ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ሀዋሳ ከተማ ኤሌክትሪክን በመርታት ወደ ድል ተመለሰ

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ስምንተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ሁለተኛ ጨዋታ 10፡00 ተደርጎ ሀዋሳ ከተማ ኤሌክትሪክን 2 ለ 0 ረቷል፡፡

የሀዋሳ ከተማ የበላይነት በታየበት እና ኤሌክትሪኮች ከቆሙ ኳሶች ብቻ ሙከራ ሲያደርጉ በነበረበት የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሀዋሳ ከተማዎች በመስመር ባጋደለው አጨዋወታቸው ቶሎ ቶሎ ወደ ኤሌክትሪክ የግብ ክልል በመድረስ የተዋጣላቸው ሆነው ታይተዋል፡፡

የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ በማድረጉ ኤሌክትሪኮች ቀዳሚዎቹ ነበሩ፡፡ መሰሉ አበራ ከግራ አቅጣጫ ከቅጣት ምት በረጅሙ አክርራ መታ ግብ ጠባቂዋ አባይነሽ ኤርቄሎ የያዘችባት ብቸኛ የኤሌክትሪክ የጠራች ሙከራ ነች፡፡ ሀዋሳ ከተማዎች አይለው በታዩበት ቀሪ ደቂቃዎች ለተጋጣሚያቸው የነበራቸው ፈጣን እንቅሴቃሴ ለኤሌክትሪክ ተከላካዮች ፈተና ሲሆን ተመልክተናል፡፡በዚህም ሂደት ነፃነት መና ከረድኤት ተቀብላ በቀጥታ መታ ትዕግስት አበራ በያዘችባት አጋጣሚ ወደ ግብ መጠጋት ችለዋል፡፡

የኤሌክትሪክን ዝንጉነት በሚገባ እየተረዱ የሄዱት ሀዋሳዎች 23ኛው ደቂቃ ላይ መሪ መሆን ችለዋል፡፡ ረድኤት አስረሳኸኝ ጣጣውን የጨረሰ ኳስ ሰጥታት ነፃነት መና አስቆጥራው ሀዋሳን ወደ 1 ለ 0 አሸጋግራለች። 33ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ የሜዳው አካል ሀዋሳዎች ያገኙትን የቅጣት ምት መሳይ ተመስገን በረጅሙ አክራራ መታ የግቡ ቋሚ የቀኝ ብረት ሲመልሰው በቅርብ ርቀት የነበረችሁ ትዝታ ኃይለሚካኤል በግንባሯ ነካ በማድረግ ከመረብ አሳርፋ የሀዋሳን የግብ መጠን ወደ ሁለት አሳድጋለች፡፡

ከእረፍት መልስ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ፍፁም ተሻሽለው የመጡበት እና በእንቅስቃሴ በሀዋሳ ላይ ብልጫ የወሰዱበት አጋማሽ ሲሆን በአንፃሩ እየመራ የሚገኘው ሀዋሳ ከተማ ከማጥቃት በተወሰነ ረገድ ተቆጥቦ በሜዳ ላይ ታይቷል፡፡አጥቂዋ ዮርዳኖስ ምዑዝ በተደጋጋሚ በግል ጥረቷ ስታደርጋቸው የነበሩት እንቅስቃሴዎች ከአጠገቧ የሚረዳት ተጫዋች ቢኖር ኖሮ ኤሌክትሪክ ጎል የሚያስቆጥርበት ዕድል በኖረ ነበር፡፡ ተጫዋቿ ኳስን ይዛ ሰብራ ለመግባት ጥረት በምታደርግበት ወቅት በተደጋጋሚ ከጎኗ የቡድን አጋሮቿ ባለመኖራቸው ኳሶቿ ለሀዋሳ ተከላካዮች ሲሳይ ሲሆን በተደጋጋሚ አይተናል፡፡

50ኛው ደቂቃ ላይ በሁለተኛው አጋማሽ ተደጋጋሚ ስህተት ስትሰራ የነበረችው የሀዋሳዋ ግብ ጠባቂ ዓባይነሽ ኤርቄሎ ሳራ ነብሶ ላይ የሰራችውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ዘለቃ አሰፋ መትታው ወደ ላይ ሰዳዋለች። ይሆች አጋጣሚ ኤሌክትሪክን ወደ ጨዋታ ትመልሳለች ተብሎ ቢጠበቅም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

ወደ ጨዋታ ሪትም የገቡት ኤሌክትሪኮች የሀዋሳን የተከላካይ ክፍል የማስከፈት ጥረታቸውን ቀጥለው እፀገነት ብዙነህ ሁለት ተጫዋቾች አልፋ ከሳጥን ውጪ ሞክራ የላይኛው ብረት የመለሰባት ሌላኛው የቡድኑ አስቆጪ ዕድል ነበረች፡፡ መሳይ ተመስገን ተመስገን ካደረገቻቸው ሁለት ሙከራዎች ውጪ ወደ ኤሌክትሪክ ግብ ክልል ለመድረስ የተቸገሩት ሀዋሳ በመጀመሪያው አጋማሽ ባስቆጠሩት ሁለት ጎል አሸናፊ ሆነዋል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የሀዋሳ ከተማዋ ተከላካይ ትዝታ ኃይለሚካኤል የጨዋታው ምርጥ ተብላ በልሳን የሴቶች ስፖርት ተሸልማለች፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ