“የሚፈለገው ሱራፌልን ሆኜ አልመጣሁም” – ሱራፌል ዳኛቸው

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮ የውድድር ዘመን እንደተጠበቀው ሆኖ ያልመጣው እና አጀማመሩ ቀዝቀዝ ያለው የፋሲል ከነማው ኮከብ ሱራፌል ዳኛቸው ስለበትን ወቅታዊ ሁኔታ ይናገራል።

የ2011 የሊጉ ኮከብ ተጫዋች የሆነው ሱራፈል ዳኛቸው በዘንድሮ ዓመት ከዐፄዎቹ ጋር የተጠናቀቀውን ኮንትራቱን በማደስ ለተጨማሪ ሁለት ዓመት ለመቆየት ከስምምነት መድረሱ ይታወሳል። ባለፉት ሁለት ዓመታት በፋሲል ከተማ እጅጉን ከደመቁ ተጫዋቾች በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሰው ሱራፌል ዘንድሮ ግን ያ ባለፉት ዓመታትን የምናውቀው አልሸነፍ ባዩ፣ ሜዳ ላይ ያለውን የሚሰጠው፣ ከምንም ተዐምርን መፍጠር የሚችለውን ተጫዋች ሜዳ ላይ እየተመለከትን አንገኝም። ይልቁንም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተቀዳሚ ተመራጭ እስከመሆን ደርሶ የነበረ ቢሆንም በቅርቡ አሰልጣኝ ውበቱ ሳይጠሩት መቅረታቸው ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ ነበር።

የዐፄዎቹ አድራጊ ፈጣሪ የነበረው ሱራፌል ዳኛቸው በዚህ ደረጃ መዳከም ምድነው ስንል ከወልቂጤ ድል በኃላ አግኝተነው አዋርተነዋል።

” ከብዙ ጊዜ በኋላ ነው ወደ ውድድር የተመለስነው። በዚህም የሚፈለገው ሱራፌል ሆኜ አልመጣሁም። በሚፈለገው ደረጃ ለመምጣት ተጨማሪ ልምምድ እየሰራሁ ነው። ትክክለኛው ሱራፌል ይመጣል። ዛሬ ተቀይሬ ነው የገባሁት፤ ከጨዋታው አንፃር ጥሩ ነገር ለመንቀሳቀስ ችያለው። በሒደት ትክክለኛው ሱራፌል ይመጣል።

” አምስት ቢጫ አይቻለሁ። በዚህም በቀጣይ ጨዋታ አራፊ ነኝ። ይህ ደግሞ ተጨማሪ ልምምዶች ስለሚያስፈልጉኝ ማረፍም ስለምፈልግ በቀጣይ ጨዋታ አለመኖሬን እንደ መልካም አጋጣሚ እጠቀምበታለሁ።

“የብሔራዊ ቡድን ጥሪ ውስጥ ባለመካተቴ ብዙ መስራት እንዳለብኝ ተገንዝቤለው። ቅድም እንዳልኩት የሚፈለገው ሱራፌል ሆኜ አልመጣሁም። ትክክለኛው ሱራፌል ሆኜ እንድመጣ ትልቅ ትምህርት ይሆነኛል። ስለዚህ በብሔራዊ ቡድን አለመጠራቴ ያነሳሳኛል እንጂ ሌላ ብዙም የምለው ነገር የለም። አለመጠራቴ አሪፍ ነው።

” በኮሮና መምጣት ምክንያት እረፍቱ በእንቅስቃሴ ላይ ጥሩ እንዳልሆን ተፅዕኖ አድርጎብኛል። ሰባት ወር ስምንት ወር ማረፍ በጣም ከባድ ነው፤ ቀላል አይደለም። አሁን እየመጣሁ ነው። በዛሬው ጨዋታ ከአሰልጣኜ ጋር ተነጋግሬ ነው ቁጭ ያልኩት፤ ማረፉን ፈልጌ ነው። ትንሽ የተረከዝ ጉዳትም ነበረብኝ።

” በሁለተኛው ዙር በሚገባ ትክክለኛውን ሱራፌል ታገኙታላችሁ። ሜዳዎቹ አዲስ አበባም እዚህም ጅማ እንደምታዩት ነው። ትንሽ ለመጫወት ያስቸግራል። እንደፈለግነው ኳስ ለማንሸራሸር እየተቸገርን ነው። ባህር ዳር ሜዳ ላይ ትክክለኛው ሱራፈልን ታዩታላችሁ።”


© ሶከር ኢትዮጵያ