ሪፖርት | ፋሲል በድል፤ ሙጂብ በጎል ማስቆጠር ጉዟቸው ቀጥለዋል

በቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ውሎ ረፋድ ላይ ወልቂጤ ከተማን የገጠሙት ፋሲል ከነማዎች ልማደኛው ሙጂብ ቃሲም ባስቆጠራት የፍፁም ቅጣት ግብ በመርታት መሪነቱን አስቀጥለዋል። 

ወልቂጤ ከተማዎች በ7ኛ ሳምንት አዳማ ከተማን ከረታው ስብስብ አማካዩ በኃይሉ ተሻገርን በአህመድ ሁሴን ብቻ ቀይረው ወደ ዛሬው ጨዋታ ሲገቡ በአንፃሩ ፋሲል ከነማዎች ደግሞ በ8ኛ ሳምንት አዳማ ከተማን ከረታው ስብስብ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ በዚህም ሱራፌል ዳኛቸው እና ሳሙኤል ዮሐንስን አሳርፈው በምትካቸው ይሁን እንደሻው እና በዛብህ መለዮን በመጀመሪያ ተመራጭነት ይዘው ገብተዋል።

እጅግ አዝናኝ እና ማጥቃትን መሰረት አድርገው በሚጫወቱ ሁለት ቡድኖች መካከል የተደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ፋሲል ከተማዎች በተለይ ወደ መሐል ሜዳ ከተጠጋው የወልቂጤ ከተማ የተከላካይ ጀርባ የሚገኘውን ከፍተት በፈጣን ሽግግሮች ለማጥቃት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል።

በዚህም ሒደት ስድስት የሚሆኑ አጋጣሚዎችን መፍጠር ሲችሉ በተለይም በሁለት አጋጣሚ ከተከላካይ ጀርባ ሙጂብን ታሳቢ ያደረጉትን ኳሶች የወልቂጤው ግብጠባቂ ፈጠን ብሎ ጎሉን ለቆ ወጥቶ አዳናቸው እንጂ እጅግ አደገኞች ነበሩ። የተቀሩት አጋጣሚዎች ግን ከጨዋታ ውጭ በሚል ሊቋረጡ ተገደዋል። በተጨማሪም ፋሲሎች በ15ኛው ደቂቃ በተመሳሳይ በፈጣን ሽግግር በተገኘው አጋጣሚ ሙጂብ ቃሲም እና በረከት ደስታ አከታትለው ሞክረው ጀማል ጣሰው ያዳነባቸው ኳሶች ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ።

ወልቂጤ ከተማዎች እንደቀደሙት ጨዋታዎችን ኳሱን ተቆጣጥረው ወደ ላይኛው የሜዳ ክፍል ለማሳደግ ጥረት ቢያደርጉም በላይኛው የሜዳ ክፍል ላይ የነበራቸው የመጨረሻ ኳሶችን የማቅረብ አፈፃፀም ድክመት መነሻነት የጠሩ የግብ እድሎችን መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። በአጋማሹ ያደረጉት ብቸኛ ተጠቃሽ ሙከራም በ7ኛው ፍሬው ወደ ቀኝ ካደላ አቋቋም የተገኘውና ፍሬው ሰለሞን አሻምቶት ረመዳን የሱፍ በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣበት ነው።

ዐፄዎቹ እጅግ የተሻሉ ሆነው በቀረቡበት የሁለተኛ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በተለይ በአጋማሹ ባደረጓቸው አዎንታዊ የተጫዋቾች ቅያሬዎች ታግዘው በአጋማሹ የበላይነት ወስደው መንቀሳቀስ ችለዋል። በአንፃሩ ወልቂጤ ከተማዎች በአጋማሹ የመጀመሪያ ደቂቃዎች አቡበከር ሳኒ እና አህመድ ሁሴን ከሳጥን ውጭ ባደረጓቸው ሙከራዎች ግብ ለማግኘት ቢሞክሩም ውጤታማ መሆን አልቻሉም።

የፋሲል ከነማ ጫና እያየለበት በመጣው ጨዋታው ፋሲል ከነማዎች በ73ኛው ጀቂቃ አምሳሉ ጥላሁን ያሻገረውን ኳስ ሱራፌል ዳኛቸው በወልቂጤ ሳጥን ውስጥ ሆኖ ኳሷ እንደመጣች ወደ ግብ የላካትና የግቡ ቋሚ የመለሰበት እንዲሁም በ81ኛው ደቂቃ ሙጂብ ቃሲም በግል ጥረቱ ወደ ግብ የላከው እና ጀማል ጣሰው ያዳነበት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ።

በ83ኛው ደቂቃ ፋሲል ከነማዎች ከማዕዘን ያሻሙትን ኳስ ሽመክት ጉግሳ ወደ ግብ ያደረገውን ሙከራ ተቀይሮ የገባው የወልቂጤው አማካይ በኃይሉ ተሻገር በእጅ በመንካቱ መነሻነት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ሙጂብ ቃሲም አስቆጥሮ ቡድኑን አሸናፊ ማድረግ ችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ