ከሳላዲን ሰዒድ እስከ ቤካም አብደላ – የአሰልጣኝ ጋሻው መኮንን ፍሬዎች…

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የጅማ ቆይታ በተፈጠረ አንድ አጋጣሚ መነሻነት የአሰልጣኝ ጋሻው መኮንንን የታዳጊዎች ሥልጠና ጉዞ ዳስሰናል።

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሰባተኛ ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስ ጅማ አባ ጅፋርን 3-2 ያሸነፈበትን ጨዋታ ከታደሙ ሰዎች መካከል አንዱ በተለየ የደስታ ስሜት ጨዋታውን ተከታትሏል። ደስታው የመጣው ግን በውጤቱ ወይም ለቡድኖቹ በነበረው የድጋፍ ስሜት የተነሳ አልነበረም፤ የዓመታት ሥራውን ውጤት በጨዋታው የሁለተኛ አጋማሽ ላይ በመመልከቱ እንጂ። በአጋማሹ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሳላዲን ሰዒድን ጅማ አባ ጅፋር ደግሞ ቤካም አብደላን ቀይረው አስገብተዋል። ወጣቱ ቤካምም አስደናቂ ግብ ማስቆጠር ችሎ ነበር። ታድያ ሁለቱን ተጫዋቾች የሚያመሳስላቸው ነገር በተለያዩ ዓመታት እና በተለያዩ ቦታዎች በዚህ ሰው ሥልጠና ውስጥ አልፈው ላሉበት ደረጃ መብቃታቸው ነው። “በቤኒሻንጉል የሰራሁት ሳላዲን እና በጅማ የሰራሁት ቤካም በተቃራኒ ሆነው ሲጫወቱ መመልከት ልዩ ስሜትን የሚፈጥር ነበር። ከጨዋታው በኋላም እንዲገናኙ እና ስልክ እንዲለዋወጡ አድርጌያለሁ። ቤካም ያለው ችሎታ በሳላ ልምድ ሲታገዝ የልጁን የወደፊት ውጤታማነት የማሳደግ ዕድል ይኖረዋል።” ሲልም ያንን ቀን ያስታውሰዋል።

የትውልድ ቦታው ጅማ ሲሆን በወጣትነቱ ለጅማ ምርጥ በመጫወት አሳልፏል። በመቀጠል በቤኒሻንጉል ንስር ለተባለ ክለብ መጫወት የቀጠለ ቢሆንም ጉልበቱ ላይ በገጠመው ጉዳት ምክንያት በጊዜ ከተጨዋችነት ዓለም ተሰናብቷል። ነገር ግን ከስፖርቱ ላለመራቅ የክልሉ መንግሥት ያመቻቸውን ዕድል በመጠቀም የአሰልጣኝነት ሥልጠና ወስዶ ታዳጊዎች ላይ መሥራትን ምርጫው አደረገ። በዚህ መልኩ በ1990ዎቹ አጋማሽ ላይ በጀመረው የታዳጊዎች ሥልጠና በርካታ ተጨዋቾችን ማውጣት የቻለ ሲሆን በጊዜ ሒደትም በትላልቅ ክለቦች የተጫወቱ እና የኢትዮጵያብሔራዊ ቡድንን ለማገልገል የበቁ ተጫዋቾችን ማፍራት ችሏል፤ አሰልጣኝ ጋሻው መኮንን።

ሳላዲን ሰዒድ ከግራ ወደ ቀኝ የመጀመርያው ..

አሰልጣኝ ጋሻው በቤኒሻንጉል ቆይታው በሙገር እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚታወቀው ሳላዲን ሰዒድ በተጨማሪ የአዳማ ከተማው አምበል ሱሌይማን መሀመድ ፣ በንግድ ባንክ ተጫውተው ያሳለፉት አልሳዲቅ አልማሂ እና ሚካኤል ጋሪ ፣ በሲዳማ ቡና የተጬወተው ሳዳት የሱፍ እንዲሁም ለጅማ አባ ቡና የተጫወተው ዘላለም ሊካሳን ጭምር ማብቃት ችሏል። ነገር ግን አሁንም ድረስ በወጣቶች እግርኳስ ላይ እየሰራ ነው የሚገኘው። በክለቦች ከማሰልጠን ይልቅ በወጣቶች ላይ መሥራት የመረጠበት ምክንያትም አረንዲህ ያብራራል። “እኔ ልጆችን ይዤ መቀጠልን ነበር የምፈልገው። ከክለቦች ሁለተኛ እና ሦስተኛ ቡድኖች ተጫዋቾችን ማብቃት ነው ምርጫዬ የነበረው። እርግጥ ነው ጥያቄዎች ቀርበውልኝ ያውቃሉ። ለምሳሌ ከጅማ አባ ቡና በኩል ፍላጎት ነበር። ነገር ግን ቢያንስ የሁለት እና የሦስት ዓመት ኮንትራት ነው የምፈልገው። የውጪ ዜጎች የሌሉበት በወጣቶች ላይ የተመሰረተ ቡድን ለመስራት ስለሆነ ፍላጎቴ የአጭር ጊዜ ስምምነቶችን አልፈለኩም። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ቡና በሀገር ውስጥ ተጨዋቾች ተገንብቶ ጥሩ እግርኳስ ሲጫወት እየተመለከትን ነው። በዛ መንገድ መሥራት ምርጫዬ ነው። አሁን ላይ ግን በትምህርቱ በኩል ማሻሻል የምፈልጋቸው ነገሮች አሉ። በተለይ በስፖርት ሳይንስ የተሻለ ትምህርት ወስጄ አካዳሚዎች ላይ ስለመስራት አስባለሁ። ከዚህ ውጪ ባለኝ የ’ቢ’ ላይሰንስም ሰርቼበታለሁ ማለት አልችልም። በታዳጊዎች ላይ መስራቴ ከሚፈጥርልኝ ሀሴት በዘለለ ያገኘሁት የተለየ ጥቅምም ኖሮ አይደለም። ግን በልጅነታቸው የሰራሁባቸው ልጆች እዚህ ደርሰው ማየት የሚሰጠኝ ትርጉም ልዩ ነው። ከዛ አንፃር እኔም ዕድሉን አግኝቼ በአቅሜ የሀገሬን እግር ኳስ ማሳደግ የምችልበትን መንገድ ባገኝ ደስተኛ ነኝ።” ይላል።

2007 ላይ ከቤኒሻንጉል ወደ ትውልድ ከተማው ጅማ የተመለሰው አሰልጣኝ ጋሻው የአሰልጣኝነት ሥልጠና ደረጃውን እስከ ቢ ላይሰንስ በማድረስ በድጋሚ በታዳጊዎች ላይ እየሰራ ቆይቷል። በግሉ መልምሏቸው በ13 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ እያሰለጠናቸው የነበሩ ልጆችን ይዞም በክልሉ ድጋፍ እንዲሁም እግርኳስን ተጫውተው ባሳለፉት የከተማዋ ባለሀብቶች ትብብር ታዳጊዎቹ በፕሮጀክት ታቅፈው እየሰሩ እንዲቆዩ አድርጓል። ዛሬ ላይ ከእነዚህ ታዳጊዎች ውስጥ ሁለቱ ከተማዋ የፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ ጅማ አባ ጅፋር ውስጥ የመሰለፍ ዕድል ሲያገኙ መመልከትም ችለናል። ያም ቢሆን ግን አሰልጣኙ የከተማው ክለቦች ታዳጊዎች ላይ ያላቸው ዕምነት እጅግ የወረደ መሆኑ አብዝቶ እንደሚከነክነው ከቀጣዩ ሀሳቡ መረዳት ይቻላል። “በፕሮጀክት የተሰሩ ልጆችን መቀበል ላይ በክለቦች በኩል ብዙ ፍላጎት አላይም። በፌዴሬሽኑ በኩል የሚያስገድዱ ህጎች ቢኖሩ እንኳን በተለይ በጅማ ክለቦች ውስጥ ተግባራዊ ሲደረግ አልተመለከትኩም። አባ ጅፋርም ሆነ አባ ቡና ላይ ተስፋ የሚባል ቡድን የለም። ተጨዋቾች ከውጪ እና ከሌሎች ክለቦች እያመጡ ዋንጫ የመብላት ትርጉሙ ብዙ አይገባኝም። ቀጣይነት ያለው ውጤት ለማግኘት ታዳጊዎች ላይ መሥራት አማራጭ የሌለው መንገድ ነው። ይህንን ለማድረግ ደግሞ የአመራር ቁርጠኝነት ያስፈልጋል። ከፌዴሬሽኑ የሚመጣውን ሰርኩላር የማስፈፀም ተነሳሽነት የግድ ሊኖረው ይገባል። የአዲስ አበባ እና የደቡብ ቡድኖች ላይ የታዳጊዎች ውድድሮች ላይ የመሳተፍ ነገር ይታያል። ጅማ ላይ ግን ይህ ነገር የለም። በአባ ጅፋር ዕድል ያገኙት ልጆችም በራሳቸው ትግል እና ጥረት ነው እዛ ደረጃ ላይ የደረሱት።”

ከግራ ወደ ቀኝ – የመጀመርያው ቤካም፣ ስምንተኛው ኢዳላሚን…

በጅማ አባ ጅፋር ዕድል ያገኙት ሁለቱ ተጫዋቾች በቅርብ ጨዋታዎች ተፅዕኖው ከፍ ብሎ የታየው እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ድንቅ ግብ ያስቆጠረው ቤካም አብደላ እንዲሁም በመጀመሪያው ጨዋታ ቡድኑ ግብ ጠባቂውን በቀይ ካርድ ሲያጣ ክፍተቱን የሞላው ከዚያም በኋላ በግራ መስመር ተከላካይነት የተመለከትነው ኢዳላሚን ናስር ናቸው። ከእነርሱ በተጨማሪም እስካሁን በአባ ጅፋር የመሰለፍ ዕድልን ያላገኘው ተካ በዛብህም የዚሁ አሰልጣኝ ፕሮጀክት ፍሬ ነው። አሰልጣኙ ከእነቤካም ዕድል ማግኘት ጋር አያይዞ የአሰልጣኞችን ሚና እንዲህ ይገልፀዋል። “አሰልጣኞች ጋርም የመሰለፍ ዕድል የመስጠት ድፍረት ያስፈልጋል። ያሉበትን ደረጃ መዝኖ የ10 እና የ 15 ደቂቃ ዕድል እየሰጡ ዕድገታቸውን ማስቀጠል ያስፈልጋል። ይህ ከሆነ ልጆቹ ማንነታቸውን የማሳየት አጋጣሚው ይፈጠርላቸዋል። ለምሳሌ ቤካም ባገኘው ዕድል መነጋገሪያ መሆን ችሏል። ይህ በራሱ ብቻውን ትምህርት የሚሰጥ ነው። ሌሎቹ ወጣቶች ላይም ዕምነት ለማሳደር የሚያበረታታ ነው። ዕድሉን ቢያገኙ ደግሞ የሚያሳፍሩ አይሆኑም። ዛሬ 10 ደቂቃ ካገኙ ቀስ በቀስ ሙሉ ጨዋታውን ወደ መሸፈኑ መምጣት ይችላሉ። ይህ እንዲሆን እናንተ ሚዲያዎችም ጫና መፍጠር ይኖርባችኋል። በተለይ በጅማ ሁለቱም ቡድኖች የታዳጊ የዕድሜ እርከን ቡድኖች ሊኖራቸው የግድ ይላል። በፋይናንሱ ረገድ ላለባቸው ጫናም ሌላ መፍትሄ ነው የሚሆናቸው። ወጣቶቹ በተመጣጣኝ ክፍያ ያደጉበትን ከተማ ክለቦች የማገልገል ዕድል ቢያገኙ በሁሉም ረገድ የከተማውን እግር ኳስ ለማነቃቃት ጠቃሚ ነው የሚሆነው። የታዳጊዎች እግርኳስ በትንሽ ፋይናንስ መንቀሳቀስ የሚችል በመሆኑም ለከፍተኛ የዝውውር ሂሳብ እንዳይጋለጡ ክለቦችን ያግዛል።”

ከሁለቱ የጅማ አባ ጅፋር ተስፋዎች በተጨማሪ ከአሰልጣኙ የጅማ ፕሮጀክት ከተገኙ ሌሎች ተጫዋቾች ውስጥ በ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተጫውቶ አሁን በወልዲያ የሚገኘው አድናን ረሻድ የሚገኝበት ሲሆን ሌሎችም በተስፋ ቡድኖች እና በአካዳሚዎች ውስጥ በመጫወት ላይ ይገኛሉ። ቀሪዎቹ ዕድሉ ያልቀናቸው ግን ከፕሮጀክቱ መቆም በኋላ ከስፖርቱ ርቀው አልባሌ ቦታዎች ላይ ጊዜያቸውን እንዲያጠፉ ሆነዋል። የታዳጊነት ጊዜያቸውን ኳሱ ላይ አሳልፈው መዳረሻ ማጣታቸውን አስመልክተው ለሚያቀርቡት ጥያቄ መልስ ያላገኘው አሰልጣኝ ጋሻው በክለብ አመራሮች ላይ ከፍተኛ ቅሬታ አለው። “ኢትዮጵያ ውስጥ ቡድኖች ውጤት ሲያጡ ቀድሞ የሚሰናበተው አሰልጣኝ ነው። እንደ እኔ አመለካከት ግን መሰናበት የሚኖርበት አመራሩ ነው። ቦታው ላይ በኮሚቴ አሰራር ስፔሻላይዝ ያደረጉ ሰዎች አሉ። ዘጠኝ እና አስር ዓመት ቦታው ላይ ሲቀመጡ ይታያል ፤ የጊዜ ገደብ እንኳን የለውም። ቢያንስ የጊዜ ገደብ ኖሮት አገልግለው በሌላ ቢተኩ አንድ ነገር ነው። ሁል ጊዜ አሰልጣኝ በመተካት ብቻ ውጤት ሊመጣ አይችልም። እዛ ጋር የሚቀመጡ ሰዎች የእግርኳሱ ዕውቀት ያላቸው እና አዳዲስ ሀሳቦችን የሚያፈልቁ መሆን ይኖርባቸዋል። አሁን ግን በተለይ ጅማ አካባቢ ሀሳብ ሳይሆን ዕዳ ነው እያፈለቁ ያሉት። እስከሚገባኝ ድረስ ክለቡን በገቢ እንዲጠናከር ማድረግ ሜዳ ላይ ያለውም ቡድን መስመሩን ጠብቆ በወጣቶች ተገንብቶ እንዲዘልቅ ማድረግ ነው የሚጠበቅባቸው። ያ ግን እየሆነ አይደለም። ” የሚለው አስተያየቱም ይህንን የሚጠቁም ነው።

አሁን ላይም በታዳጊዎች ላይ የመስራት ፍላጎቱ ያልበረደው አሰልጣኝ ጋሻው መኮንን በጅማ ያለው ተሰጥኦ ለሁለቱ ክለቦች ብዙ ነገሮችን የመቀየር አቅም እንዳለው ያምናል። ዛሬም ውድድሮችን እየተመለከተ ጥሩ ብቃት በሚያሳዩ ልጆች ላይ ተስፋን ያደርጋል። “ዛሬ ራሱ እንደአጋጣሚ በከተማው የሚደረግ የታዳጊዎች ውድድር ላይ ተገኝቼ ነበር። ያየኋቸው ልጆች በጣም ተሰጥኦ ያላቸው ማስተካከያ ብቻ የሚፈልጉ ዓይነት ናቸው። ለመላው ኦሮሚያ ጨዋታዎች ምርጫ የሚደረጉ የየሰፈሩ ፕሮጀክቶች ውድድሮች ናቸው። ከእነዚህ በተወጣጡ ልጆች ተስፋ ቡድኖችን መስራት ይቻላል። ቁርጠኝነት ያለው አመራር ካለ ልምዱ ያላቸው አማካሪዎችን ሰብስቦ መስራት ይቻላል። አለበለዚያ ግን ዝም ብሎ ቁጭ ብሎ በናይጄሪያ እና በጋና ተጫዋቾች ቦታው ተይዞ ለውጥ ሊመጣ አይችልም። የዚህ ችግር ተፅዕኖ እስከ ብሔራዊ ቡድኑ ድረስም የሚዘልቅ በመሆኑ ከፍ ያላ ትኩረት ያስፈልግዋል። እንደእኔ ዕምነት በ1990ዎቹ ላይ የነበሩት ፕሮጀክቶች ፍሬ ይመስለኛል ኋላ ላይ ለታየው የብሔራዊ ቡድን ውጤት መነሻ የሆነው። አሁንም ቢሆን በሀገር አቀፍ ደረጃ ጥናት ላይ ተመስርቶ ከተሰራበት ውጤት ያመጣል የሚል ዕምነት አለኝ። አስፈላጊ ከሆነም እንደ አቅማችን ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ልምድ መውሰድ እንችላለን።” ይላል።

በመላው ሀገራችን ከመጋረጃ ጀርባ ለተጨዋቾች መገኘት ጉልህ ድርሻ ያላቸው አሰልጣኞች ስለመኖራቸው ማስረጃ መቁጠር አይጠይቅም። እነዚህ ግለሰቦች ያላቸውን ልምድ ትኩረት ሰጥቶ ጥቅም ላይ ማዋል ደግሞ ስፖርቱን ወደ ፊት ማራመድ ስለመቻሉ መገመት አይከብድም። የዛሬው እንግዳችን የነበረው በተለያዩ ትውልዶች ተጫዋቾችን ማብቃት የቻለው አሰልጣኝ ጋሻውም የዚህ እውነት ምስክር ነው። ከአሰልጣኙ ጋር የነበረንን ቆይታ ስንደመድምም በረጅሙ ጉዞው ውስጥ ከጎኑ የነበሩትን አመስግኗል። “አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ጅማ በነበረበት ወቅት ፕሮጀክቴን መጥቶ በማየት ሀሳብ እና አስተያየቶችን ሰጥቶኝ ነበር። በግሉም ፒብሶችን አበርክቶልናል። ከእርሱ በስተቀር ማንም የፕሪምየር ሊግ አሰልጣኝ ወርዶ ፕሮጀክት ላይ የመጣ አልነበረም። ስለዚህ በጣም ነው የማመሰግነው። ከዛ ውጪ የሰይፍ ሆቴል ባለቤት አቶ ይርጋለም ጥላሁን ከጎኔ ሆነው በፋይናንስ ሲያግዙኝ ነበር። ዳንኤል አወቀም እንዲሁ የተለያዩ ቁሳቁሶችን በማቅረብ ያግዘኝ ነበር። አሜሪካን ሀገር የሚገኘው አበባው ጋሻውም በመጣ ሰዓት እንዲሁ ለሥልጠና የሚሆኑ ኳሶችን በማቅረብ ረድቶኛል። እነዚህ ግለሰቦች ለእነዚህ ተጫዋቾች መገኘት የበኩላቸውን በመወጣታቸው ሊመሰገኑ ይገባል።”


© ሶከር ኢትዮጵያ