ቅድመ ዳሰሳ | ሀዲያ ሆሳዕና ከ ሀዋሳ ከተማ

የጨዋታ ሳምንቱን የመጨረሻ ግጥሚያ እንዲህ ዳሰነዋል።

ሁለት በጥሩ አቋም ላይ የሚገኙ ቡድኖችን የሚያገናኘው የሳምንቱ የመጨረሻ ፍልሚያ ሦስት ነጥቡን ለመውሰድ በብዙ ረገድ ጠንካራ ፉክክር እንደሚደረግበት ይጠበቃል።
በተከታታይ ድል ከታጀበ ምርጥ አጀማመር በኋላ አቻ እና ሽንፈት አስመዝግቦ የነበረው ሀዲያ ሆሳዕና በስምንተኛ ሳምንት ድሬዳዋን አሸንፎ ወደ ድል እንደመመለሱ በጥሩ መነቃቃት ላይ ይገኛል። ቡድኑ ድሬዳዋን ባሸነፈበት ጨዋታ አብዛኛዎቹን ወሳኝ ተጫዋቾቹን ከጤና መታወክ መልስ ማግኘቱ የሚታወስ ሲሆን ለዚህኛው ጨዋታ ይበልጥ በጥሩ ጤንነት እንደሚገኙ ይታመናል።

እንደየጨዋታው ባህርይ አቀራረባቸውን የሚቀያይሩት አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በነገው ጨዋታ የላቀ የአጨራረስ ብቃታቸውን እያሳዩ የሚገኙት ፈጣኖቹ የሀዋሳ አጥቂዎችን በምን አይነት አቀራረብ እንደሚያቆሙ ትኩረት የሚስብ ጉዳይ ነው። ለጥንቃቄ ቅድሚያ የሚሰጡት አሰልጣኙ ነገ በተለይ በመስመር የሚሰነዘርባቸው ፈጣን ማጥቃትን ለመከላከል የመስመር ተከላካዮቻቸው የማጥቃት ተሳትፎን በመገደብ ላይ ሊያተኩሩ እንደሚችል ይገመታል። ሀዲያ ሆሳዕና ከተከላካይ ጀርባ የሚጣሉ ኳሶችን በብዛት የሚጠቀም ቡድን ከመሆኑ አንፃር የነገ ተጋጣሚው እምብዛም ከጀርባው የማጥቂያ ስፍራ የማይተው መሆኑ ለአሰልጣኝ አሸናፊ ቡድን ፈተና እንደሚሆን ይጠበቃል። ምናልባትም ወደፊት ሄደው ማጥቃት የሚያዘወትሩት የሀዋሳ የመስመር ተከላካዮች ትተው የሚሄዱትን ክፍተት በመጠቀም በታታሪዎቹ አጥቂዎች ለማጥቃት መሞከር ከነብሮቹ የሚጠበቅ ይሆናል።

በአስደናቂ ወቅታዊ አቋም ላይ የሚገኘው ሀዋሳ ከተማ ይበልጥ ወደ መሪዎቹ ለመጠጋት አናት ላይ ከሚገኙ ቡድኖች አንዱ የሆነው ሆሳዕናን ማሸነፍ ይጠበቅበታል።

ሙሉጌታ ምህረት እንደተጋጣሚው አሰልጣኝ ሁሉ ለእያንዳንዱ ተጋጣሚ ተዘጋጅቶ በተለያየ አቀራረብ በመምጣት የማይታሙ ናቸው። ይህም በነገው ጨዋታ ይዘው ሊቀርቡ የሚችሉትን ቡድን ለማየት የሚያጓጓ ነው። ቡድኑ ሲዳማ ቡናን በረታበት ጨዋታ ፈጣን የመስመር ሽግግርን በመተግበር በቶሎ ጎል አስቆጥሮ በሁለተኛው አጋማሽ አፈግፍጎ በመጫወት የሚፈልገውን አሳክቶ መውጣቱ የሚታወስ ሲሆን በሜዳው ቁመት እና ስፋት እምብዛም ክፍተት የማይተወው ሀዲያ ሆሳዕናን በምን መልኩ አስከፍተው ጎል ያገኛሉ የሚለው ጉዳይ ለአሰልጣኙ ከባድ ፈተና ይሆናል።

የአማካይ ክፍል ፍልሚያን በበላይነት መወጣት የጨዋታውን ውጤት ሊወስን የሚችል ሌላው ዐቢይ ጉዳይ ነው። በዚህ ረገድ በምርጥ ብቃት ላይ የሚገኙት ወጣቶቹ ዳዊት ታደሰ እና ወንድማገኝ ኃይሉ እንዲሁም ሌላው ጥሩ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ኤፍሬም ዘካርያስ በልምድ ከተሞላው እና ኃይል ቀላቅሎ ከሚጫወተው የሀዲያ ሆሳዕና የአማካይ ክፍል የሚጠብቃቸውን ከፍተኛ ጫና በአሸናፊነት የመወጣት ከባድ ፈተና ይጠብቃቸዋል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– በሊጉ ከዚህ ቀደም በ 2008 የውድድር ዓመት 2 ጊዜ ተገናኝተው ሀዋሳ አንዱን ሲያሸንፍ በሌላኛው ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹ በአስገራሚ ሁኔታ 11 ጎሎች ሲቆጠሩ ሀዋሳ ከተማ ስድስቱን ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ አምስቱን ከመረብ አገናኝተዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሀዲያ ሆሳዕና (4-3-3)

ደረጄ ዓለሙ

ሱለይማን ሀሚድ – ኢሴንዴ አይዛክ – ተስፋዬ በቀለ – ሄኖክ አርፌጮ

ካሉሻ አልሀሰን – ተስፋዬ አለባቸው – አማንኤል ጎበና

ቢስማርክ አፒያ – ሳሊፉ ፎፋና – ዳዋ ሆቴሳ

ሀዋሳ ከተማ (4-3-3)

ሶሆሆ ሜንሳህ

ዳንኤል ደርቤ – ምኞት ደበበ – ላውረንስ ላርቴ – ደስታ ዮሐንስ

ኤፍሬም ዘካርያስ – ዳዊት ታደሰ – ወንድምአገኝ ኃይሉ

ኤፍሬም አሻሞ – መስፍን ታፈሰ – ብሩክ በየነ


© ሶከር ኢትዮጵያ