ቅድመ ዳሰሳ | ድሬዳዋ ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ

በ13ኛው ሳምንት የመጨረሻ ቀን በቅድሚያ የሚከናወነው ጨዋታ ላይ ተከታዮቹን ሀሳቦች አንስተናል።

ድሬዳዋ ከተማ ከበላይ ያሉት ሁለቱ ተፎካካሪዎቹ ወላይታ ድቻ እና ሲዳማ ቡና እርስ በእርስ በሚገናኙበት በዚህ የጨዋታ ሳምንት ድል ከቀናው ከወራጅ ቀጠናው ከፍ የማለት ዕድል ይኖረዋል።

ከአሰልጣኝ ፍሰሐ ጥዑመልሳን ስንብት በኋላ ለ20 ቀናት ዕረፍት ላይ የከረመው ድሬዳዋ ከተማ ከአዲሱ አለቃው አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ጋር ወደ ሜዳ ይመለሳል። ሶከር ኢትዮጵያ ከአሰልጣኝ ዘማርያም ጋር ባደረገችው ቆይታ ቡድኑ ሦስት የልምምድ መርሐ ግብሮችን እንዳከናወነ መረዳት ችላለች። አሰልጣኙ እንዳሉትም ምንም እንኳን የተወሰኑ ክፍተቶችን ለመድፈን ክለቡ ወደ ገበያ ሊወጣ ቢችልም ከነገው ጨዋታ አስቀድሞ ግን አሁን ያለው ስብስቡ በጥሩ መነሳሳት ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል። የተጨዋቾቹ የተናጠል ብቃትም ሲገመገም ቡድኑ አሁን ካለበት ደረጃ ጋር እንደማይሄድም አሰልጣኝ ዘማርያም ዕምነታቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ባለፉት ስድስት ሳምንታት አንድ ድል ብቻ ያሳካው ድሬዳዋ ፊት መስመር ላይ ውጤትን መቀየር የሚያስችል ብቃት ያላቸው እንደ ሙኸዲን ሙሳ ዓይነት ተጨዋቾችን ቢይዝም በተከላካይ መስመሩ ላይ የሚሰሩ ተደጋጋሚ ስህተቶች ዋጋ ሲያስከፍሉት እንደነበር ይታወሳል። ነገም በመሀል ተከላካይ ቦታ ላይ ቀዳሚ ተመራጭ የሆኑት በረከት ሳሙኤል እና ፍቃዱ ደነቀ ወደ ሜዳ የማይመለሱ መሆኑ ለድሬ ፈተና ሊሆን ይችላል። ከዚህ ውጪ አምበሉ ኤልያስ ማሞ ከክለቡ ጋር መለያየቱ ሲታወስ ያሬድ ዘውድነህ እና ቢኒያም ጥዑመልሳን ደግሞ አገግመዋለታል።

ከድል ጋር ከተለያየ አራት የጨዋታ ሳምንታትን ያሳለፈው ሀዋሳ ከተማ ነገም እስከ አምስተኝነት ከፍ የሚደርገውን ድል ፍለጋ ወደ ሜዳ ይገባል።

በፋሲል ከነማ 2-1 ከተሸነፈ በኋላ ወደ ዛሬው ጨዋታ የሚመጣው ሀዋሳ በመጨረሻ ጨዋታው መጥፎ አቋም አሳይቷል ለማለት አያስደፍርም። በተለይም ሙሉ ትኩረቱን ማጥቃት ላይ ባደረገባቸው የመጨረሻ ደቂቃዎች ለመልሶ መጠቃት ላለመጋለጥ ከግብ ክልላቸው ርቀው የነበሩት የኋላ መስመር ተሰላፊዎቹ የነበራቸው ቅልጥፍና የሚደነቅ ነበር። ይህን ጠንካራ ጎን ተጭኖ ለመጫወት በማሰብ በሚጀምረው የነገው ጨዋታ ይዞት መሻገር ይኖርበታል። ከድሬዳዋ አጥቂዎች ፍጥነት አኳያም እንደባለፈው ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ የነበሩ መዘናጋቶች ከተደገሙ ቡድኑን ዋጋ ማስከፈላቸው አይቀርም።

ሀዋሳ ነገ የሚጠቀምበት ስብስብ ዝግጁነት ለአስሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ደስ የሚያሰኝ የሚያሳዝንም ዜና ያለበት ሆኗል።አማካይ ክፍል ላይ ከረጅም ጊዜ በኋላ ወደ ሜዳ ተመልሶ ከሳጥን እስከ ሳጥን ያለውን ቦታ በትጋት ሲሸፍን የነበራው የአለልኝ አዘነ ከነገው ጨዋታ ውጪ ሆኗል። ለቡድኑ የማጥቂያ አማራጭ ሆኖ የነበረው ይህ ተጨዋች ትልቅ ዕጦት ሲሆን በተቃራኒው ከግራ መስመር የሚነሳው የሀዋሳ ጥቃት ዋነኛ ተዋናይ የሆነው ደስታ ዮሃንስ ደግሞ ወደ ሜዳ እንደሚመለስ ይጠበቃል። የቡድኑን ሚዛን ከመጠበቅ እና ለተጋጣሚ አቀራረብ ምላሽ ከመስጠት አንፃር ጉልህ ሚና የነበረው ኤፍሬም ዘካርያስ ፣ ጉዳት ላይ የሰነበተው ወንድምአገኝ ማዕረግ እንዲሁም ታታሪው የመስመር ተከላካይ ዳንኤል ደርቤ ደግሞ ሌሎች ጨዋታው የሚያልፋቸው ተጫዋቾች ሆነዋል።

የእርስ በእርስ ግንኘነት

– ሁለቱ ክለቦች እስካሁን በሊጉ 16 ጊዜ ሲገናኙ እኩል አምስት አምስት ጊዜ ተሸናንፈው በቀሪዎቹ ስድስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። ድሬዳዋ ከተማ 16 ጎሎች በማስቆጠር ብልጫ ሲኖረው ሀዋሳ ከተማ 14 ጎሎችን አስቆጥሯል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ድሬዳዋ ከተማ (4-2-3-1)

ፍሬው ጌታሁን

ምንያምር ጴጥሮስ – ያሬድ ዘውድነህ – ፍሬዘር ካሳ – ዘነበ ከበደ

ዳንኤል ደምሴ – አስጨናቂ ሉቃስ

ጁኒያስ ናንጄቦ – ሱራፌል ጌታቸው – አስቻለው ግርማ

ሙኸዲን ሙሳ

ሀዋሳ ከተማ (4-3-3)

ሶሆሆ ሜንሳህ

ዘነበ ከድር – ምኞት ደበበ – ላውረንስ ላርቴ – ደስታ ዮሐንስ

ሄኖክ ድልቢ – ዳዊት ታደሰ – ወንድምአገኝ ኃይሉ

ኤፍሬም አሻሞ – መስፍን ታፈሰ – ብሩክ በየነ


© ሶከር ኢትዮጵያ