ሪፖርት | በክስተቶች የተሞላው ጨዋታ በሲዳማ አሸናፊነት ተጠናቋል

ሲዳማ እና ሰበታን ያገናኘው የዘጠነኛው ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ በማማዱ ሲዲቤ ጎል ሲዳማን ባለ ድል አድርጓል። 

ሲዳማ ቡና ከሀዋሳ ከተማው ጨዋታ ጉዳት የገጠመው የቀኝ መስመር ተከላካዩ ዮናታን ፍሰሀን በአማኑኤል እንዳለ ሰንደይ ሙቱኩን ደግሞ በጊት ጋትኮች በመተካት ወደ ሜዳ ሲገባ የአራት ተጨዋቾች ለውጥ ያደረጉት አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ደግሞ ቅጣት ላይ ያለው ያሬድ ሀሰንን በኃይለሚካኤል አደፍርስ ሲተኩ ምንተኖት አሎ ፣ አዲሱ ተስፋዬ እና ኢብራሂም ከድርም በፋሲል ገብረሚካዌል ፣ መሳይ ጳውሎስ እና ጉዳት በገጠመው ፉዓድ ፈረጃ ምትክ ወደ አሰላለፍ መጥተዋል።

በሰበታ ከተማ ከፍ ያለ የኳስ ቁጥጥር በሲዳማ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ የተከወነበት የመጀመሪያው አጋማሽ ጥቂት የሚባሉ ሙከራዎች ብቻ የተደረገበት ነበር። በሰበታ ከተማ በኩል የመስመር አጥቂው ኢብራሂም ከድር ከቀኝ መስመር አሻምቶት ወደ ግብ ያመራው ኳስ ለጥቂት የወጣበት የሰበታ የተሻለ ሙከራ ነበር። በያስር ሙገርዋ እና ማማዱ ሲዲቤ አማካይነት የርቀት ሙከራዎች ያደረጉት ሲዳማዎችም የምንተስኖት አሎ ድንቅ ጥረት ተካሎበት ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታውን ሁሉንም ክስተቶች የያዘ ነበር። 50ኛው ደቂቃ ላይ የአዲሱ ተስፋዬን የኋልዮሽ ቅብብል ስህተትን ተከትሎ ማማዱ ሲዲቤ ያገኘውን አጋጣሚ በመጠቀም የቡድኑን ወሳኝ ግብ ከመረብ አገናኝቷል። ከዚህም በኃላ ሲዳማ ቡናዎች ወደ ግብ መቀየር የሚችሉ የመልሶ ማጥቃት ቅፅበቶችን ማግኘት ጀምረው ጨዋታውን ሙሉ ለሙሉ በእጃቸው ያስገቡ መስለው ነበር። ነገር ግን ከ70ኛው ደቂቃ በኃላ በድራማዊ ክስተቶች የተሞላው ጨዋታ የሰበታ የማጥቃት የበላይነት የታየበት ነበር።

70ኛው ደቂቃ ላይ ፈቱዲን ጀማል ኃይለሚካኤል አደፍርስ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ፍፁም ገብረማርያም ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ተቀይሮ ገብቶ ድንቅ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው ዱሬሳ ሹቢሳ 65 እና 77ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን ሊታደግ የሚችልባቸውን የግብ ዕድሎች ከሳጥን ውስጥ አምክኗል። 79ኛው ደቂቃ ላይም ፍፁም በድጋሚ ከግቡ አፋፍ ላይ ያገኘውን ዕድል ሲዳማን የታደገው መሳይ አያኖ መረብ ላይ ማሳረፍ ሳይችል ቀርቷል። በእነዚህ ደቂቃዎች ጨዋታውን መጨረስ የሚችሉባቸው ዕድሎች ያመለጧቸው ሰበታዎች 80ኛው ደቂቃ ላይ ሌላ ፈተና ገጥሟቸዋል።

የሰበታው አማካይ ዳንኤል ኃይሉ ጥፋት ሰርቶበት የነበረው ያስር ሙገርዋ ላይ በሰነዘረው የአፀፋ እርምጃ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል። ያም ቢሆን ሰበታዎች የነበራቸውን ብልጫ አጠናክረው የአቻነት ግብ ፍለጋ እስከመጨረሻው ደቂቃ ድረስ ጥረታቸውን ቀጥለዋል። በተለይም 87ኛው ደቂቃ ላይ ከጌቱ ኃይለማርያም የተነሳው እና በዱሬሳ ሹቢሳ ከቅርብ ርቀት የተሳተው ኳስ ሰበታን ነጥብ ለማጋራት የተቃረበ ነበር። ነገር ግን በአበባየሁ ዮሃንስ የርቀት ሙከራዎች በመጨረሻ ደቂቃ የሰበታ ሳጥን አቅራቢያ ደርሰው የነበሩት ሲዳማዎች ጥንቃቄ ላይ አመዝነው በቆዩባቸው 20 ደቂቃዎች ግብ ሳያስተናግዱ ጨዋታውን 1-0 ማሸነፍ ችለዋል።



© ሶከር ኢትዮጵያ