የአሰልጣኞች አስተያየት | ባህር ዳር ከተማ 0-0 ቅዱስ ጊዮርጊስ

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ለሱፐር ስፖርት ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።

ማሒር ዳቪድስ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ስለተሰጠባቸው ፍፁም ቅጣት ምት

” ይሄን እንግዲህ በቴሊቪዥን የተከታተለ ሰው የሚፈርደው ነው።”

በመጀመሪያው አጋማሽ ሀይደር በጉዳት መውጣት ወደ ተቀያሪ የጨዋታ እቅድ ካስገባቸው

“አዎ በሚገባ። ይዘነው የገባነውን እቅድ ረብሾብናል። ውጤቱ አቻ ቢሆንም እንደጥቅሉ ስንመለከተው ግን እንደቡድን ጥሩ ተንቀሳቅሰናል። በመጀመሪያዎቹ ስድስት ጨዋታዎች ግብ ሳይቆጠርብን መውጣት ተስኖን ነበር። አሁን በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ግብ አላስተናገድንም። ከዚያ አንፃር ከተመለከተነው ጥሩ የሚባል ነው።”

በቡድኑ የዛሬው እንቅስቃሴ ደስተኛ ስለመሆኑ

“በትክክል መናገር የምችለው ነገር ቢኖር በትክክለኛው መንገድ ላይ እየተጓዝን ነው። መሠራት የሚገባቸው ቀሪ ሥራዎች ቢኖርም ባለፉት ጥቂት ጨዋታዎች እንደቡድን ጥሩ እየተንቀሳቀስን ነው።”

ፋሲል ተካልኝ – ባህር ዳር ከተማ

በቡድኑ እንቅስቃሴ ደስተኛ ስለመሆኑ

” አዎ ከአንዳንድ ስህተቶች በስተቀር ደስተኛ ነኝ ። ተጫዋቾቼ ነጥብ ለመውሰድ የተቻላቸውን ጥረት አድርገዋል። መጨረሻ ላይ ጨዋታውን ልናሸንፈበት የምንችለውን እድል አግኝተን ሳንጠቀም ቀርተዋል። ያው በእግርኳስ የሚያጋጥም ነው። ከሁሉም በላይ ለእኔ አስፈላጊው ነገር ተጫዋቾቼ ጨዋታውን ለማሸነፍ የተቻላቸውን ጥረት ማድረጋቸው ነው።”

ተጫዋቾቹ በሜዳ ላይ ያሰበውን ስለመተግበራቸው

“ያው የእነሱን የማጥቂያ መንገድ ዘግተን በራሳችን መንገድ ለመጫወት ነው የሞከርነው። 4-2-3-1 የተጫዋቾች ድርደራን ይዘን ነበር የገባነው። በመከላከሉ ረገድ የተሳካ ቢሆንም በማጥቃት ረገድ ግን ሳስተን ነበር። የእነሱን እንቅስቃሴ በመዝጋት ረገድ የተሻልን ብንሆንም ከመከላከል ወደ ማጥቃት የነበረን ሽግግር ግን ችግሮች ነበሩብን።

ምንይሉ ወንድሙ ስላመከናት የፍፁም ቅጣት ምት

” የሚያጋጥም ነው። በ90 ደቂቃ ያሳየው ጥረት ጥሩ ነው። ምንይሉ ጎበዝ ተጫዋች ነው። ቢያገባ ለእርሱም ለእኛም ጥሩ ነበር። ግን በዚህ ደረጃ የሚወራ ነገር አይደለም።”


© ሶከር ኢትዮጵያ