን በመግባት ካደረጓቸው ኢላማቸውን ያልጠበቁ ሙከራዎች ውጪም ዕድሎች ሳይፈጥሩ የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል።

አነጋጋሪ ክስተት በነበረበት ሁለተኛ አጋማሽ የተሻሻለ የጨዋታ እንቅስቃሴ ቢታይም ከክፍት ጨዋታ ሙከራዎችን መመልከት ግን አልተቻለም። በ55ኛው ደቂቃ ጋዲሳ መብራቴ ከቅጣት ምት የሞከረው እንዲሁም ኤድዊን ፍሪምፖንግ ከማዕዘን የተሻማን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ሳሙኤል ተስፋዬ ከጎሉ መስመር ያወጣበት ፈረሰኞቹ ጎል ለማስቆጠር የተቃረቡበት ነበር።

ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር ጥንቃቄ እየጨመሩ የመጡት ባህርዳሮች አሸንፈው ሊወጡ የሚችሉበት ወርቃማ አጋጣሚ እና የጨዋታውን መልክ ሊቀይር የሚችል ክስተት አግኝተዋል። ምንይሉ ከባህርዳር የጎል ክልል የተሻገረለትን ኳስ ከጊዮርጊስ ተከላካዮች ጋር ታግሎ ወደ ጎል በሚያመራበት ወቅት በሳጥኑ ጠርዝ አስቻለው ታመነ በሰራው ጥፋት የዕለቱ ዳኛ ባህሩ ተካ በቀጥታ ቀይ ካርድ አስቻለውን ሲያስወጡት በአወዛጋቢ ውሳኔ የፍፁም ቅጣት ምት ሰጥተዋል። ሆኖም የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ምንይሉ ወንድሙ መትቶ በግቡ አናት ሰዶታል። በቀሩት ደቂቃዎችም ተጠቃሽ የጎል ሙከራዎች ሳንመለከት ከተጠበቀው በታች የሆነ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ታይቶበት ያለ ጎል ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ