ከአንድ ዓመት ጉዳት በኋላ ወደ ጨዋታ የተመለሰው ናትናኤል ዘለቀ ይናገራል

በልምምድ ወቅት ባጋጠመው ጉዳት ከአንድ ዓመት በላይ ከሜዳ ርቆ የቆየውና በዛሬው ጨዋታ በመጀመርያ አሰላለፍ በመግባት መልካም እንቅስቃሴ ያደረገው ናትናኤል ዘለቀ ስላሳለፈው አስቸጋሪ ጊዜ አጫውቶናል። 

ሜዳ ላይ በቴክኒክ ችሎታቸው አልያም በኃይል አጨዋወታቸው በቶሎ ዕይታ ውስጥ የማይገቡ ነገር ግን የሚሰጣቸውን ሚና በአግባቡ እና በቀላል መንገድ የሚወጡ ተጫዋቾች አሉ፤ እንደ ቅዱስ ጊዮርጊሱ አማካይ ናትናኤል ዘለቀ አይነት ተጫዋቾች። ባሳለፍነው ዓመት መጀመርያ በልምምድ ወቅት ባጋጠመው የጉልበት ጉዳት ምክንያት ለረጅም ጊዜያት ከሜዳ ርቆ ቆይቷል። ከኢትዮጵያ ውጭ በቱርክ ህክምናውን ሲከታተል ቆይቶ በቅርቡ ወደ ልምምድ የተመለሰው ተጫዋቹ በዛሬው ዕለት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከባህር ዳር ከተማ ጋር ባደረገው ጨዋታ በመጀመርያ አሰላለፍ በመግባት መልካም እንቅስቃሴ ማድረግ ችሏል።

ናትናኤል ዘለቀ የሰውነት ክብደት ሳይጨምር በነበረው አቋም ለረጅም ወራት ከራቀበት ሜዳ ሲመለስ ያዩ ተመልካቾች በሁኔታው ተገርመው እንደነበረ ለመታዘብ ችለናል። ከአስቸጋሪ ጊዜያት በኋላ በዚህ ሁኔታ መታየት ለሌሎች ተጫዋቾች የሚኖረውን ምሳሌነት ከግምት በማስገባት ስላሳለፈው ሁኔታ እንዲያጫውተን ጠይቀነው ተከታዩን ሀሳብ አጋርቶናል።

” ያሳለፍኩት ጊዜ ትንሽ ከባድ ነበር። ከኢትዮጵያ ውጭ የተሻለ ህክምና ለማግኘት ብሞክርም ኮቪድ ገብቶ ሙሉ ለሙሉ የአውሮፕላን በረራ በመቋረጡ በፍጥነት አገግሜ ወደ ሜዳ እንዳልመለስ ህክምና ማግኘት አለመቻሌ እንቅፋት ሆኖብኝ ነበር። ያም ቢሆን ዝም ብዬ ቁጭ አላልኩም። ከጉዳቴ ጋር ያልተያያዙ ልምምዶችን እየሰራው ቆይቻለው። ያው ኮሮና በአጠቃላይ በዓለም የመጣ ስለሆነ 2012 ከባድ ጊዜ ነው ያሳለፍኩት። ፈጣሪ ይመስገን አሁን ደህና ሆኜ ወደ ሜዳ ተመልሻለሁ።

” በተቻለኝ መጠን ራሴን እጠብቃለው። አመጋገቤን አስተካክላለው። በተጨማሪም ጉዳቴን የማይነካ ተጨማሪ ልምምዶችን እሰራለው። ይሄ ሰውነቴ ላይ ምንም አይነት የክብደት መጨመር እና ሌሎች ለውጦች ሳላሳይ እንድመጣ ጠቅሞኛል። በእግርኳስ ተጫዋቾች ላይ የተለያዩ ጉዳቶች ሊከሰቱ ይችላሉ። ዋነው ጠንካራ ሆኖ ነገ ወደሚፈለገው ደረጃ መድረስ እንደሚቻል ውስጥን ማሳመን ተገቢ ነው ብዬ አስባለሁ።

“ዛሬ ከአንድ ዓመት በኃላ ወደ ሜዳ ተመልሻለው። ከጨዋታ ርቀህ ስትመጣ ወደሚፈለገው የአከሐል ብቃት ደረጃ ለመድረስ ትንሽ ተፅዕኖ አለው። ፈጣሪ ይመስገን በዛሬው ጨዋታ ላይ የተቻለኝን ጥረት ለማድረግ ሞክሬያለሁ። ከጨዋታ መራቅ በራሱ ተፅዕኖ ይኖረዋል። በቀጣይ ከዚህ የተሻለ በመሥራት ቅዱስ ጊዮርጊስን ቻምፒዮን ለማድረግ እየሞከርን ነው። እኔም በግሌ ጥሩ ጊዜ ለማሳለፍ እሞክራለሁ።”


© ሶከር ኢትዮጵያ