ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | አዲስ አበባ ከተማ እና አቃቂ ቃሊቲ አቻ ተለያይተዋል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ስምንተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን የመጀመሪያ የረፋድ 4:00 ጨዋታ በአቃቂ ቃሊቲ እና አዲስ አበባ ከተማ መካከል ተደርጎ 1 ለ 1 ተጠናቋል፡፡ 

ተመጣጣኝ እንቅስቃሴን ባስተዋልንበት እና መሐል ሜዳ ላይ ባመዘነ መልኩ የተካሄደው የአቃቂ እና አዲስ አበባ ጨዋታ ቡድኖቹ ኳስን ያንሸራሽሩ የነበረበት መንገድ ለዕይታ ሙሉውን ዘጠና ደቂቃ ማራኪ የነበረ ቢሆንም ሁነኛ ግብ አስቆጣሪ ያለመኖሩ ሁለቱም ክለቦች ላይ የጎላ ክፍተት ሆኖ የታየም ነበር፡፡ በመጀመሪያው አርባ አምስት ኳስን መሠረት ባደረገ የመሀል ክፍል እንቅሴቃሴያቸው ለተመልካች ሳቢ ሆነው የቀረቡ ቢሆንም በተወሰነ መልኩ አቃቂዎች በቀኝ በኩል በዮርዳኖስ በርሄ ላይ አመዝነው ሲጫወቱ ተስተውሏል። ሆኖም የመስመር አጥቂዋን የሚያግዛት ተጫዋች ያለ መኖሩ ቡድኑ ከነበረው ብልጫ አንፃር ከጎል ጋር እንዲራራቅ አድርጓል፡፡

በአንጻሩ ብልጭ ብለው ይጠፉ የነበሩት እና ኳስን ሲያገኙ ግን አደጋ ለመፍጠር ሲጥሩ የሚስተዋሉት አዲስ አበባዎች ከተሻጋሪ አልያም ከቀኝ በኩል ፈጣኗን አጥቂ እምወድሽ አሸብርን ማዕከል አድርገው ተንቀሳቅሰዋል። በተለይ እምወድሽ በፍጥነት ሰብራ ለመግባት የምታደርገው ጥረት አስገራሚ የነበረ ቢሆንም የኳሱ የመጨረሻ ማረፊያ በአቃቂ ተከላካዮች የተገደበ መሆኑን የተጫዋቿን ፈጣን አመጣጥ ያገደ ነበር፡፡ ወደ መልበሻ ክፍል ሊያመሩ ጥቂት ደቂቃ ሲቀረው የአቃቂዋ አማካይ ኪፊያ አብዱራህማን ነፃ ኳስ አግኝታ ያመከነችው ከተሞከሩት ሙከራዎች የጠራች እና ብቸኛዋ አጋጣሚ ነበረች፡፡

ከእረፍት መልስ የቀጠለው ይህ ጨዋታ ውበቱ ካይደበዝዝ የቀጠለ ሲሆን ይበልጡኑ ግን ለአዲስ አበባ ከተማዎች ምቹ የነበረ ሁለተኛ አጋማሽ ሆኗላቸዋል፡፡ በተለይ በመልሶ ማጥቃት ወደ ቤተልሄም ታምሩ እና ቤተልሄም ሰማን ከሚጣሉ ኳሶች ዕድሎችን ለማግኘት ያደረጉበት መንገድ ሳቢ የነበረ ነበር፡፡ በተመሳሳይ ከመጀመሪያው አጋማሽ ቀዝቀዝ ቢሉም በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ አዲስ አበባ የግብ ክልል በመድረሱ የተዋጣላቸው አቃቂዎች ኳስን ከመረብ የሚያዋህድ ጨራሽ አጥቂ ካለመኖሩ የተነሳ ገና በጊዜ ያገኟቸውን ዕድሎች እንዳይጠቀሙ አድርጓቸዋል፡፡ 55ኛው ደቂቃ ላይ የአዲስ አበባዋ ፈጣን አጥቂ እምወድሽ በቀኝ የአቃቂ የግብ ክልል ኳስን እየገፋች ወደ ሳጥን ስትገባ ማክዳ ዓሊ በሰራችባት ጥፋት የዕለቱ ዋና ዳኛ ገነት ታገሰ የሰጠችሁን የፍፁም ቅጣት ምት ቤተልሄም ታምሩ ወደ ጎልነት ለውጣው አዲስ አበባን መሪ አድርጋለች፡፡

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የመጨረሻ ኃይላቸውን በመጠቀም በተደጋጋሚ ጥቃት የሰነዘሩት አቃቂዎች በትደግ ፍሰሀ፣ ዙለይካ ጁሀድ እና ኪፊያ ያለቀላቸውን ዕድሎች አግኝተው አምክነውታል፡፡ በተለይ ቤዛዊት ንጉሴ ከቀኝ መስመር አክርራ መታ ቤተልሄም የመለከችባት እና ዙለይካ ጁሀድ ፊት ለፊት ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝታ ኳሷን የመታችበት አቅም አናሳ በመሆኑ ግብ ጠባቂዋ ቤተልሄም በቀላሉ የያዘችባት ለአቃቂ ብልጫ መውሰድ ማሳያዎች ነበሩ፡፡ ይሁንና ከተደጋጋሚ ጥረቶች በኃላ ተሳክቶላቸው ግብ አስቆጥረዋል፡፡ ከቀኝ በኩል ቤዛዊት ንጉሤ የግል አቅሟን ተጠቀም ተጫዋቾችን አታላ ካለፈች በኋላ ያሻገረችውን ኳስ ትደግ ፍሰሀ አስቆጥራው አቃቂ ቃሊቲ አንድ ነጥብ እንዲጋራ በማድረግ ጨዋታው 1 ለ 1 ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ልሳን የሴቶች ስፖርት የአዲስ አበባ ከተማዋን ተጫዋች አብነት ለገሰን የጨዋታው ምርጥ ብሎ ሸልሟታል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ