የአሰልጣኞች አስተያየት | ወልቂጤ ከተማ 0-1 ፋሲል ከነማ

ፋሲል ከነማ ወልቂጤ ከተማን 1-0 ከረታበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዩን ሀሳብ ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ – ፋሲል ከነማ

ስለጨዋታው

“ወልቂጤ እስካሁን የመጣበት መንገድ ጥሩ ነው። የኳስ አደረጃጀታቸውም ሆነ ወደፊት ለመሄድ የሚያደርጉት ጥረት አጠቃላይ ጥረታቸው ጥሩ ከሚባሉ ቡድኖች አንዱ ናቸው። ስለዚህ ትልቅ ፈተና እንደሚጠብቀን ገምተናል። ከዚህ አንፃር የእኛ ቡድንም ጥሩ በራስ መተማመን እያገኘ ሁሉም የሚችለውን እያደረገ ይገኛል። ለውጦቻችን ጥሩ ናቸው፤ በስተመጨረሻም ነጥብ ይዘን መውጣታችን በቀጣይ ለሚኖረን ጉዞ ያግዘናል።”

ሱራፌል ዳኛቸው ከተጠባባቂ ወንበር ተነስቶ ስለፈጠረው ተፅዕኖ

“አንደኛ እስካሁን ባደረግናቸው ጨዋታዎች የእሱ መልካም እንዲሁም ደካማ ጎኖች ነበሩ። እነዛን ከዚህ በፊት ቁጭ ብለን ማረም እና ማስተካከል እንዳለበት ተነጋግረናል። ዛሬ ደግም ይበልጥ ቁጭ ብሎ እንዲያየው አጠቃላይ እንቅስቃሴውን እንዲመለከተው ማድረጋችን ለእሱ እድል ሰጥቶታል። ሲገባም እንዳያችሁት በእርጋታ የሚያደርጋቸው ነገሮች ሁሉ መልካም ናቸው። ሱራፌል ትልቅ አቅም ያለው ጎበዝ ተጫዋች ነው። ለክለብ እና ለብሔራዊ ቡድን ብቻ ሳይሆን ከሀገር ወጥቶም ለመጫወት የሚያስችል አቅም ያለው ተጫዋች ነው። ስለዚህ እነዚህን ጥቃቅን ነገሮችን እያስተካከለ መሄድ ይኖርበታል።”

ወልቂጤ ከተማዎች አፈግፈገው መጫወታቸው ስለፈጠረባቸው ተፅዕኖ

“በሚገባ! የእነሱ የኳስ ቁጥጥር በእዛው የተገደበ ነው። ወደ እኛ ሜዳ የደረሱበት በጣም አናሳ ነው። ወደ ኃላ አፈግፍጎ የሚጫወት ቡድንን ስትገጥም ደግሞ እንቅስቃሴህን ረጋ ማድረግ ይፈልጋል። ኳስን እያንሸራሸርክ ቀዳዳዎችን መፈለግ ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ እኛ ጥሩ አልነበርንም፤ በተወሰነ መልኩ መጣደፎች ነበሩ። ይህም እነሱ እንዲነሱ እያደረጋቸው ነበር። በዚህ ረገድ በቀጣይ ሥራዎች ይጠብቁናል።”

አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው – ወልቂጤ ከተማ

የተከላካይ መስመራቸውን ወደ መሐል ስለማስጠጋታቸው

“ወደ ጨዋታው ይዘነው የገባነው ነገር ሁለት አጥቂዎችን ወደ ተጋጣሚ ሜዳ በመላክ በ4-4-2 ለመጫወት ነበር ያሰብነው። ሁለቱን አጥቂዎች ለመጠቀም ያሰብነው የእነሱ የመስመር ተከላካዮች በማጥቃቱ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ለመገደብ እና በሚገኙ ክፍተቶች ደግሞ እድሎችን ለመፍጠር ነበር። ነገር ግን በመጀመሪያው አጋማሽ ባሰብነው ልክ አልሄደልንም። በሁለተኛው አጋማሽ ግን የተወሰኑ ማስተካከያዎችን ለማድረግ ሞክረናል። መስመሮችን በመዝጋት ወደ ፊት ለመሄድ ጥረት አድርገናል። ሆኖም ግን የዕለቱ ተጋጣሚያችን ፋሲል ከነማ በሁሉም ረገድ ጥሩ ግስጋሴ እያደረገ የሚገኝ ቡድን እንደመሆኑ የተለከታችሁት ውጤት ተመዝግቧል።”

የፍሬው ሰለሞን ተጎድቶ መውጣት ስለፈጠረው ተፅዕኖ

“እውነት ነው! ሙሉ ለሙሉ ኃይል ቀንሶብናል። ምክንያቱም ፍሬው የአዕምሮም ተጫዋች ነው። ለቡድንህ እንቅስቃሴ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ነው። አስገዳጅ ቅያሬ እንድናደርግ ተገደናል። ሆኖም ግን ተጫዋቾቻችን ሜዳ ላይ የሚችሉትን በሙሉ ለማድረግ ሞክረዋል። በእግርኳስ የሚያጋጥም ነው። በጨዋታው እኛም ልጆቻችንም ብዙ ነገር ተምረንበታል። ፋሲል ከነማ በዛሬው ጨዋታ የተሻለ በመንቀሳቀሱ ውጤቱን ይዞ መውጣት ችሏል።”


© ሶከር ኢትዮጵያ