የአሰልጣኞች አስተያየት | አዳማ ከተማ 0 -3 ድሬዳዋ ከተማ

የረፋዱ ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኃላ የቡድኖቹ አሰልጣኞች ከሱፐር ስፖርት ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።

አሰልጣኝ ፍሰሀ ጥዑመልሳን – ድሬዳዋ ከተማ

ስለጨዋታው

ትልቁ ነገር ተጫዋቾች ላይ የተሰራው ነገር ነው። ከዚህ ጫና ውስጥ መውጣት ከባድ ነው። ባለፈው ሳምንት ወደ ጨዋታችን ተመልሰናል ፤ ማሸነፍ አልቻልንም አጋጣሚ። ዛሬ ደግሞ ጨዋታውንም ማሸነፉንም አንድ ላይ ማድረግ ችለናል። ተጫዋቾቼ በጣም ትልቅ ስራ ነው የሰሩት። ምክንያቱም ያን ጫና ተሸክሞ ማሸነፍ ቀላል ነገር አይደለም። እና ተጫዋቾቼን በጣም ነው የማመሰግናቸው ዛሬ ላደረጉት ነገር።

ስለጫናው

‘አንዳንዴ በእግር ኳስ ጥሩ ቡድን ሰርተህ ውጤት እምቢ ይልሀል። አንዳንዴ አንተ ገለል ስትል ውጤቱ ይመጣል።’ የሚል ጭንቅላቴ ውስጥ ሳብሰለስለው የነበረ ነገር ስላለ ዛሬ ብንሸነፍ በፍቃዴ ለመልቀቅ ወስኜ ነበር በራሴ። እንጂ ኃላፊዎቼ ያስጨነቁኝ ነገር የለም። እንደውም ትናንትም ከትናንት ወዲያም ደውለው ‘በርታ አይዞህ ጥሩ ቡድን ነው’ ነበር የሚሉኝ። ያው እግዚአብሔር ረዳኝ እና ወደ ዛሬ ማሸነፉ መጣሁ። ከዚህ በኃላ ያለውን ነገር ወደማስቀጠሉ ነው። ያው ድካም አለ ተጫዋቾችን እያሳረፍኩ ማጫወት አሁን አዲስ ያመጣሁት ነገር እየተጫወቱ ያሉትን እያሳረፍኩ ጉልበት የሰበሰቡትን እያስገባሁ በዚሁ ቡድኑን ማስቀጠል ነው የምፈልገው።

ስለተሳቱ ኳሶች

ጫናው አለ፤ የማግባት ጉጉት አለ። በቃ የተሸከሙት ነገር ከባድ ነበር፤ ለዚህ ነው። እና ከዚህ ውስጥ መውጣታችን ከማጥ ውስጥ የመውጣት ያህል ነው። ያው የአሰልጣኝ ሥራ ከባድ ነው።

አሰልጣኝ አስቻለው ኃይለሚካኤል – አዳማ ከተማ

የግብ ዕድሎችን ስላለመጠቀማቸው

ተጫዋቾች ላይ ጉጉት አለ። ወደ ቅኝት ለመግባት ፣ ውጤት ለማምጣት ካለው ጉጉት አኳያ ነው። ያው የማይሳቱ ኳሶችን ነው ያጣነው። ያው ዋጋ ያስከፍላል ፤ በሳትክ ቁጥር አንተ ላይም አደጋ ይኖራል።

ስለተከላካይ ክፍል ችግር

መጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ረጃጅም ኳሶች ነው ሲጥሉ የነበሩት። የእኛ የተከላካይ መስመር አቋቋም ትንሽ ክፍተት ነበረው። ከዕረፍት በኋላ ቅያሪም አድርገን ለማስተካከል ሞክረናል። ያው በውጤቱ ታዝናለህ ፤ ትቀበላለህ ግድ ነው።

ጫና ውስጥ ስለመሆናቸው

ጫና ሲባል አሰልጣኝ እኮ ይሰራል ይለቃል። ይሄ ያለ ነው ፤ ለሁሉ ነገር ዝግጁ ነኝ። ውጤት ካጣህ ባለህ አቅም ነው የምትወዳደረው። የመጀመሪያው ዙር ካለቀ በኃላ ለማስተካከል ጥረት ይኖራል። ግን ምንም አያስጨንቀኝም ፤ ባለህ አቅም ነው ወደ ውድድር የምትገባው። የሚመጣውን ነገር ለመቀበል ዝግጁ ነኝ ፤ አዲስ ነገር አይኖርም።


© ሶከር ኢትዮጵያ