ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ14ኛ ሳምንት ምርጥ 11

በ14ኛው ሳምንት በተደረጉ ጨዋታዎች ላይ በመመስረት ተከታዮቹን ምርጦች በሳምንቱ ቡድን ውስጥ አካተናል።

አሰላለፍ : 4-3-3

ግብ ጠባቂ

አቤል ማሞ – ኢትዮጵያ ቡና

የተክለማርያም ሻንቆን ቅጣት ተከትሎ በተከታታይ ጨዋታዎች የቋሚነት ዕድል እያገኘ ያለው የግብ ዘቡ አቤል ቡድኑ ወልቂጤ ላይ ሦስት ነጥብ እንዲያገኝ የነበረው አስተዋጽኦ ትልቅ ነበር። በተለይ ቡና የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ተወስዶበት የግብ ሙከራዎች በሚሰነዘሩበት ወቅት ግቡን ላለማስደፈር በጥሩ ቅልጥፍና ከግብ ክልሉ እየወጣ ያከሸፋቸው ኳሶች የሳምንቱ ምርጥ ቡድናችን ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል።

ተከላካዮች

ወንድምአገኝ ማርቆስ – ጅማ አባ ጅፋር

በሊጉ በወጥነት በማገልገል ከዘለቁ የቀኝ መስመር ተከላካዮች ውስጥ አንዱ ወንድምአገኝ ነው። ከቡድኑ መሻሻል ጋርም ብቃቱ አብሮ የዘለቀው ተከላካዩ ጅማ በአዳማ ላይ የዓመቱን ሁለተኛ ድል ሲያስመዘግብ በመከላከሉ ረገድ ያረገው እንቅስቃሴ የአዳማን የመስመር አጥቂዎች ከመቆጣጠር አንፃር ሲመዘን መልካም የነበረ ሲሆን የሳዲቅ ሴቾን ግብ አመቻችቶ በማቀበልም የማጥቃት ተሳትፎው አመርቂ እንዲሆን አድርጓል።

አንተነህ ጉግሳ – ወላይታ ድቻ

ድንቅ ጊዜ እያሳለፈ በሚገኘው የወላይታ ስብስብ ውስጥ አንተነህ ከደጉ ደበበ ጋር የፈጠረው ጥምረት የሰመረ እንደሆነ ቀጥሏል። በዚህ የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ሀዲያ ሆሳዕናን ሲያሸንፍም የተጋጣሚን አጥቂዎች በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት ከመቆጣጠር ባለፈ የአየር ላይ ኳሶችንም በማፅዳት ወላይታ ድቻ ግብ ሳይቆጠርበት ውጤቱን አስጠብቆ እንዲወጣ የበኩሉን ተወጥቷል።

ያሬድ ባዬ – ፋሲል ከነማ

የሊጉ መሪ ፋሲል ከነማ ከቀጥተኛ የዋንጫ ተፎካካሪው ጋር ተጫውቶ ድል ሲቀዳጅ ያሬድ ያሳየው ብቃት የሳምንቱ ምርጥ ቡድናችን ውስጥ እንዲገባ አስችሎታል። ተጫዋቹ ዋና ኃላፊነቱ የሆነውን የመከላከል ሥራ በአግባቡ ከመወጣቱ በተጨማሪ ቡድኑን ከኋላ ሆኖ የሚመራበት እና ኳሶችን የሚያደራጅበት መንገድ ድንቅ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ተጫዋቹ ባለቀ ደቂቃ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት በእርጋታ በመጠቀም ፋሲልን አሸናፊ አድርጓል።

ረመዳን የሱፍ – ወልቂጤ ከተማ

ምንም እንኳን ወልቂጤ ከተማ ኢትዮጵያ ቡናን ገጥሞ 2-1 ቢሸነፍም የመስመር ተከላካዩ ረመዳን የሱፍ በጨዋታው ያሳየው ብቃት እንደተለመደው አድናቆትን የሚያስቸረው ነው። የተሰለፈበትን የግራ መስመር ከጫፍ ጫፍ ሲያካልል ሲታይ የነበረው ተጫዋቹ በተለይ ቡድኑ በጨዋታው የያደረጌቸው የጎል ሙከራዎች መነሻ በመሆን እና በሜዳው ቁመት ቀጥተኛ ሩጫዎችን በማድረግ የማጥቂያ አማራጭ ሲሰጥ ነበር።



አማካዮች

አማኑኤል ተሾመ – ጅማ አባ ጅፋር

ከወላይታ ድቻ ጋር የመጀመሪያውን ዙር ያሳለፈው አማኑኤል ተሾመ ወደ ጅማ አባ ጅፋር ያደረገውን ዝውውር ካጠናቀቀ ከቀናት በኋላ በቀጥታ በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ተካቷል። ተጨዋቹ ከተከላካይ ፊት ባለው እና ከፍተኛ እርጋታን በሚጠይቀው የመጨዋቻ ቦታው ላይ በጥቂት የልምምድ ጊዜ ከአዲስ የቡድን ጓደኞቹ ጋር በመግባባት የተሻለ የኳስ ቁጥጥር የነበረው አዳማ ከተማ የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን እንዳይፈጥር ጥሩ ሽፋን መስጠት ችሏል።

ናትናኤል ዘለቀ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጨረሻ ደቂቃ የፍፁም ቅጣት ምት ጎል ለሽንፈት ይዳረግ እንጂ ተከላካይ አማካዩ ናትናኤል ጥሩ የጨዋታ ቀንን ማሳለፍ ችሎ ነበር። የፋሲልን የማጥቃት ጥረቶች በተደጋጋሚ ሲያቋርጥ የነበረው ናትናኤል ሌሎቹ አማካዮች በነፃነት በማጥቃት ሂደቱ ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ እና ተገቢውን የመከላከል ሽፋን ሰጥቶ በምላሹ ጥቃትን በማስጀመረ በግሉ የሚጠበቅበትን አድርጓል።

አብዱልከሪም ወርቁ – ወልቂጤ ከተማ

ባለ ክህሎት እንደሆነ ከጨዋታ ጨዋታ ሲያሳይ የከረመው አብዱልከሪም ወልቂጤ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ባከናወነው ሳቢ ጨዋታ ላይ የአማካይ መስመሩን በጥሩ ሁኔታ ሲዘውር ነበር። በተለይም የቡድኑ የአማካይ መስመር ከአጥቂ መስመሩ ጋር እንዲገናኝ እንደ ድልድይ ሆኖ የመጨረሻ ኳሶችን ለመስጠት ሲታትር የነበረበት መንገድ መልካም ነበር። ከኳስ ጋር በተገናኘ ቁጥር ቡናዎችን ሲረብሽ የነበረው ደቃቃው አማካይ ብቸኛዋን የአቡበከር ሳኒ ጎልም አመቻችቶ ማቀበል ችሏል።

አጥቂዎች

ወሰኑ ዓሊ – ባህር ዳር ከተማ

ፈጣኑ የመስመር ተጫዋች ወሰኑ ዓሊ ቡድኑ ከአራት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ ድል እንዲያደርግ የማሸነፊያ ጎሉን ከመረብ ከማሳረፉ በተጨማሪ በጨዋታው የነበረው ተሳትፎ የሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲገባ አድርጎታል። ከምንም በላይ ደግሞ ኳስ በሚያገኝበት ጊዜ ፍጥነቱን ተጠቅሞ የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች እንዲሁም ቡድኑ ኳስ ሲያጣ ኳሱን ለማግኘት በሚያደርገው መታተር የተሞላበት አጨዋወት ለተጋጣሚ ቡድን ምቾት አልነበረውም።

አቡበከር ናስር – ኢትዮጵያ ቡና

የምርጥ 11ችን ቋሚ ደንበኛ የሆነው አቡበከር ናስር አሁንም ግቦችን በማምረቱ እና የቡድኑ ዋና ሰው መሆኑን ማሳየቱን ገፍቶበታል። ኢትዮጵያ ቡና አብዛኛውን ጊዜ በወልቂጤ ከተማ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢወሰድበትም ኳስ አቡበከር ጋር በደረሰ ጊዜ ሁሉ ቡድኑ አስፈሪ ሆኖ ታይቷል። ቡናን ለድል ያበቁትን ሁለት ግቦች ሲያስቆጥርም የግል ጥረቱ ጎልቶ የታየ ከመሆኑ ባሻገር የመጨረሻ ውሳኔዎቹ ድንቅ ነበሩ።

ፍፁም ገብረማርያም – ሰበታ ከተማ

ሰበታ ከተማ ሙሉ ሦስት ነጥብ ለማሳካት ባይታደልም ፍፁም በውድድር ዓመቱ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት ስድስት ያደረሰባቸውን ሁለት ኳሶች በድሬዳዋ ከተማ መረብ ላይ በማሳረፍ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የምርጥ ቡድናችን አጥቂ ሆኗል። በተጋጣሚ ግብ አፋፍ ላይ ግቦችን የማነፍነፍ ብቃቱን ደጋግሞ እያሳየን የሚገኘው ፍፁም ካለው የኳስ ቁጥጥር አንፃር በክፍት ጨዋታዎች በርካታ ዕድሎች በማይፈጥረው ቡድን ውስጥ ያሳየው የአጨራረስ ብቃት የሚያስመሰግነው ሆኖ አልፏል።

አሰልጣኝ 

ዘላለም ሽፈራው – ወላይታ ድቻ

ወላይታ ድቻ እና አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ተያይዘው ወደ ሰንጠረዡ ከፍታ መጓዛቸውን ቀጥለዋል። በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ ከአንድ ግብ በላይ ተቆጥሮበት የማያውቀው ሀዲያ ሆሳዕናን ጉሽሚያዎች በበረከቱበት ጨዋታ ሁለት ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝተው የራሳቸውን የግብ ክልል በአግባቡ በመዝጋት ባለድል መሆን ችለዋል። የመጀመሪያ ዕቅዳቸው በአስናቀ ሞገስ ጉዳት ምክንያት የተዛባባቸው አሰልጣኝ ዘላለምም ሽግሽጎችን በማድረግ ቡድኑን ወደ አሸናፊነት መርተውታል።

ተጠባባቂዎች

ሚኬል ሳማኬ – ፋሲል ከነማ
ደጉ ደበበ – ወላይታ ድቻ
ሚኪያስ ግርማ – ባህር ዳር ከተማ
ዳንኤል ደምሴ – ድሬዳዋ ከተማ
ሱራፌል ዳኛቸው – ፋሲል ከነማ
ፍፁም ዓለሙ – ባህር ዳር ከተማ
ሳዲቅ ሴቾ – ጅማ አባ ጅፋር


© ሶከር ኢትዮጵያ