ሪፖርት | ወላይታ ድቻ ወደ አሸናፊነት የተመለሰበትን ውጤት ቡና ላይ አስመዝግቧል

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዘጠነኛ ሳምንት የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናን የገጠመው ወላይታ ድቻ ከመመራት ተነስቶ ከስድስት ድል አልባ ጨዋታዎች በኋላ አሸንፏል። 

ወላይታ ድቻ በቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 ከተሸነፈበት አሰላለፍ ሦስት ተጫዋቾችን ለውጥ አድርጎ በመቅረብ መልካሙ ቦጋለ፣ እንድሪስ ሰዒድ እና ቢኒያም ፍቅሬን አሳርፎ ፀጋዬ አበራ፣ ቸርነት ጉግሳ እና መሳይ ኒኮልን ሲጠቀም ኢትዮጵያ ቡና ጅማ አባ ጅፋርን 3-1 የረታው ስብስብን ሙሉ ለሙሉ ይዞ ቀርቧል።

ወላይታ ድቻ ከተጠበቀበት የተለየ አቀራረብ እና ቅርፅ ይዞ በገባበት ጨዋታ ጫናዎች በማሳደር የቡናን ቅብብል በማበላሸት ላይ አተኩሮ በሚገኙ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች የጎል ዕድሎችን ለመፍጠር ጥሯል። በዚህም በ7ኛው ደቂቃ ፀጋዬ ብርሀኑ ከቀኝ መስመር ወደ ግብ የላከው ኳስ በአበበ ጥላሁን ሲመለስ በድጋሚ አግኝቶ ባደረገው አስደንጋጭ ሙከራ ለጎል ቀርበዋል።

ታፈሰ ሰለሞን ከርቀት ባደረገውና ኢላማውን ባልጠበቀ ሙከራ ወደ ጎል የቀረቡት ቡናዎች በ24ኛው ደቂቃ ቀዳሚ ሆነዋል። በጥሩ ሁኔታ የተመሰረተውን ኳስ ታፈሠ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ለነበረው አቤል አሳልፎለት የመስመር አጥቂው ያመቻቸውን አቡበከር ናስር መትቶ ተከላካይ ቢመልሰውም መልሶ አግኝቶ የዓመቱን አስረኛ ጎል አስቆጥሯል።

ጎሉ ከተቆጠረ በኋላ ጨዋታው በሚፈልጉት መንገድ የሄደላቸው ቡናዎች በተሻለ ነፃነት ኳሶችን ወደፊት ማድረስ ቢችሉም የጠራ የጎል ዕድል መፍጠር አልቻሉም። በ33ኛው ደቂቃ አማኑኤል ዮሐንስ ከጥቃት የተመለሰ ኳስን ከሳጥን ውጪ አክርሮ መትቶ የጎሉ አግዳሚ የመለሰበት የአጋማሹ ተጠቃሽ ሙከራ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ በእጅጉ ተሻሽለው የቀረበቡት ወላይታ ድቻዎች በአስገራሚ ተነሳሽነት ከተመሪነት ወደ ድል ተሸጋግረዋል። በመጀመርያው አጋማሽ መገባደጃ እንድሪስ በኤልያስ ተቀይሮ ከገባ በኋላ መረጋጋት የታየባቸው ድቻዎች በረጅም ኳሶች የቡና የጎል ክልል ለመድረስ ያደረጉት ጥረት ጎል አስገኝቶላቸዋል። በ56ኛው ደቂቃ በረጅሙ የተላከውን ኳስ አበበ ጥላሁን እና ግብ ጠባቂው ተክለማርያም በአግባቡ ባለመናበባቸው ፀጋዬ አበራ ክፍተቱን ተጠቅሞ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላም ተመሳሳይ የኋላ ክፍል አለመናበብን ተጠቅመው ድቻዎች ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ቢንያም ፍቅሬ በግንባሩ የገጨውን ኳስ ተክለማርያም አውጥቶበታል።


በሁለተኛው አጋማሽ ለድቻ አጨዋወት ለምላሽ ለመስጠት እና ተረጋግተው ለመጫወት ጊዜ የፈጀባቸው ቡናዎች በሒደት ወደ ድቻ የጎል ክልል አመዝነው ጫና መፍጠር የቻሉ ሲሆን በተለይ በ76ኛው ደቂቃ በድጋሚ መሪ ለመሆን በእጅጉ ቀርበው ነበር። ሳጥኑ ጠርዝ ላይ የተገኘውን የቅጣት ምት አቡበከር መትቶ የጎሉ ቋሚ የመለሰበት የቡና አስቆጪ እድል ነበረች።

በከፍተኛ ብርታት የቡናን ቅብብል በማቋረጥ እና በመልሶ ማጥቃት መጫወታቸውን የቀጠሉት ድቻዎች በ82ኛው ደቂቃ ወደ መሪነት ተሸጋግረዋል። ተቀይሮ ገብቶ ጥሩ የተንቀሳቀሰው ቢኒያም ፍቅሬ በመልሶ ማጥቃት ያገኘውን ኳስ በነፃ አቋቋም ላይ ለነበረው ፀጋዬ ብርሀኑ አሳልፎለት የጨዋታ ድንቅ የነበረው ፀጋዬ በተረጋጋ አጨራረስ ጎሉን አስቆጥሯል። ጨዋታውም ተጨማሪ ሙከራም ሆነ ጎል ሳይታይበት በድቻ 2-1 ተጠናቋል።

ውጤቱ ለወላይታ ድቻ ከስድስት ጨዋታ በኋላ የተገኘ ድል ሲሆን ለአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ደግሞ የመጀመርያ ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ